በተስፋለም ወልደየስ
የእግድ እርምጃ በተወሰደባቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ ተጨማሪ “የማጣራት” እና “የምርመራ” ስራ እያከናወነ መሆኑን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አስታወቀ። ባለስልጣኑ በዚህ ምርምራ ግኝቱ ላይ ተመስርቶ፤ እግዱ “በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንዲነሳ” ሊያደርግ አሊያም ድርጅቶቹ “እንዲፈርሱ” ወይም “እንዲሰረዙ” ለመስሪያ ቤቱ ቦርድ የውሳኔ ሃሳብ ሊያቀርብ እንደሚችልም ገልጿል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተመዘገቡበት ዓላማ መሰረት ስራቸውን ማከናወናቸውን የመከታተል እና የመቆጣጠር ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፤ ባለፈው መንፈቅ ዓመት ብቻ ሰባት ድርጅቶች ላይ የእግድ ውሳኔ አስተላልፏል። ባለስልጣኑ በዚሁ ጊዜ ውስጥ ለ10 ድርጅቶች ማስጠንቀቂያ መስጠቱም፤ ዛሬ ረቡዕ ጥር 28፤ 2017 በፓርላማ በተካሄደ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ይፋ ተደርጓል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የዛሬውን ስብሰባ የጠራው፤ የፍትሕ ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማቱን የስድስት ወር የስራ አፈጻጸም ለመገምገም ነበር። ተጠሪነቱ ለሚኒስቴሩ የሆነው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የስራ ክንውን፤ ለቋሚ ኮሚቴ በቀረበው ሪፖርት ተካትቶ ቀርቧል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዘንድሮው በጀት ዓመት የመንፈቅ ጊዜ ብቻ፤ 271 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን መመዝገቡን ሪፖርቱን ያቀረቡት የፍትሕ ሚኒስትሯ ሃና አርአያ ስላሴ ተናግረዋል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ በ1,331 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ የዴስክ ክትትል መደረጉን ያመለከቱት ሚኒስትሯ፤ “የቁጥጥር ስራን በማጠናከር” በድምሩ በ17 ድርጅቶች ላይ የእግድ እና የማስጠንቀቂያ ውሳኔ መተላለፉን ጠቁመዋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በቀጣይ የቁጥጥር ስራውን ለማጠናከር የሚያስችል፤ “የአደረጃጀት፣ የአሰራር እና የህግ ማሻሻያዎችን” እየሰራ እንደሚገኝም የፍትሕ ሚኒስትሯ ገልጸዋል። በቋሚ ኮሚቴው ስብሰባ የጥያቄ እና ምላሽ ወቅት የመናገር ዕድል የተሰጣቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ፤ መስሪያ ቤታቸው በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ የሚያደርገው “ክትትል፣ ቁጥጥር እና ምርመራ” “ተጠናክሮ ቀጥሏል” ብለዋል።
“የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለተቋቋሙለት ዓላማ፣ በዚያ መስመር ላይ እንዲሰሩ፤ ህግን እና ህግን ብቻ አክብረው እንዲሰሩ ያላሰለሰ ጥረት እያደረግን ነው” ሲሉም አቶ ሳምሶን ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል። እርሳቸው የሚመሩት መስሪያ ቤት፤ “ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ ተንቀሳቅሰዋል” ያላቸውን አራት የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ባለፈው ታህሳስ ወር አጋማሽ ማገዱ ይታወሳል።

ባለስልጣኑ የእግድ እርምጃ ያስተላለፈባቸው ድርጅቶች፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል (EHRDC)፣ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD) እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች (LHR) ናቸው። እነዚህን ጨምሮ ባለፉት ስድስት ወራት የታገዱ ሰባት ድርጅቶች “የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነ” ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ፤ ጉዳያቸው “በህጉ መሰረት” እልባት እንደሚያገኝ አስረድተዋል።
“ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በህጉ መሰረት ሶስት ወር የማገድ ስልጣን አለው። አሁን የታገዱት ድርጅቶች የማጣራት ስራው እየተከናወነ ነው። ሶስት ወር ድረስ አለን። ከዚያ በላይ ማለፍ አንችልም። ከዚያ በላይ ማለፍ ካለበት ለቦርዱ ቀርቦ፤ ቦርዱ ሲፈቅድ ነው። አሁን ሶስት ወር አልሞላም። ባለስልጣኑ የማጣራት ስራውን አጠናቅቆ፤ የመጨረሻ የሚባለው ውሳኔ ይተላለፋል” ሲሉ አቶ ፋሲካው ቀጣይ ሂደቱ ምን እንደሚሆን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።
“እርምጃው ምን ይሁን የሚለውን [ለመወሰን] ተጨማሪ ጥናት፣ ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል። ስለዚህ እርሱን በመነሻ በማድረግ የሚገኘው የመጨረሻ ግኝት ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ይተላለፋል” ሲሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለዋል። በ2011 ዓ.ም. የተሻሻለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ፤ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ “ከባድ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን ሲያረጋግጥ” በዋና ዳይሬክተሩ ትዕዛዝ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን “ከሶስት ወር ላልበለጠ ጊዜ” ማገድ እንደሚችል ደንግጓል።

እገዳው የተላለፈበት ድርጅት በ30 ቀናት ውስጥ ቅሬታውን ለመስሪያ ቤቱ ቦርድ ማቅረብ እንደሚችል በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። በአዋጁ መሰረት 11 አባላት ሊኖሩት የሚገባው ይህ ቦርድ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በሚሰጠው ውሳኔ ላይ የሚቀርቡ ይግባኞችን “የመመርመር” እና “ውሳኔ የመስጠት” ስልጣን አለው። ቦርዱ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ጉዳዩን የሚመረምር “ገለልተኛ አቤቱታ አጣሪ ኮሚቴ” የመሰየም ስልጣን በአዋጁ ተሰጥቶታል።
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቦርድ፤ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሚቀርቡለት ይግባኞች ላይ በሶስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ውሳኔ ካልሰጠ በድርጅቱ ላይ የተላለፈው እገዳ “ቀሪ” እንደሚሆን በአዋጁ ላይ ተቀምጧል። “የዋና ዳይሬክተሩ ውሳኔ በቦርዱ ካልተነሳ ወይም በፍርድ ቤት ካልታገደ በቀር፣ የእገዳ ውሳኔው በተሰጠ በሶስት ወራት ውስጥ ማስተካከያ ያላደረገ ድርጅት እንዲፈርስ ቦርዱ ይወስናል” ሲልም አዋጁ ያትታል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በስተመጨረሻ የሚደርስበት ግኝት “ድርጅቶቹ ‘መፍረስ፣ መሰረዝ አለባቸው’ የሚል ከሆነ፤ በህጉ መሰረት ለቦርድ ይቀርባል” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። “ ‘በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እግዱ ይነሳ’ የሚባል ከሆነ፤ ከማፍረስ በመለስ ያሉ ውሳኔዎች ሁሉ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይወስናል ማለት ነው” ሲሉም አሰራሩን አብራርተዋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ማስጠንቀቂያ የሰጣቸው 10 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጉዳይም በተመሳሳይ መልኩ “በህግ ስርዓቱ” የሚታይ መሆኑን አቶ ፋሲካው አመልክተዋል። “ማስጠንቀቂያ በራሱ እርምጃ ነው። ጥፋታቸው ተጠቅሶ፣ ምን፣ ምን ጥፋት እንዳጠፉ እና ይሄንን ጥፋት ማስተካከል እንደሚገባቸው ተገልጾ፣ ማስጠንቀቂያ ተጽፎላቸዋል። ቅጣት ደርሷቸዋል ማለት ነው። እርምጃ ተወስዶባቸዋል። [ሆኖም] ስራቸውን እየሰሩ ነው” ሲሉ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል።
እነዚህ ድርጅቶች ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ምክንያት የሆነውን “የህግ እና ስርዓት መተላለፍ ጉዳይ” ካላረሙ፤ የጥፋት መጠናቸው ታይቶ “ወደ ቀጣይ እርምጃዎች” ሊገባ እንደሚችልም አቶ ፋሲካው ጥቆማ ሰጥተዋል። ባለስልጣኑ “ድርጅቶቹን አግዶ፣ እንደገና አጣርቶ ከዚያ ወደ መሰረዝ እርምጃ ሊገባ ይችላል” ሲሉም ማስጠንቀቂያ በተሰጣቸው ድርጅቶች ሊወሰዱ የሚችሉ እርምጃዎችን ዘርዝረዋል።
በድርጅቶቹ ላይ የተላለፈው ማስጠንቀቂያ፤ በህግ ቋንቋ ሲገለጽ “እንደ ወንጀል ሪከርድ ተደርጎ የሚወሰድ ነው” ብለዋል ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ። “በቀጣይ ድርጅቱ ማስተካከያ ካላደረገ፤ የድርጅቱ ታሪክ ላይ ‘የድርጅቱ ልምምድ ምንድነው? ባህሪው ምን ይመስላል?’ በሚለው ማስረጃ ሆኖ የሚቀርብ ጉዳይ ነው የሚሆነው” ሲሉም አቶ ፋሲካው አስገንዝበዋል።
“ማስጠንቀቂያ በራሱ እርምጃ ነው። [ድርጅቶቹ] ጥፋታቸው ተጠቅሶ፣ ምን፣ ምን ጥፋት እንዳጠፉ እና ይሄንን ጥፋት ማስተካከል እንደሚገባቸው ተገልጾ፣ ማስጠንቀቂያ ተጽፎላቸዋል። ቅጣት ደርሷቸዋል ማለት ነው”
– አቶ ፋሲካው ሞላ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር
ባለፉት ስድስት ወራት ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው 10 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ውስጥ አብዛኞቹ “በልማት” እና “በአገልግሎት” ስራዎች ላይ የሚሰሩ መሆናቸውን የተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ እገዳ ከተላለፈባቸው ሰባት ድርጅቶች ውስጥ አራቱ በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)