በቤርሳቤህ ገብረ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በአንድ ጊዜ በርካታ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር የሚያወጣው ገንዘብ ምንጭ፤ በከተማይቱ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ አነገጋረ። የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ “የበጀታችን ምንጩ ግብር ነው። የከተማይቱ ግብር ከፋዮች ናቸው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የከተማይቱ ምክር ቤት አባላት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተተገበረ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት የተመለከቱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን የሰነዘሩት፤ ዛሬ ረቡዕ የካቲት 12፤ 2017 በተካሄደ የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው። አቶ ጋትዌች ዎርዲየው የተባሉ የከተማይቱ ምክር ቤት አባል “የኮሪደር ልማት በጀት ምንጩ ከየት ነው?” ሲሉ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ይህ የእርሳቸው ጥያቄ፤ በሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ ፍቃዱ ታምራት በተሰጠ አስተያየት ላይም ተንጸባርቋል። የኮሪደር ልማት ስራው “ከስፋቱ አንጻር ሲታይ፣ ምን ያህል በጀት የወሰደ እንደሆነ ሲታይ፣ ምን ያህል ለውጥ ከተማዋ ላይ እያመጣ እንደሆነ ሲታይ፣ ብቻውን በቂ ነበር” ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ ይህንኑ አስመልክቶ ብዙ ሰዎች “በግርምት” የሚጠይቁት ጥያቄ “የከተማ አስተዳደሩ ይሄን ያህል ገንዘብ ከየት ሊያመጣ ቻለ?” የሚል እንደሆነ አመልክተዋል።

እንደ አቶ ፍቃዱ ሁሉ በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ወራቶች በፕሮጀክቶች ላይ የታየውን አፈጻጸም ያደነቁት ዶ/ር ወርቅነሽ ምትኩ የተባሉ የምክር ቤት አባል፤ “አንድ ከተማ በነበረው ሁኔታ፣ ከነበረው ገቢ፣ ይሄን ሁሉ ስኬት ማሳለጥ የሚችል ከሆነ፤ የት ነበርን? ይህ ገንዘብ ገንዘቡ ፈልቆ ነበር?” ሲሉ በገረሜታ ጠይቀዋል።
“ከዚህ በፊት ስንሰማ የነበርነው ‘ገንዘቡ የት ገባ? የተበጀተው በጀት የት ገባ? የት ወሰዳችሁት?’ የሚል ነበር ብዙ ምክር ቤቶች ሲጠይቁ የነበሩት። አሁን ደግሞ ‘ገንዘቡ ከየት መጣ? ይሄ ሁሉ እንዴት ተሰራ?’ የሚለው በጣም የሚያስደንቅን ነው” ሲሉ ዶ/ር ወርቅነሽ አስተያየታቸው ቋጭተዋል።
በዛሬው መደበኛ ጉባኤ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች የማጠቃለያ ምላሽ የሰጡት ከንቲባ አዳነች፤ የከተማይቱ ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎችን ያነሱት የሚከናወኑት ስራዎች “ከእርዳታ ወይም ከሌላ ሀገር ብድር እያተገኘ ነው” በሚል አመለካከት እንዳልሆነ ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ለሚሰራቸው ፕሮጀክቶች የሚጠቀምበት ገንዘብ በጀት ምንጭ “ግብር” እንደሆነ እና እርሱም የሚገኘው “ከከተማይቱ ግብር ከፋዮች” እንደሆነ አስረድተዋል።

ከንቲባዋ ለዚህ በማስረጃነት የጠቀሱት፤ የአዲስ አበባ ከተማን የበጀት ወይም የገቢ እድገትን ነው። ከሰባት ዓመት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ ዓመታዊ ገቢ 30 ቢሊዮን ብር እንደነበር ያስታወሱት አዳነች፤ ይህ መጠን በመንፈቅ ዓመቱ ብቻ 111.5 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ገልጸዋል። የከተማይቱ አስተዳደር እስከ ዓመቱ መጨረሻ ለመሰብሰብ ያቀደው ገቢ 230 ቢሊዮን ብር እንደሆነም ጠቁመዋል።
“እድገቱ ወደ ስምንት እጥፍ ነው። ይሄ ቀላል አደለም። በሌላ በኩል ደግሞ ከተማዋ የምታመነጨውን ገቢ ስንመለከት፤ ለሀገራችን GDP የምታበረክተውን አቅም ስንመለከት፤ ገና አልተነካም” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወደፊት ተጨማሪ ገቢ የማሰባሰብ ሃሳብ እንዳለው ከንቲባዋ ፍንጭ ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ገቢ በዚህን ያህል ይጨምር እንጂ አስተዳደሩ የታክስ ምጣኔን “እንዳልቀየረ” አዳነች ለምክር ቤቱ አባላት በአጽንኦት አስረድተዋል። “የታክስ rate እንደቀየርን እና ግብር እንደጨመርን የሚነገረው ነገር ስህተት ነው። ማሳያዎች ካሉ መነጋገር እንችላለን። ያደረግነው የታክስ መሰረቱን ማስፋት ነው” ሲሉ ከንቲባዋ ተናግረዋል።

“የታክስ መሰረት ማስፋት” ሲባል ከዚህ ቀደም “ግብር የማይከፍሉ የነበሩ” የማህበረሰብ ክፍሎችን ወደ ግብር ስርዓቱ ማካተት እንደሆነም አዳነች አብራርተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ኃላፊነታቸው ከተወሰነ የግል ድርጅቶች “በትክክል ግብር እያገኘ አንዳልነበር” ከንቲባዋ ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል። በእነዚህ ድርጅቶች ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች “ግብር አይከፍሉንም ነበር” ሲሉም አክለዋል።
ከንቲባዋ “በሺህዎች የሚቆጠሩ” ሲሉ ብዛታቸውን ከጠቀሷቸው ከእነዚህ ድርጅቶች በተጨማሪ በተለያዩ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎችም ትክክለኛ የደመወዝ መጠናቸውን አያሳውቁም ሲሉ ወንጅለዋል። የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ባደረገው ኦዲት ጭምር ማረጋገጡንም አስታውቀዋል።
“ኦዲት ሲደረግ፤ አርክቴክቶች፣ ኢንጂነሮች፣ የተለያዩ የጤና ባለሙያዎች፤ ጀማሪ እንኳን ሆነው የዛሬ 10 እና 15 አመት በማይቀጠሩበት ደመወዝ ነው ሪፖርት የሚያደርጉልን። ትክክለኛ ደመወዛቸውን አግኝተን ስንፈትሽ፣ ኦዲት ስናደርግ፤ በዚያ ልክ የገቢ ግብራቸውን እንዲከፍሉ የማድረግ መስሪያ ቤቱ ይቆርጣል፣ ለራሱ ያስቀራል እንጂ፤ ለሰራተኞቹ አይደለም ሲደርስ የነበረው። እንደዚህ አይነት ማስተካከያዎች ተደርገዋል” ሲሉ አዳነች ተናግረዋል።
“አርክቴክቶች፣ ኢንጂነሮች፣ የተለያዩ የጤና ባለሙያዎች፤ ጀማሪ እንኳን ሆነው የዛሬ 10 እና 15 አመት በማይቀጠሩበት ደመወዝ ነው ሪፖርት የሚያደርጉልን”
– ከንቲባ አዳነች አቤቤ
ከአራት ሺህ በላይ የሆኑ የከተማይቱ ታክስ ከፋዮች፤ ወደ ተጨማሪ እሴት ታክስ ስርአት እንዲገቡ መደረጉንም ከንቲባዋ በዛሬው ማብራሪያቸው ላይ አንስተዋል። እነዚህ ግብር ከፋዮች መጀመሪያውኑ ካፒታላቸው ተጨማሪ እሴት ታክስ “እንዲከፍሉ የሚያስገድዳቸው” እንጂ፤ በእነርሱ ላይ “ድንገተኛ ወይም የተወሰነ ግብር ለመጨመር” በሚል የተላለፈ ውሳኔ እንዳልሆነም አስረድተዋል።
በመርካቶ የገበያ ስፍራ የሚገኙ ነጋዴዎችን ወደ ግብር ስርዓቱ ለማስገባት የተደረገውንም ጥረት፤ ከንቲባዋ ዘለግ ያለ ጊዜ ወስደው ለከተማይቱ ምክር ቤት አባላት አብራርተዋል። ከመርካቶ የሚከፋፈለው ሸቀጥ እና የተለያየ ግብይት “የሀገርን አጠቃላይ የግብር ስርአት የሚያናጋ ነበር” ሲሉም ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
“እነ መርካቶ የማይሞከሩ ነበሩ። የማይሞከሩ ቦታዎች ወይንም የሚፈሩ ሆነው፤ ግብር የሚከፍለው ነጋዴ የሚጎዳባቸው ናቸው። ነገር ግን ደግሞ በአጭር መንገድ እየከበሩ ያሉ፣ ግብር የማይከፍሉ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ያለበት ነበር” ሲሉም ከንቲባዋ አክለዋል። “አሁንም ‘አልቋል፤ በጣም ተጠናክሯል’ ባንልም፤ ነገር ግን ለውጦችን ማየት ጀምረናል” ሲሉ የከተማ አስተዳደሩ በወሰዳቸው እርምጃዎች በጎ መሻሻሎች እንዳሉ አዳነች አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚያገኘው ገቢ “አስተዋጽኦ አድርገዋል” በሚል በከንቲባዋ ከተጠቀሱ ጉዳዮች ውስጥ “ብክነት እና ብልሹ አሰራር መከላከል” የሚሉ ይገኙበታል። አዳነች ለዚህ በማሳያነት ያነሱት፤ ለግብር ስረዛ የቀረቡ ዶክመንቶች ላይ ባለፉት ስድስት ወራት በተደረገ ፍተሻ 10 ቢሊዮን ብር “ማዳን መቻሉን” ነው።
“እንዲሰረዝ የቀረበ 10 ቢሊዮን ብር ሲፈተሽ፤ ‘ንብረት የላቸውም፣ ገቢ የላቸውም፣ ድርጅቶቹ ከስረዋል’ የሚሉ ምክንያቶች ናቸው የቀረቡት። ሲፈተሽ ግን ተሽከርካሪዎች አሏቸው። ትልልቅ የንግድ ተቋም አላቸው። ትራንዛክሽናቸው ሞቅ ያለ ነው” ሲሉ ከንቲባዋ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)