በቤርሳቤህ ገብረ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰራተኞች “በሁለት እና በሶስት መስሪያ ቤቶች ተቀጥረው” ደመወዝ ሲከፈላቸው እንደነበር የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ። የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ሰራተኞች “ተጠያቂ ማድረጉንም” ከንቲባዋ ገልጸዋል።
አዳነች ይህንን የገለጹት፤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዛሬ ረቡዕ የካቲት 12፤ 2017 እያካሄደ ባለው መደበኛ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ነው። ከንቲባዋ በዚሁ ሪፖርታቸው፤ የከተማ አስተዳደሩ የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ መረጃ አያያዝ ስርዓት ተግባራዊ በማድረጉ፤ በስሩ ምን ያህል ሰራተኞች እንዳሉት ለማወቅ እንደቻለ ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ 168 ሺህ ያህል ሰራተኞቹን ፋይል “ስካን አድርጎ” ወደ ስርዓቱ እንዲገባ ካደረገ በኋላ በተደረገው ማጣራት፤ ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰራተኞች “ያለአግባብ በሁለት እና በሶስት መስሪያ ቤቶች ተቀጥረው” ደመወዝ እንደሚከፈላቸው እንደተደረሰበት አብራርተዋል። የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ሰራተኞች “ተጠያቂ” ማድረጉን አዳነች በሪፖርታቸው ቢጠቅሱም፤ የተወሰደባቸው እርምጃ ምን እንደሆነ ግን በዝርዝር ሳይገልጹ ቀርተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስሩ ያሉ ሰራተኞችን መረጃ በቴክኖሎጂ ታግዞ ለመያዝ የሚያስችለውን ስርዓት መተግበር መጀመሩን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስታወቀው ከአራት ዓመት በፊት ነው። ይህ የሲቪል ሰርቪስ የመረጃ አያያዝ ስርዓት፤ ሰራተኞቹ ከቅጥር ጀምሮ እስከ ሚሰናበቱበት ጊዜ ድረስ ያለውን መረጃ ለማጠናቀር የሚያስችል እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
የአዲስ አበባ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ በታህሳስ 2015 ዓ.ም ባወጣው መረጃ፤ የከተማ አስተዳደሩን 162 ሺህ ሰራተኞች የሰው ሀብት መረጃዎች ወደዚህ ስርዓት የማስገባት ስራ “ሙሉ ለሙሉ ማጠናቀቁን” አስታውቆ ነበር። በቀጣይም አዲስ የተከናወኑ ቅጥሮችን እና ዝውውር በተካሄደባቸው ተቋማት ያሉ የሰው ሀብት መረጃዎችን፤ ወደ ስርዓቱ የማስገባት ስራዎችን እንደሚያከናውን ቢሮው በወቅቱ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)