የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችላቸው አዋጅ “ጊዜውን የጠበቀ አይደለም” በሚል ተተቸ 

በቤርሳቤህ ገብረ

የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቅስ ንብረት ባለቤት እና ባለይዞታ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው አዋጅ “ጊዜውን የጠበቀ አይደለም” በሚል በፓርላማ አባላት ተተቸ። ትችቱ የቀረበው ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 12፤ 2017 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው።

ምክር ቤቱ በዚሁ ስብሰባው፤ የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ መሬትን በሊዝ በባለቤትነት መያዝ በሚያስችላቸው የአዋጅ ረቂቅ ላይ ተወያይቷል። የአዋጅ ረቂቁ የተዘጋጀው የኢትዮጵያውያንን “የመሬት ይዞታ የማግኘት እና የመጠቀም መብት በማያጣብብ መልኩ”፤ የውጭ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት እንዲሆኑ አሊያም ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል መሬት የሚያገኙበትን ህጋዊ አሰራር ለመዘርጋት እንደሆነ ተገልጿል።

በአራት ክፍሎች እና በ20 አንቀጾች የተከፋፈለው ይህ የአዋጅ ረቂቅ፤ የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ ለመሆን ማሟላት ስለሚጠበቅባቸው ቅድመ ሁኔታዎች፣ የፈቃድ አሰራሮች፣ ገደቦች፣ መብቶች እና ግዴታዎች አካትቶ ይዟል። የህግ ረቂቁ በዝርዝር እንዲታይ ለተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ከመመራቱ አስቀድሞ በተደረገ ውይይት ላይ፤ ሁለት የፓርላማ አባላት ትችት አዘል ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል።

የአዋጁ ዋና ዓላማ “የውጭ ካፒታል ወደ ሀገር ውስጥ ማምጫ” እና “የውጭ ምንዛሬ ማግኛ እንደሆነ” መገንዘባቸውን የገለጹት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ተወካዩ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ በህግ ረቂቁ ላይ ያላቸውን ስጋቶች እና አስተያየቶች በዝርዝር አቅርበዋል። የፓርላማ አባሉ ለስጋታቸው በምክንያትነት ካስቀመጧቸው ጉዳዮች አንዱ የሀገሪቱ የነፍስ ወከፍ ገቢ እና ደመወዝ በአለም አቀፍ ደረጃ ካለው ሲነጻጸር ያለውን ልዩነት ነው።

“የእኛ ሀገር የነፍስ ወከፍ ገቢ፣ የእኛ ሀገር ደመወዝ፣ ከአለም አቀፍ ስታንዳርድ ጋር ሲታይ፤ ከነጮች ጋር ተወዳድሮ፣ በተለይ እንደ አዲስ አበባ እና ሌሎች ትልልቅ ከተሞች የቤት ባለቤት መሆን ዜጎች ይቸገራሉ” ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ፤ አዋጁ በእነዚህ ከተሞች ያለውን የቤት መግዣ ዋጋ “በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሻቅብ” በማድረግ የዜጎችን ቤት የማግኘት አቅም ሊፈታተነው እንደሚችል ያላቸው ስጋት ገልጸዋል።

የፓርላማ አባሉ “የቅኝ ግዛት ሌጋሲ ያለባቸው” ባልዋቸው ከተሞች፤ “የተወሰኑ” ሰፈሮች በውጭ ሀገር ዜጎች የተያዙ እና የሀገሪቱ ዜጎች በዚያ አካባቢ የቤት ባለቤት መሆን “የተገለሉባቸው” እንደሆኑ አስረድተዋል። ለዚህም በምሳሌነት የደቡብ አፍሪካ ከተሞች የሆኑትን ኬፕታውን እና ጆሀንስበርግን ጠቅሰዋል። “ድሃው ከዋና ከተሞች እየተነቀለ ወደ ዳር የሚገፋበት እና መሀሉ ደግሞ ለውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች እየተመቻቸ የሚሰጥበትን ሁኔታ እንዳይፈጥር ስጋት አለኝ” ሲሉም አክለዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ ሌላው በስጋትነት ያነሱት ጉዳይ አዋጁ ወደ ውጭ የሚደረግን የካፒታል ሽሽት “ሊያበረታታ ይችላል” የሚል ነው። “አንድ ባለሀብት ይመጣል ይገዛል። ትርፉን ወደሀገሩ ትራንስፈር ያደርጋል። ቤት መግዛት፣ መሸጥ ውስጥ መሰማራት ስለሚችል የታክስ ስወራ፣ የህገወጥ የገንዘብ ዝውውር በከፍተኛ ሁኔታ ሊያባብስ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ” ሲሉ ለፓርላማ አባላት አስረድተዋል።

የውጭ ሀገር ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት እና ባለይዞታ እንዲሆኑ የሚያስችለው የአዋጅ ከብሔራዊ ደህንነት አንጻር “በደንብ ሊታይ” እንደሚገባውም የፓርላማ አባሉ አሳስበዋል። “የመከላከያ፣ የደህንነት ተቋሞቻችን randomly  ከመኖሪያ ቤት አካባቢ ነው የሚሰፍሩት። ለሀገራች የደህንነት ስጋት ሊፈጥሩ የሚችሉ የውጭ ሀገር ግለሰቦች መጥተው፤ አንድ ሪል ስቴት ወይም አፓርታማ ገዝተው በእነዚህ ተቋሞቻችን ላይ ስጋት ሊፈጥሩ ይችላሉ” ብለዋል ዶ/ር ደሳለኝ።

“የተወሰኑ ሀገራት ዜጎች” ወይም “ዜግነት የሌላቸው የውጭ አገር ሰዎች” የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ እንዳይሆኑ “የሚከለክል” መመሪያ ወደፊት ሊወጣ እንደሚችል በአዋጁ ላይ የተቀመጠውን ድንጋጌ ላይም የፓርላማ አባሉ አስተያየት ሰጥተዋል። “እሱን መወሰን አስቸጋሪ ይመስለኛል። ‘ከሀገራችን ጋር ጥሩ ግንኙነት የላቸውም’ የሚባሉ ዜጎችን ‘መከልከል’ ተብሎ ነው የታሰበው። ግን ይህን በተግባር ማውረድ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል። 

“አዋጁ ጊዜውን የጠበቀ ነው ብዬ አላስብም። ወደፊት የዜጎች የቤት ባለቤትነት ይዞታ ተረጋግጦ የregulatory አቅማችን አድጎ፣ በኢኮኖሚያችን የተሻለ የመወዳደር አቅም ባለበት ሁኔታ እና ዜጎች የተሻለ የመወዳደር አቅም ሲያዳብሩ እንደዚህ አይነት አዋጆች ቢወጡ የተሻለ ነበር ብዬ አስባለሁ”

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ የአብን የፓርላማ አባል

የአብኑ የፓርላማ አባል የሀገሪቱ ዜጎች የመሬት ባለቤትነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ አዋጅ የማውጣት “አስፈላጊነት” ላይም ጥያቄ አንስተዋል። ዶ/ ደሳለኝ አስተያየታቸው ያጠቃለሉት “አዋጁ ጊዜውን የጠበቀ ነው ብዬ አላስብም” በማለት ነው። “ወደፊት የዜጎች የቤት ባለቤትነት ይዞታ ተረጋግጦ የregulatory አቅማችን አድጎ፣ በኢኮኖሚያችን የተሻለ የመወዳደር አቅም ባለበት ሁኔታ እና ዜጎች የተሻለ የመወዳደር አቅም ሲያዳብሩ እንደዚህ አይነት አዋጆች ቢወጡ የተሻለ ነበር ብዬ አስባለሁ” ሲሉም የህግ ረቂቁ በአሁኑ ወቅት መቅረቡን ተችተዋል። 

እንደ እርሳቸው ሁሉ አብንን ወክለው ፓርላማውን የተቀላቀሉት ዶ/ር አበባው ደሳለውም፤ ተመሳሳይ ሀሳብ አንጸባርቀዋል። “መጀመሪያ ዜጎቻችን ኑሮዋቸው እንዲሻሻል፣ የመሬት ፣ የቤት ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ህገ መንግስቱም እንዲሻሻል አድርገን፣ ከዚያ በኋላ ይህን አዋጅ ወደ ምክር ቤቱ ብናመጣው ይሻላል” ሲሉ ተደምጠዋል። 

የአዋጅ ረቂቁ በዚህ ጊዜ ለፓርላማ መቅረቡን “እንደማይደግፉ” የገለጹት ዶ/ር አበባው፤ ለዚህ ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች ዘርዝረዋል። የፓርላማ አባሉ በቅድሚያ ያነሱት፤ መሬትን በተመለከተ በኢፌዴሪ የተቀመጠውን ድንጋጌ ከአዲሱ አዋጅ አንጻር እንዴት እንደሚታይ ነው።   

“ህገ መንግስቱ መሬት የጋራ ንብረት እንደሆነ እንደማይሸጥ እንደማይለወጥ ይደነግጋል። አሁን እያልን ያለነው የውጭ ባለሀብቶች ነው። ሁለተኛ የጋራ ንብረት ሳይሆን የግለሰቦች ነው እያልን ነው። ሶስተኛ መሸጥ መለወጥ እንደሚችል እየደነግግን ስለሆነ በእነዚህ ሶስት ሁኔታዎች ምክንያት ከህገ መንግስት ጋር የሚጣረስ አዋጅ እያወጣን እንዳይሆን እሰጋለሁ” ብለዋል።

የህግ ረቂቁ ተግባራዊ መደረግ ሲጀምር የመግዛት አቅም ባለው እና በሌለው የህብረተሰብ ክፍል መካከል ልዩነት በመፍጠር ጫና እንደሚፈጥርም የፓርላማ አባሉ አመልክተዋል። በሀብታም እና ድሃ ዜጎች መካከል ልዩነት “ከፍ ያለ” መሆኑን በአስተያየታቸው የጠቆሙት ዶ/ር አበባው፤ የውጭ ዜጎች በብዛት ወደ ሀገሪቱ የሚገቡበት ሁኔታ ሲፈጠር፤ ይህ ልዩነት “የበለጠ” ከፍ ሊል እንደሚችል አስረድተዋል። 

“እንደሚታወቀው ሪሶርሶች ውስን ናቸው። ነገር ግን ፍላጎት በጨመረ ቁጥር ያለን የሪሶርሶች ዋጋ ከፍ ይላል። ድሃዎች ኑሮውን የመቋቋም አቅማቸው የበለጠ ዝቅ እያለ ይመጣል። ወደፊትም መቋቋም አቅቷቸው ከጨዋታው ውጪ ይሆናሉ” ሲሉ የአብኑ የፓርላማ አባል መጪውን ጊዜ ተንብይዋል።

“እንደሚታወቀው ሪሶርሶች ውስን ናቸው። ነገር ግን ፍላጎት በጨመረ ቁጥር ያለን የሪሶርሶች ዋጋ ከፍ ይላል። ድሃዎች ኑሮውን የመቋቋም አቅማቸው የበለጠ ዝቅ እያለ ይመጣል። ወደፊትም መቋቋም አቅቷቸው ከጨዋታው ውጪ ይሆናሉ”

– ዶ/ር አበባው ደሳለው፤ የአብን የፓርላማ አባል

አዲሱ አዋጅ ሙስና እንዲስፋፋ ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ዶ/ር አበባው ስጋታቸውን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ሙስና የመዋጋት ዘመቻ “እየተቀዛቀዘ እና እየተዳከመ መሆኑን መንግስት የሚያምነው ጉዳይ ነው” ያሉት ዶ/ር አበባው፤ የውጭ ባለሀብቶች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ይዘው በሚመጡበት ጊዜ ባለስልጣኖቻችን “በማማለል” የበለጠ ሙስና እንዲስፋፋ ሊያደርግ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል። 

እንዲህ አይነቱ አካሄድ “ህዝብ ሳይጠቀም ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል” ብለዋል። ዜጎች የሀገራቸው መሬት እና ሀብት ተጠቃሚ ሳይሆኑ በከፍተኛ ደረጃ ሌብነት እና ስርአት አልበኝነት ሊስፋፋ እንደሚችል የጠቆሙት የፓርላማ አባሉ፤ እንዲህ አይነት ሁኔታ በኬንያ እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሚታይ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ያ አይነት ሁኔታ እንዳይፈጠር ስጋት አለ። ስለዚህ ቅደመ ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው” ሲሉ ዶ/ር አበባው አሳስበዋል። ሁለቱ የአብን የፓርላማ አባላት የተቹት የአዋጅ ረቂቅ፤ በዋነነት ለከተማ እና መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ደግሞ ለህግ እና ፍትህ ጉዳዮች በዝርዝር እንዲመለከቱት ተመርቶላቸዋል። የአዋጅ ረቂቁ ለኮሚቴዎቹ መመራቱን ሶስት የፓርላማ አባላት ተቃውመውታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)