ውናት በትግራይ እስከ አመጽ ድረስ የሚሄድ የህዝባዊ እምቢተኝነት የፖለቲካ ትግል እንደሚያካሄድ አስታወቀ

በሁለት ጎራ የተከፈሉት የህወሓት ፖለቲከኞች ከብልጽግና ፓርቲም ሆነ ከሻዕቢያ ጋር “የፈጠሩትን ህብረት” እንደማይቀበለው የውድብ ናፅነት ትግራይ (ውናት) ፓርቲ ገለጸ። በክልሉ ህወሓት በብቸኝነት የሚቆጣጠረውን የፖለቲካ ስርዓት “አደብ ለማስያዝ”፤ “እስከ አመጽ ድረስ የሚሄድ”፣ “ህጋዊ የሆነ”፣ “የህዝባዊ እምቢተኝነት የፖለቲካ ትግል” ለማካሄድ መወሰኑን ፓርቲው አስታውቋል። 

ውናት ይህን ያስታወቀው፤ የፓርቲው ምክር ቤት ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 9፤ 2017 ዓ.ም ያካሄደውን የፓርቲው ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በማስመልከት በዛሬው ዕለት በመቐለ ከተማ በሚገኘው ጽህፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ ነው። የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ደጀን መዝገበ፤ የውናት ምክር ቤት በወቅታዊ ክልላዊ እና ቀጠናዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ያሳለፈውን ውሳኔ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል። 

በፓርቲው ምክር ቤት ጉባኤ ላይ በዋነኛነት የተነሳው ጉዳይ፤ በሁለት ጎራ የተከፈሉት የህወሓት አመራሮች ከሌሎች አካላት ጋር እያደረጉት ያለውን ግንኙነት የተመለከተ እንደሆነ ዶ/ር ደጀን ተናግረዋል። ሁለት የህወሓት ጎራዎች ከኤርትራው ህግደፍ እና ከብልጽግና ፓርቲ ጋር የፈጠሩት ወዳጅነት፤ በትግራይ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አንደምታ ጉባኤው እንደተወያየበትም ገልጸዋል።

“ህወሓት በውስጡ ባጋጠመው መከፋፈል ምክንያት ገሚሱ ከብልጽግና ጋር፤ ገሚሱ ደግሞ ከሻዕቢያ ፓርቲ ጋር ‘ህብረት እንደርጋለን’ እያሉ ወዳልተፈለገ ሌላ ዙር ጦርነት ልንገባ የምንችልበት ሁኔታ በስፋት እየታየ ነው ያለው” ሲሉ የፓርቲው ሊቀመንበር ተናግረዋል። በእነዚህ ኃይሎች የሚፈጠር ጦርነት “የትግራይ ህዝብ ጦርነት ሊሆን አይችልም” ሲሉም በጉዳዩ ላይ ፓርቲያቸው ያለውን አቋም አስታውቀዋል። 

“ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሚያደርጉት ማንኛውም ግንኙነት የትግራይን ህዝብ የሚመለከት አይደለም። ይሄ ማለት ወላፈኑ አያገኘንም ማለት አይደለም። ነገር ግን የትግራይ [ህዝብ] እሰዋለታለሁ ብሎ የሚታገለልት አላማ አይደለም ማለት ነው። ኤርትራ ኢትዮጵያ ላይ ያለው ጥያቄም ይሁን፤ ኢትዮጵያ ኤርትራ ላይ ያለው ጥያቄ እኛን እንድንሰዋ የሚያደርግ አይደለም” ብለዋል ዶ/ር ደጀን።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም አይነት ውክልና የለንም” ያሉት የውናት ሊቀመንበር፤ ለዚህም በአሁኑ ወቅት በተወካዮችም ሆነ በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የትግራይ ተወካዮች አለመኖራቸውን በማሳያነት አንስተዋል። የትግራይ ክልል በሀገር መከላከያ ሰራዊትም ሆነ በብዙ የፌደራል መንግስታዊ ተቋማት “ውክልና የለውም” ሲሉም አክለዋል።

በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ መንግስት ትግራይን “አስገድዶ”፣ “ወደ ራሱ አጀንዳ ጎትቶ ወስዶ፣ “ውጊያ ውስጥ ሊያሰማራ አይችልም” ሲሉ ዶ/ር ደጀን ጠንከር ያለ አቋማቸውን አስደምጠዋል። “ኤርትራ ደግሞ ሌላ ሀገር ነው። ከኤርትራ ጋር ህብረትም ይሁን ግንኙነት ሊኖረን አይችልም” ሲሉም አክለዋል። በዚህ ምክንያት ፓርቲያቸው “የተሰላ ገለልተኝነት” (calculated neutrality) የተሰኘ ፖሊሲ እንደሚከተል አስረድተዋል። 

ከሻዕቢያ ጋር በአሁኑ ወቅት ግንኙነት እንደፈጠረ በተለያየ መልኩ እየተገለጸ ያለው የህወሓት ጎራ፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን ስልጣን ህወሓት በኃይል ታግዞ መቆጣጠሩን ዶ/ር ደጀን በዛሬው መግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል። ውናት ይህንን አካሄድ እንደሚቃወም የፓርቲው ሊቀመንበር ገልጸዋል።   

በትግራይ ክልል ጉዳይ “ህወሓት ብቻውን የሚወስንበት ሁኔታ” እንዲያበቃ “የህዝባዊ እምቢተኝነት” ትግል ለማካሄድ ውናት ከውሳኔ ላይ መድረሱን ዶ/ር ደጀን ተናግረዋል። “ህወሓት በብቸኝነት የሚቆጣጠረው ፖለቲካ ሆነ የብሔራዊ ጥቅም አይኖርም። ስለዚህ ይህን አደብ ለማስያዝ የፖለቲካ ትግል እናደርጋለን። ህዝባዊ እምቢተኝነትን እናሳያለን። አመጽን ጨምሮ ህጋዊ የሆነ የፖለቲካዊ ተቃውሞ እና ትግል እናደርጋለን” ሲሉም ውናት በቀጣይ ሊያካሄደው ያቀደውን እንቅስቃሴ ይፋ አድርገዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)