በኢትዮጵያ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎች የሚፈስሰውን የአውሮፓ መዋዕለ ንዋይ ለማሳደግ ያለመ ኮንፍረንስ በፈረንሳይ ፓሪስ ሊካሄድ ነው። ከአንድ ወር በኋላ በሚካሄደው በዚህ ኮንፍረንስ ላይ ከ100 በላይ የአውሮፓ ኩባንያዎች ተወካዮች ይታደማሉ ተብሏል።
በመጪው ጥቅምት 24፤ 2018 የሚካሄደውን ይህን ኮንፍረንስ በጋራ ያዘጋጁት የፈረንሳይ ቢዝነስ ኮንፌዴሬሽን (Medef) እና የአውሮፓ ኮሚሽን ናቸው። የፈረንሳይ ቢዝነስ ኮንፌዴሬሽን 173 ሺህ ኩባንያዎች አባል የሆኑበት እና በሀገሪቱ የሚገኙ ዋነኛ ቀጣሪዎችን በስሩ ያቀፈ ቁልፍ ተቋም ነው።
ኮንፌዴሬሽኑ ለሚመለከታቸው አካላት በዛሬው ዕለት ባሰራጨው እና “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው የግብዣ ጥሪ፤ ኢትዮጵያን በሚመለከት በሚዘጋጀው ኮንፍረንስ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ተቋማት፣ የልማት ፋይናንስ ተቋማት እና የቢዝነስ ተወካዮች እንደሚሳተፉ አስታውቋል። የኢትዮጵያ መንግስትን በመወከል በፓሪሱ ኮንፍረንስ ላይ ይገኛሉ ተብለው የሚጠበቁት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ናቸው።
ለፓሪሱ ኮንፍረንስ ከተመረጡ ዘርፎች መካከል በቀዳሚነት የተቀመጡት ትራንስፖርት፣ ሎጂስቲክስ እና የመሰረተ ልማት ግንባታ ናቸው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ የሚያስገነባው አየር ማረፊያ በኮንፍረንሱ በዋነኛነት ከሚቀርቡ የኢንቨስትመንት አማራጮች አንዱ እንደሚሆን በግብዣ ሰነዱ ላይ ተመልክቷል።
ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ይጠይቃል ተብሎ ለሚጠበቀው የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ ግንባታ፤ የአፍሪካ ልማት ባንክ ብድር የማፈላለግ ኃላፊነቱን ወስዷል። ከአዲስ አበባ በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚያርፈው እና በዓመት 60 ሚሊዮን ተጓዦች የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል ተብሎ በሚጠበቀው ፕሮጀክት፤ አሜሪካ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት ፍንጭ ሰጥታለች።
ይህንን የአሜሪካ ፍላጎት ከአንድ ሳምንት በፊት በሰጡት መግለጫ ላይ ያሳወቁት በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ማሳድ ቡሎስ ናቸው። በዚህ ወር መጀመሪያ ወደ አዲስ አበባ መጥተው የነበሩት ቡሎስ፤ ከፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ይታወሳል።

ከፍተኛ አማካሪው ከጉብኝታቸው በኋላ በሰጡት መግለጫ፤ የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ ሲጠናቀቅ “ምናልባትም ከአፍሪካ ትልቁ ይሆናል” ሲሉ የፕሮጀክቱን ግዝፈት አመልክተው ነበር። ቡሎስ በዚሁ መግለጫቸው የአየር ማረፊያውን ፕሮጀክት የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (DFC) እና ሌሎች ተቋማት “እየደገፉ ነው” ቢሉም፤ ድጋፉን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ ቀርተዋል።
የፓሪሱ ኮንፍረንስ የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ ፕሮጀክት ከሚካተትበት የትራንስፖርት እና የመሰረተ ልማት ዘርፎች በተጨማሪ የቴሌኮሚዩኒኬሽን፣ የታዳሽ ኃይል፣ የዲጂታል፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሺያል ኢንተለጀንስ) ዘርፎች ላይም ትኩረት እንደሚያደርግ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
ከተመረጡት ከእነዚህ ዘርፎች በተጨማሪ የኢትዮጵያ የቢዝነስ ከባቢን በተመለከተ እንዲሁም በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ አጋርነት (PPP) ስለሚሰሩ ፕሮጀክቶች ውይይት ይካሄዳል ተብሏል። በአውሮፓ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት “ለማደስ” እንዲሁም የንግድ ልውውጦችን “ለማፋጠን” ባለመው የፓሪሱ ኮንፍረንስ፤ በሚያዝያ 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሊካሄድ በታቀደው የአውሮፓ ህብረት እና የኢትዮጵያ ኮንፍረንስን በተመለከተ ውይይት እንደሚደረግ ከአዘጋጆቹ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኮንፍረሱ አዘጋጆች፤ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና በበርካታ ዓለም አቀፍ አጋሮች ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለአውሮፓ ኩባንያዎች “መነቃቃት” መፍጠሩን ገልጸዋል። ቴሌኮም፣ ሎጂስቲክስ እና ኢነርጂን በመሳሰሉ ዘርፎች የተሰማሩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ካፒታል “ቀስ በቀስ መከፈት”፣ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ዘርፎች “መፋጠን” እንዲሁም የዲጂታል ዘርፉ ዕድገት፤ በዘርፎቹ ለመሳተፍ ዝግጁ ለሆኑ ኩባንያዎች “ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ዕድሎች እየፈጠሩ ነው” ብለዋል።
አውሮፓውያኑ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ ተስፋቸውን በዚህ መልኩ ቢገልጹም፤ የአሜሪካ መንግስት ከሳምንት በፊት ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት ግን የሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለአሜሪካም ሆነ ለውጭ ቢዝነሶች “ፈታኝ” እንደሆነ አስታውቆ ነበር። ይኸው ሪፖርት፤ የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይን ለመሳብ “ጉጉ” ቢሆንም፤ በዚህ ረገድ ላሉ በርካታ “እጥረቶች” በአብዛኛው መፍትሔ መስጠት አለመቻሉን በማንሳት ተችቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)