በመሬት መንቀጥቀጥ “ከፍተኛ ጉዳት” የደረሰበት የከሰም ስኳር ፋብሪካ፤ ሰራተኞቹን በመጪዎቹ ወራት ሊያሰናብት ነው 

በቤርሳቤህ ገብረ

ባለፉት ወራት በተደጋጋሚ በተከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦች “ከፍተኛ ጉዳት” የደረሰበት የከሰም ስኳር ፋብሪካ፤ ከአንድ ሺህ በላይ ሰራተኞቹን እስከ መጪው ግንቦት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ለማሰናበት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሰጠ። የስኳር ፋብሪካው የሰራተኞች ማህበር በበኩሉ ሰራተኞቹ ሳይሰናብቱ ወደ ሌሎች ፋብሪካዎች እንዲበተኑ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል።

ከአዲስ አበባ በስተምስራቅ በ250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የከሰም ስኳር ፋብሪካ ስራ የጀመረው በ2008 ዓ.ም ነው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2014 ዓ.ም ባወጣው ደንብ ራሳቸውን እንዲያስተዳደሩ ካደረጋቸው አምስት የስኳር ፋብሪካዎች አንዱ የከሰም ስኳር ፋብሪካ ነው። 

በስሩ ከአራት ሺህ በላይ ሰራተኞችን የሚያስተዳድረው የከሰም ስኳር ፋብሪካ፤ የቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት የሰራተኞቹን የስራ ውል ያቋረጠው ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የካቲት 11፤ 2017 ዓ.ም ባወጣው ማስታወቂያ ነው። በፋብሪካው የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ የተለጠፈው እና “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይህ ማስታወቂያ፤ የስራ ውላቸው የተቋረጠ ከአንድ ሺህ በላይ ሰራተኞችን ስም ዝርዝር የያዘ ነው።

የከሰም ስኳር ፋብሪካ የሰው ሀብት ስራ አመራር እና አቅርቦት ዘርፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ዝናቡ ብርሃኑ ፊርማ ያረፈበት ማስታወቂያ፤ ፋብሪካው ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከታህሳስ 20 ጀምሮ በተደጋጋሚ የተከሰተው ርዕደ መሬት ባስከተለበት “ከፍተኛ ጉዳት” መሆኑን ያስረዳል። የስኳር ፋብሪካው በዚህ ምክንያት “ስራውን ሙሉ ለሙሉ ያቆመ በመሆኑ”፤ በማስታወቂያው ስማቸው የተዘረዘረ ሰራተኞቹ የስራ ውል ከየካቲት 10፤ 2017 ጀምሮ “በቅደመ ማስጠንቀቂያ” መቋረጡንም አትቷል።

የፋብሪካው ሰራተኞች ለስራ የተረከቡትን ማንኛውም የድርጅቱን ንብረቶች እና ሰነዶች በማስረከብ “ከእዳ ነጻ ማረጋገጫ አስፈራርመው እንዲያቀርቡ” በዚሁ ማስታወቂያ ታዝዘዋል። በማስታወቂያው ላይ የስም ዝርዝራቸው ያልተገለጸ ሰራተኞች “በጊዜያዊነት ለድርጅቱ ስራ የቀሩ መሆኑን” የገለጸው ፋብሪካው፤ ሆኖም እነርሱም ቢሆኑ “ለወደፊት በሂደት እንደሚሰናበቱ” አስታውቋል።

ይሁንና በዚያው ዕለት ፋብሪካው ማስተካከያ በማድረግ በለጠፈው ማስታወቂያ፤ ሰራተኞቹ ከየካቲት 10 ቀን ጀምሮ መሰናበታቸውን በማስቀረት ከዚሁ ቀን ጀምሮ እንደ የአገልግሎት ቆይታቸው ቅድመ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑን ገልጿል። በማስታወቂያው ከስራ መሰናበታቸውን የተረዱት የፋብሪካው ሰራተኞች፤ በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ባሉበት የስራ ውላቸው መቋረጡ ተገቢ አለመሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

በከሰም ስኳር ፋብሪካ ላለፉት ሰባት ዓመት በመካኒክነት የሰሩት አቶ ይድነቃቸው አባቡ፤ ከስራ የተሰናበቱት “ህግን ባልተከተለ መልኩ ነው” ባይ ናቸው። ከድርጅቱ ጋር የነበራቸው የስራ ውል መቋረጡን የሚገልጽ ደብዳቤ በግል እንዳልደረሳቸው የሚጠቅሱት አቶ ይድነቃቸው፤ ፋብሪካው “የሶስት ወር እንኳን ደመወዝ በስርዓት ሳይሰጠን፤ ህገወጥ በሆነ መንገድ ደብዳቤ ለጥፎ አሰናብቶናል” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የከሰም ስኳር ፋብሪካ ባለፈው ሳምንት ባወጣው ማስታወቂያ ላይ ሰራተኞቹ የግል ደብዳቤያቸውን ከድርጅቱ የሰው ሀብት አስተዳደር ቡድን መውሰድ እንደሚችሉ አመልክቷል። በዚሁ ማስታወቂያ ላይ ስማቸው የተካተተው አቶ ይድነቃቸው፤ እስካለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ የቀጠለውን የመሬት መንቀጥቀጥ በመስጋት የስራ እና የመኖሪያ አካባቢያቸውን ለቅቀው በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ናቸው።

እንደ አቶ ይድነቃቸው ሁሉ የመፈናቀል እጣ ፈንታ የገጠማቸው ሌላኛው የድርጅቱ ሰራተኛ አቶ ሱልጣን ሎኦይታ፤ ፋብሪካው ሰራተኞቹን ሳይነጋግር እና ሳያወያይ ከስራ ማሰናበቱ ቅር ተሰኝተዋል። የስኳር ፋብሪካው ለሰራተኞቹ ባስገነባው ቤት ይኖሩ የነበሩት አቶ ሱልጣን፤ በርዕደ መሬቱ ምክንያት ከተፈናቀሉ ሁለት ወር ሆኗቸዋል። 

በዚህ ጊዜ ውስጥ የአንድ ወር ደመወዝ ማግኘታቸውን የሚናገሩት አቶ ሱልጣን፤ በአሁኑ ወቅት ተፈናቅለው ከሚገኙበት “አዲስ ራዕይ” በተባለ ቦታ ሲሰጣቸው የነበረው እርዳታ ለመጨረሻ ጊዜ ካገኙ አንድ ወር እየተጠጋ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የከሰም ስኳር ፋብሪካ የተፈናቀሉ ሰራተኞቹን ወደ ፊንጫ፣ መተሐራ፣ ጣና በለስ እና ወደ ሌሎችም የስኳር ፋብሪካዎች እንደሚበተኑ መስማታቸውን የሚጠቅሱት አቶ ሱልጣን፤ ይህንን በመተው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን ብቻ በማስቀረት ለሌሎቹ “የስንብት ደብዳቤ በማስታወቂያ መለጠፉ” አሳዝኗቸዋል።

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የከሰም ስኳር ፋብሪካ የቦርድ አባል፤ ከስራ የተሰናበቱት ሰራተኞች “ጥቅማ ጥቅማቸውን ከወሰዱ በኋላ” የስራ ልምዳቸውን የያዘ ሰነድ (CV) ለሌሎች ፋብሪካዎች የመበተን እቅድ እንዳለ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የተሰናበቱት ሰራተኞች በሌሎች የስኳር ፋብሪካዎች “የመቀጠር እድል” አሁንም እንዳላቸው የቦርድ አባሉ ገልጸዋል። የከሰም ስኳር ፋብሪካ የስራ አመራር ቦርድ ሰራተኞቹ እንዲሰናበቱ የወሰነው፤ ከአንድ ወር በፊት የድርጅቱ የአስተዳደር አካላት ያቀረቡለትን ገለጻ ካደመጠ በኋላ መሆኑን እኚሁ የቦርድ አባል አመልክተዋል።

“እንደዚህ አይነት አደጋ በሚደርስበት ጊዜ፤ አሁን የተወሰደውን እርምጃ ከመውሰድ ውጭ ምንም አማራጭ የለውም። ማኔጅመንቱ ቢያንስ ከሁለት እስከ ሶስት አመት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ መስራት እንደማይችሉ ገልጿል። ይሄ ከሆነ ደግሞ ያለ ስራ እና ያለገቢ ለሰራተኛ ደመወዝ ከየትም መጥቶ አይከፍልም። ገቢ መኖር አለበት። የተኬደበት መንገድ ያ ነው” ሲሉ የቦርድ አባሉ ውሳኔውን አብራርተዋል። 

የከሰም ስኳር ፋብሪካ የሰው ሀብት ስራ አመራር እና አቅርቦት ዘርፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ዝናቡ ብርሃኑ፤ ፋብሪካው ሁሉንም ሰራተኞቹን እንደሚያሰናብት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ማረጋገጫ ሰጥተዋል። ፋብሪካው የሰራተኞቹን ውል በአገልግሎታቸው ጊዜ በመከፋፈል፤ በመጪዎቹ መጋቢት፣ ሚያዝያ እና ግንቦት ወራት ለማቋረጥ ማቀዱንም አክለዋል።

አሁን በስራ ላይ የቀሩት “ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጡ፣ የሰው ሀብት እና የፋይናንስ ንብረት የሚረከቡ የግምጃ ቤት ሰራተኞች” መሆናቸውንም  አቶ ዝናቡ ጠቁመዋል። “አሁን ስማቸው የተለጠፈውን አገልግሎታቸውን ከሰሩ፣ ከሸኙ እና ከጨረሱ በኋላ ለእነኚህም ይሰራ እና አገልግሎታቸው ተከፍሎ ይወጣሉ። መንግስት ውጡ ባለበት ቀን” ሲሉ በቀጣይ ወራት በፋብሪካው የሚቀር ሰራተኛ እንደማይኖር አቶ ዝናቡ አስረድተዋል።

የከሰም ስኳር ፋብሪካ ሰራተኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ጌታሁን አርሲጮ፤ የሰራተኞቹ ደመውዝ የቅድመ ማስጠንቅቂያ ጊዜያቸውን እንደሚከፈላቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ፋብሪካው ሰራተኞችን ከማሰናበቱ አስቀድሞ ሌሎች አማራጮች መታየት ይችላል የሚል አቋም ማህበሩ እንዳለውም ገልጸዋል። 

የፋብሪካውን ሰራተኞች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስር ወዳሉ የስኳር ፋብሪካዎች እና ወደ ሌሎች የልማት ድርጅቶች አዘዋውሮ ማሰራት ይቻል ነበር የሚሉት አቶ አቶ ጌታሁን፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተደረገው ነገር ትክክል አይደለም ባይ ናቸው። የሰራተኛ ማህበሩ ለኢትዮጵያ ሰራተኞች ኮንፌደሬሽን ደብዳቤ መጻፉን ያመለከቱት ሊቀመንበሩ፤ ኮንፌደሬሽኑ በሚጽፈው ደብዳቤ መሰረት ማህበሩ ጥረቱን እስከ መጨረሻው እንደሚቀጥልም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)