ሙሉ ንግግር፦ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ያደረጉት የመክፈቻ ንግግር

የተከበሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ። የተከበሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ። የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት። ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች። ክቡራትና ክቡራን! 

የኢፌዲሪ ህገ መንግስት በሚደነግገው መሰረት፤ የሁለቱ ምክር ቤቶች የስራ ዘመን መጀመርን በይፋ ለማብሰር በሚከናወነው የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝቼ ንግግር ለማድረግ በመቻሌ ከፍ ያለ ደስታ ይሰማኛል። 

በአዲሱ አመት መባቻ፤ የበርካታ አመታት ቁጭታችን እና የጥረታችን ውጤት የሆነውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ያስመረቅንበት፣ በወርሃ መስከረም መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ሀብት የብስራት ጅማሮ የሆነውን የተፈጥሮ ጋዝ ያወጣንበት እና የተፈጥሮ ሀብታችን በመጠቀም የእድገታችንን መልህቅ የሆኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የጀመርንበት በመሆኑ፤ ይህ ዘመን በታሪካችን ውስጥ በጉልህ የሚወሳ አዲስ ምዕራፍ ሊሆን እንደሚችል አልጠራጠርም። 

ክቡራት እና ክቡራን! 

መንግስት ለዓመታት ሲያጠናና ሲዘጋጅበት ቆይቶ ተግባራዊ ባደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሁም ቀደም ሲል በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ ተይዘው በተከታታይ ዓመታት ተግባራዊ ሲደረጉ በቆዩ ፕሮግራሞች፤ ኢኮኖሚያችን በማንሰራራት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለዘመናት በመዋቅራዊ ተግዳሮቶች ተፅእኖ ስር ወድቆ በከፍተኛ የእዳ ጫና ውስጥ ይገኝ ነበር። ከለውጡ በፊት ይመዘገብ የነበረው እድገትም በዘላቂ የፋይናንስ መሰረት ላይ ያልተዋቀረ፣ ሀገርን ለከፍተኛ ዕዳ የዳረገ እና የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችን የፈጠረ ነበር። መንግስት እነዚህን የኢኮኖሚ መዛባቶች የሚያርሙና ወደ ብልፅግና ጎዳና የሚያደርሱ ፈጣን እና መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻዎች ተግባራዊ አድርጓል። 

የመንግስት ገቢ፣ የወጪ ንግድ ወይም ኤክስፖርት እንዲሁም የውጪ ምንዛሬ ክምችት ለማሳደግ ተችሏል። የልማት አቅጣጫችንም ትኩረትም ውሱን ከሆኑ ዘርፎች ወደ ባለ ብዙ ዘርፍ ኢኮኖሚ መሰረቶች በመቀየር ላይ ይገኛል። መንግስት ኢኮኖሚውን ከእዳ ጥገኝነት በማላቀቅ ወደ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት ለማሸጋገር የሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ ከፍቷል። 

የኢኮኖሚ ለውጡ መሰረቶችም ያሉንን አቅሞች ማወቅ፣ በችግር ውስጥ እድልን ማየት፣ በፈጠራ እና በፍጥነት፣ በትብብርና የተለያዩ አቅሞችን በማሰባሰብ እንዲሁም ዘላቂ ግቦችን በማሳካት ላይ ያተኮሩ ናቸው። እነዚህ መሰረቶች አጠቃላይ አገራዊ እድገትን ለማፋጠን አስችለዋል። 

በዚህም ከእዳ ጫና በመላቀቅ በራስ አቅም ችግሮችን በመፍታት ከአግላይ የኢኮኖሚ ስርዓት ወደ አሳታፊ እና ምቹ የኢኮኖሚ ምህዳር በመሸጋገር፣ ከዝናብ ጥገኝነት ወደ ራስ ቻይ አምራችነት በመብቃት፣ የማዕድን ጥሪታችንን ወደ ወሳኝ የሃብት ምንጭነት በመቀየር፣ የቱሪዝም ሃብታችንን ከመዳህ ጉዞ ወደ ጉልህ የእድገት አንቀሳቃሽነት በማሳደግ፣ የህዝባችንን አኗኗር ለመለወጥ እና ዘላቂ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። 

በዚህ መሰረት የሀገራችን ኢኮኖሚ በ2017 በጀት ዓመት 8.8 በመቶ እድገት አስመዝግቧል። በግብርና በ2016 በጀት ዓመት 1.2 ቢሊዮን ኩንታል ምርት ተመርቶ የነበረ ሲሆን በ2017 ምርት ዘመን 1.57 ቢልዮን ኩንታል ምርት ተመርቷል። ይህም ከቀደመው ዓመት 24.7 በመቶ ብልጫ አለው። የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ59 በመቶ ወደ 65 በመቶ አድጓል። የወርቅ ምርት በ2016 በጀት ዓመት ከነበረበት 3.9 ቶን በ2017 በጀት ዓመት ወደ 38.87 ቶን አድጓል። የሲሚንቶ ምርት በ2016 በጀት ዓመት 7.5 ሚሊዮን ቶን በ2017 በጀት አመት ደግሞ ወደ 9.1 ሚሊዮን ቶን ከፍ ብሏል። 

ከ150 በላይ የዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች በአገራችን ተካሂደዋል። የዲጂታል ኢኮኖሚ አመላካቾች በከፍተኛ ሁኔታ እድገት አሳይተዋል። የባንክ ብድር 822.8 ቢሊዮን ተለቋል። ከዚህ ውስጥ 3/4ኛው ወይም 77 በመቶ ለግሉ ዘርፍ የተሰጠ ብድር ነው። ከኤክስፖርት በ2017 በጀት ዓመት በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ 8.3 ቢሊዮን ዶላር ከወጪ ንግድ ተገኝቷል። ይህም ከአምናው በ116 በመቶ ብልጫ አሳይቷል። 

የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በተደረገው ተከታታይ ጥረት የዋጋ ንረት በ2016 የሰኔ ወር 19.9 በመቶ ከነበረው በ2017 ተመሳሳይ ወር ላይ 13.9 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። ለመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ በማድረግ 4,760 የነበረውን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ወደ 6ሺህ ብር ማሳደግ ተችሏል። በ2017 በጀት ዓመት መንግስት ከብሔራዊ ባንክ ምንም ዓይነት የቀጥታ ብድር ሳይወስድ የበጀት ዓመቱን ለማጠናቀቅ ችሏል። ይህም ታላቅ ቁም ነገር ነው።

ክቡራት እና ክቡራን! 

ባሳለፍነው ዓመት በማህበራዊ ዘርፍ በርካታ ውጤታማ ተግባራት ተመዝግበዋል። በትውልዶች ውስጥ የሚስተዋለው የእሴት መሸርሸር ዋነኛ መነሻው የትምህርት ጥራት ችግር እንደሆነ መንግስት ያምናል። ይህንን ሳንካ ለመቅረፍ ባለፈው ዓመት በትምህርት ጥራት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል። መንግስት የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ቀርጾ ተግባራዊ አድርጓል። 

“ትምህርት ለትውልድ” በሚል መሪ ቃል ማህበረሰቡን በማንቀሳቀስ የትምህርት ተደራሽነትን የማረጋገጥ ስራ ተሰርቷል። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ተማሪዎች፤ በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ከትምህርት ገበታ እንዳይቀሩ አድርጓል። ይህ ጉልህ ተግባር በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር እውቅና የተሰጠው ነው።

መንግስት በጤናው ዘርፍ ባለፉት አመታት የተመዘገቡትን ስኬቶች መነሻ በማድረግ፤ ክፍተቶቹን የመሙላት ስራ ሰርቷል። በሽታን ከመከላከል ባለፈ አክሞ በማዳን ላይ ልዩ ትኩረት አድርጓል። መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የህክምና መሳሪያዎች እና መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል። 

መንግስት በሚያከናውናቸው ተግባራት ሁሉ ዋና መገለጫው አካታችነት ነው። ህፃናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን እንዲሁም የሀገር ባለውለታዎችን ታሳቢ በመደረጉ ተሳትፏቸው እና ሁለንተናዊ አቅማቸውን ለማሳደግ ጥረት ተደርጓል። ሴቶች እና ወጣቶችን ወደ አመራርነት በማምጣት ውሳኔ ሰጪነታቸው እንዲጨምር ተደርጓል። ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን “በነገዋ የሴቶች ማገገሚያ እና የክህሎት ማዕከል” በማሰልጠን ተሳትፏቸው እንዲጨምር ተደርጓል።

የወጣቶችን ክህሎት በማጎልበት የሀገር ውስጥ እና የውጪ ስራ እድሎች ተጠቃሚ ለማድረግ ተችሏል። የወጣቶችን አእምሮአዊ እና አካላዊ እድገትን ለማዳበር የሚያስችሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ማእከላት በብዛት ተገንብተዋል። ለአካል ጉዳተኞች ከተሰጡት በርካታ ድጋፎች መካከል ዘመናዊ የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉ አንደኛው አብነት ነው። መንግስት ለመጪው ትውልድ ሰፊ ትኩረት የሚሰጥ ሲሆን በተለይም በህጻናት እድገት እና ትምህርት ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል። 

ክቡራት እና ክቡራን! 

የውጭ ግንኙነታችን ማዕከል እና መሰረታዊ ማጠንጠኛው ብሔራዊ ጥቅም እና የዜጎች ክብር ነው። በዚህ መነሻነትም የኢትዮጵያ የጂኦ ስትራቴጃዊ ቁመና በመደርጀት ላይ ይገኛል። ይህ ስትራቴጂካዊ ምርጫ ከታዛቢነት ወደ አጀንዳ ተላሚነት እና ተፅእኖ ፈጣሪነት ለማሸጋገር አስችሏል። 

ሀገራችን በድንበር ተሻጋሪ ሀብቶቿ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ስትቀበል፤ በዛው ልኬታም አስተማማኝ የባህር በር የማግኘት መብቷን ማረጋገጥ ይኖርባታል። የኢትዮጵያ ህልውና መሰረት በሆኑት በሁለቱም ታላላቅ የውሃ ሃብቶች ዙሪያ መንግስት ያልተቆራረጠ ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል። እስካሁን በተደረጉ ጥረቶች 3 ጉልህ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል። 

አንደኛው፦ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አጋጥሞት የነበሩትን ፈተናዎች በጥበብ በማለፍ፣ ማጠናቀቅ እና በደመቀ ስነ ስርዓት ማስመረቅ ችለናል። ሁለተኛው፦ አስተማማኝ እና ዘላቂነት ያለው የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ከፍ ወዳለ ደረጃ የተሸጋገረ ሲሆን ይህ ፍትሃዊ ጥያቄአችንም በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ እያደገ የመጣ ቅቡልነት ማግኘት ችሏል። 

ሶስተኛው፦ በውጭ ሀገር ለእንግልት እና ለችግር የተጋለጡ ዜጎች በክብር ወደ ሀገር የተመለሱ ሲሆን ለወደፊትም ይሄው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው የልማት ግንባታ ይሳተፉ ዘንድ ጥረቶች ተደርገዋል። 

ውድ ኢትዮጵያውያን!

ኢትዮጵያ ሀገራችን ቁልፍ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። ዛሬ የምናከናውናቸው ተግባራት የሀገራችንን የቀጣይ ዘመን  ዕጣ ፋንታ ይወስናሉ። አሁን ያለንበትን ጊዜ በተገቢው ልኬታ እና ወቅቱ በሚጠይቀው ብልሃት መጠቀም መቻላችን፤ መጻኢው ዘመናችን አስተማማኝ እና በታሪክ የሚዘክር እንደሚያደርገው እሙን ነው። መንግስት ይህንን ሲል በሁለት አበይት ምክንያቶች ነው። 

አንደኛው፦ ሀገራችን አጋጥሟት የነበረውን የህልውና አደጋ እና በርካታ ፈተናዎችን ተሻግራ፤ ‘ጠንካራ ሀገራዊ አቅም ገንብታለች’ ብሎ ስለሚያምን ነው። ይህ አዲስ አቅም ኢኮኖሚያችንን እና የፖለቲካ ባህላችንን እየቀየረ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ዋና አብነቶቹም፤ አለመግባባቶችም በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ልምምድ መጀመራችን፣ ለሀገራዊ መግባባት መደላደል የሚሆን የምክክር መድረክ መፍጠራችን፣ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቃችን፣ የአረንጓዴ አሻራ ትልማችን ማስፋፋታችን እንዲሁም ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን መተግበራችን በጉልህ የሚጠቀሱ ናቸው። 

ከዚህ ጎን ለጎን የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት የማውጣት እና የመጠቀም ስራ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ትግበራ መግባቱ እና ሁለተኛው ምዕራፍ የተፈጥሮ ጋዝ ልማት መጀመሩ፣ ሀገራችንን ከማዳበሪያ ግዢ ጥገኝነት በማላቀቅ ለጎረቤት ሀገራት የሚተርፍ ግዙፍ የማዳበሪያ ማምረቻ ተቋሙ ግንባታ መጀመሩ፣ 1 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ከጋዝ የማመንጨት እና የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ የመገንባት ፕሮጀክቶች መጀመራችን በጉልህ የሚጠቀሱ ሲሆኑ፤ እነዚህን እና መሰል ታላላቅ ስራዎችን አጠናክረን ተግባራዊ ስናደርጋቸው የሀገራችን እድገት እና ብልፅግና የሚታይ የሚዳሰስ እውነታ መሆኑ አይቀሬ ነው። 

ሁለተኛው ‘ሀገራችን ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች’ የምንልበት ምክንያት፤ ዓለም ባልለየለት ቁልፍ ሽግግር ውስጥ በመገኘቱ ነው። ሽግግሩ እድልም፣ ፈተናም ያለው ሲሆን ከሽግግሩ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችልን አቅም በመፍጠር ላይ እንገኛለን። ባለፉት ዓመታት ከዓለም ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ራእይ እና ዓላማ ሰንቀን በመንቀሳቀሳችን፤ ሊደርስብን የሚችለውን ጫና ተቋቁመን ሀገራዊ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ ጥረት አድርገናል። 

ይህንን ዕድል በአግባቡ ከተጠቀምንበት በአለም አቀፍ የጂኦ ፖለቲካ እና የጂኦ ኢኮኖሚ ሽግግር ውስጥ ብሩህ ተስፋን የምታሳይ እና አርአያ የምትሆን ሀገር ለመገንባት እንችላለን። ይህንኑ ለመከወን የሚያስችሉ ፅኑ አቋም፣ አቅም እና ልምምድም አዳብረናል። ‘ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች’ በማለት የሰነቅነውን ራዕይ ከዓለም ጋር ያለንን የእድገት አሰላለፍ የሰመረ እንዲሆን መንገድ ይጠርጋል። 

በመሆኑም የተጀመረውን የሀገራችንን የማንሰራራት ጉዞ በፅኑ የማንሰራራት ላይ እንዲገነባ መንግስት በ2018 የበጀት ዓመት በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ይሰራል። 

አንደኛ፦ ከስርዓት መለዋወጥ ጋር የማይናዱ ነጻ፣ ገለልተኛ እና ህዝባዊ ብሔራዊ ተቋማትን ለመፍጠር መንግስት ጽኑ መሠረት በመጣል ላይ ይገኛል። በያዝነው የበጀት ዓመትም አንድነታችን እና ሰላማችንን በማይናወጥ ደረጃ ላይ ለማድረስ፤ መንግሥት በተቋማት ግንባታ ላይ አበክሮ ይሰራል። ብሔራዊ የጸጥታ እና የደህንነት ተቋሞችን የስርዓት ለውጥን የሚሻገሩ እና የአገርን ቀጣይነት የሚያረጋግጡ ብርቱ ተቋማት እንዲሆኑ መንግስት በቁርጠኝነት ይተጋል።

ሁለተኛ፦ በየቦታው የሚታዩ ግጭቶችን በኃይል ማረቅ፣ ማስተካከል የሚቻል ቢሆንም፤ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው ግን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ መንግስት ፅኑ እምነት አለው። በዚህ እምነቱ የእርቅ እና የሰላም አማራጮችን በመከተል የሀገራችን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል። ምንም እንኳን በየጊዜው የሚስተዋሉ የኃይል እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም መንግስት ሙሉ ዝግጁነት እና ዘመናዊ አቅም ቢኖረውም፤ ‘የዛሬውን ግጭት በማሸነፍ ለነገው ትውልድ ቂምና ቁርሾ አናወርስም’ የሚልን መርህ በመከተል በዛሬ ብልሃት እና ትግስት ለነገ ዘላቂ ሰላም የሚበጅ አካሄድን መርጧል። 

ይህ እምነት አገራዊ መግባባትን ለመትከል፣ ዘላቂ እና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት ለመመሰረት ያለው ፋይዳ የላቀ ነው። ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት መላው ህዝባችን እንዲሁም ልሂቃን የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪዬን አቀርባለው። 

ሶስተኛ፦ ለህዝብ የቀረበ እና ለህግ የታመነ አስተዳደር ወደ ብልፅግና ለሚደረገው ጉዞ ወሳኝ ነው። ይህንንም እውን ለማድረግ፤ መንግስት የአስተዳደር ማዕቀፎችን በማሻሻል፣ የተቋማትን ቅንጅት በማጠናከር እንዲሁም ተመሳሳይ እና ተጓዳኝ ዘርፎችን በማሰባሰብ ውጤታማ እንዲሆኑ አድርጓል። መልካም አስተዳደር የዘመናዊ ፖለቲካ የማዕዘን ድንጋይ መሆኑንም ይገነዘባል። 

የህዝብ አገልግሎት ለማዘመን በ2025ቱ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትልም መሰረት አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በቀጣይም በ2030 ዲጂታል ስትራቴጂ ይህን ውጤት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ይሰራል። የመንግስት ተቋማት የብዙሃነት ማዕከል እንዲሆኑ ይደረጋል። 

ለህብረተሰቡ የቀረበና እንግልትን የሚቀንስ የአገልግሎት ስርዓት ለመዘርጋት የተጀመረው እና ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ዲጂታል ማዕከል ለመስጠት ያለመው ‘የመሶብ አገልግሎት’ ተጠናክሮ፣ ተስፋፍቶ ይቀጥላል። የመረጃ አሰባሰብ እና ትንተና አቅም በላቀ ቴክኖሎጂ በማዘመን፤ በመረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ አፈጻጸምን በማጎልበት፣ የመረጃ ሉዓላዊ አቅማችንን የምንገነባ ይሆናል። 

አራተኛ፦ መንግስት የዜጎችን ዋስትና የሚያስጠብቅ የፍትህ ስርዓት ለመዘርጋት በ2018 በጀት ዓመት በትጋት ይሰራል። እንደሚታወቀው መንግስት የህግ አስከባሪ እና ፍትህ ተቋማትን ለማሻሻል ሰፊ ርቀት ተጉዟል። የህግና የአሰራር ማነቆዎችን በመፍታት እና ተቋማቱን በነፃነት በማደራጀት፤ የአቅም ማጎልበቻ ስራዎችን አከናውኗል። የተሻሻሉት የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ህጎች በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ ተደርጓል። 

የፍርድ ቤት አገልግሎትን ለማዘመን የተጀመሩ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራዎችን በማስፋት፣ በማሟላት እና በማብቃት መርሆዎች መሰረት ተግባራዊ ይሆናሉ። ባህላዊ የፍትህ አማራጮችም በአሰራር ጎልብተው፤ በፍትህ ስርዓት ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የተጀመረው አሰራር ተጠናክሮ ይቀጥላል። 

ክቡራትና ክቡራን!

በያዝነው ዓመት ድህነት ከሚፈጥረው እንግልት በመውጣት ወደ አስተማማኝ የዕድገት ምዕራፍ ለመሸጋገር መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል። በ2018 በጀት ዓመት 9 በመቶ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት እድገትን ለማረጋገጥም ይተጋል። ለዚህ ዕቅድ ስኬታማነትም መንግሥት ምርትን በብዛት፣ በዓይነት፣ በጥራት ያሳድጋል።

ተወዳዳሪ የወጪ ንግድ ወይንም ኤክስፖርት እድገት፤ ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚያስችል ስልት ተግባራዊ ይደረጋል። ምርታማነትን የሚያሳድጉ አካሄዶችን፣ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን የሚጨምሩ ስትራቴጂዎችን፣ ሀገራዊ ቁጠባ እና ኢንቨስትመንትን የሚያጎለብቱ ስልቶችን ተግባራዊ ለማድረግም ይሰራል።

ሀገራችንን ለዘመናት ከኖረችበት የተለቃችነት አበሳ ነጻ በማውጣት አንገቷን ቀና የምታደርግበት አቅምም ይገነባል። እንደሚታወቀው ግብርናችን በተፈጥሮ ላይ፣ መሰረታዊ ፍላጎቶቻችን ደግሞ በውጭ ምርቶች ላይ ጥገኛ በመሆናቸው፣ ለዓለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ተጋላጭ አድርጎናል። በመሆኑም መንግስት የኢኮኖሚ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እና ለተፈጥሮና ውጫዊ ጫናዎች የማይበገር ተገዳዳሪ እና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት ይተጋል።

መንግስት ባለፉት አመታት ጠንካራ የፊሲካል እና የገንዘብ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ በማድረግ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የዋጋ ግሽበት እንዲቀንስ ጉልህ ጥረት አድርጓል። በዚህ ዓመት ይህ ተጠናክሮ የዋጋ ግሽበቱ ወደ ነጠላ አሃዝ እንዲወርድ ይደረጋል።

ምርታማነትን በማሳደግ፣ አቅርቦትን በማሻሻል፣ የዋጋ ግሽበትን ትንተና አቅምን በማዳበር፣ የግብይት ስርዓቱን በማዘመን እንዲሁም በከተማ ግብርና፣ በሌማት ትሩፋት፣ በስንዴ ልማት እና በኢንዱስትሪ የማምረት አቅም የተገኙ ውጤቶችን በማስጠበቅ የዜጎች የኑሮ ጫናን ለማቃለል ይሰራል። 

ከዚህ በተጨማሪም ዘላቂ፣ በቂ እና ጥራት ያለው የስራ ዕድልን መፍጠር የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር ይሆናል። በድጋፍ እና በሴፊቲኔት የሚኖሩ ዜጎች ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገሩ ይደረጋል። ከፍተኛ የስራ ዕድል የመፍጠር አቅም ያላቸው ዘርፎችን በመለየት እና በመደገፍ፤ በርከት ላሉ ዜጎች በሀገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ ሀገራትም ጭምር የስራ እድል ይፈጠራል። 

የግብርናው የልማት ዘርፍ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን መንግስት በእጅጉ ያምናል። በያዝነው አመትም ግብርናው ከባህላዊ የአመራረት ከፍ ብሎ በቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስ አቅርቦት እና በክህሎት ልማት እንዲደገፍ፤ ልዩ ትኩረትን በመስጠት የ6.8 በመቶ እድገት እንዲያስመዝግብ ይደረጋል። የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር የምግብ ሉዓላዊነታችንን የምናጸናበት ዘመንም ይሆናል። 

የመስኖ አቅማችንን በማጎልበት ግብርናችን የዝናብ ጥገኝነቱ እንዲቀንስ ይደረጋል። የግብርና ግብአቶች በሀገር ውስጥ ማምረት፣ በተለይም የተጀመረውን የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ማፋጠን፣ ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ይሆናሉ። ይህ ሀገራዊ የዘመናት መሻት እውን እንዲሆን በቅርቡ የመሰረት ድንጋይ መጣሉ ለኢትዮጵያ ታላቅ ብስራት ሲሆን ይህንኑ ራዕይ ወደሚታይ እና የሚጨበጥ የልማት ትልም ላሸጋገሩት፤ ምክር ቤቱን በማስፈቀድ ለጠቅላይ ሚኒስትር እና ለመንግስትዎ እና ለመስተዳደርዎ ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ። (ረጅም ጭብጨባ)

ክቡራት እና ክቡራን!

የኢንዱስትሪ ዘርፍ ማነቆዎችን በመፍታት፤ ፈጣንና ጥራት ያለው የኢንዱስትሪ ልማት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል። ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በኢንዱስትሪው ዘርፍ ጉልህ ተሳትፎ እንዲኖረው ይደረጋል። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ የኢንቨስትመንት፣ የምርት ማሳደግ፣ የገበያ ማፈላለግ እና የቴክኖሎጂ ድጋፎች በስፋት እንዲቀርቡ ይደረጋል። 

በያዝነው ዓመት ለዘርፉ እድገት ወሳኝ የሆኑት የሰለጠነ የሰው ኃይል እና እውቀት እንዲሁም ከፍተኛ ካፒታል ለሚጠይቁ አምራች ኢንዱስትሪዎች ትኩረት ይሰጣል። መንግስት ‘በኢትዮጵያ ታምርት’ ንቅናቄ አማካኝነት ከውጭ የሚገቡ የካፒታል እና ወሳኝ ሸቀጦችን በመተካት፤ በሀገራችን ውስጥ እንዲመረቱ ተፈላጊውን ድጋፍ ይሰጣል። 

የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በሙሉ አቅማቸው ወደ ምርት እንዲገቡ በማድረግ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ቁልፍ ሚና እንዲኖረው ይደረጋል። ለአምራች ዘርፍ በቂና ተቀባይነት ያለው ብድርና የስራ ውጤት ወረት ለማቅረብ ሰፋ ሥራዎች ይከናወናሉ።

የከተሞች ልማትን በተመለከተ መንግስት በኮሪደር ልማት እና በተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ በርካታ ስራዎችን አከናውኗል። በቀጣይነትም የከተማ ልማት ስራ የድህነት ቅነሳ ጥረትን የሚያግዝና የተሻለ ገቢን በሚፈጥር መልኩ የሚከናወን ይሆናል። የይዞታ ማረጋገጫ ስርዓትን በማጎልበትና የመሬት አቅርቦትን በማሳደግ የመሬት ይዞታ መብት እንዲረጋገጥ በትኩረት ይሰራል። 

በመንግሥት፣ በግሉ ዘርፍ እንዲሁም በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ የጋራ ትብብር፤ የቤት አቅርቦት ችግር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቃለል ይደረጋል። በገጠሪቱ ኢትዮጵያም የመኖሪያ ቤቶች ደረጃ እንዲሻሻል የሚያስችሉ ስራዎች ይከናወናሉ። የንጹህ ውሃ፣ የመብራት፣ የመንገድ እና ትራንስፖርት ተደራሽነት የማሳደግ ስራ በትኩረት ይከናወናል። 

የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት በማሻሻል እና በቱሪዝም አገልግሎት ሀገራዊት ሀብት መፍጠር እንደሚቻል በማመን በመንግስት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ። እነዚህን ጥረቶች በማስፋት በያዝነው በጀት አመት ውብ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችሉ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ይስፋፋሉ። ነባሮቹ የቱሪዝም መስህቦችንም ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በማልማት ለጎብኚዎች ምቹ እንዲሆኑ ይደረጋል። የህብረተሰቡን ጥቅም የሚያስጠብቁ፣ የማህበረሰብ ቱሪዝም ፕሮጀክቶችን በመተግበር፣ የኗሪውን ወግና ታሪክ የሚያሳዩ የባህል ማዕከላትን አጣምሮ በመገንባት፣ በመዳረሻ ስፍራዎች ከአየር ትራንስፖርት ጋር በማስተሳሰር ለጎብኚዎች እና ለነዋሪዎች ጭምር ምቹ እንዲሆኑ ይደረጋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ ልማት እውን መሆን የቴክኖሎጂ ሽግግር ጉዳይ ብቻም ሳይሆን የሀገራችን የፖለቲካ ተራክቦት፣ ኢኮኖሚያችን እና ማህበራዊ ህይወታችንን ይቀይራል። የዲጂታል ቴክኖሎጂን በማስፋት፣ የመረጃ ልውውጥን በማቀላጠፍ እና አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ፤ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን በአጭር ጊዜ እውን ማድረግ እንደሚቻል መንግስት በጽኑ ያምናል። 

በ2018 በጀት ዓመት ዜጎች የዲጅታል መታወቂያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል አገልግሎቶች በዲጅታል ማዕቀፍ እንዲሰጡ እና እንዲሳለጡ ይደረጋል። የዲጂታል ዘርፍ ለሌሎች ዘርፎች አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር እንዲሆንም ይደረጋል። 

የማዕድን ዘርፍ አንዱ የኢኮኖሚያችን ምሶሶ ሆኖ ይቀጥል ዘንድ፤ የከርሰ ምድር ሀብታችንም ለህዝብ ጥቅም እንዲውል በትኩረት ይሰራል። በዘርፉ የተለመዱ ማዕድናት በጥራት እና በስፋት ወደ ገበያ እንዲቀርቡ ከማድረግ ባሻገር፤ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች ለገበያ እንዲቀርቡ የሚደረግ ሲሆን አዳዲስ የማዕድን ልማት ግንባታዎችን ክትትል በማጠናከር በኢኮኖሚያችን ላይ ከፍ ያለ ትሩፋት የሚጨምሩ ተግባራት በጥብቅ ክትትል የሚመሩ ይሆናል።

ክቡራት እና ክቡራን! 

መሰረተ ልማት በሀገራችን ሁለት ግቦች ያሉት ሲሆን አንደኛው ግቡ የኢኮኖሚ እድገትን ማፋጠን እና ማቀላጠፍ ማስቻሉ ነው። ሁለተኛው ግቡ ደግሞ የዜጎችን አኗኗር ለማሻሻል እና ለማዘመን ማገዙ ነው። ከዚህ አኳያ መንግስት በትራንስፖርት፣ በኢነርጂ፣ በመስኖ እና በውሃ ዘርፎች ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በበጀት አመቱም የተመጣጠነ የመሰረተ ልማት ስርጭትን ለማረጋገጥ መንግስት ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ቆርጦ ተነሳስቷል። 

በዚህ መሰረት በ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሀገር ውስጥ መንገድ አውታር ሽፋን ለማሳደግ ይሰራል። የአየር ትራንስፖርት መዳረሻዎችም ይስፋፋሉ። የባቡር ትራንስፖርት ሎጂስቲክ ዘርፍም ጉልህ ሚና እንዲኖረው ይደረጋል። የህዝቡን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ለማርካት፤ የታዳሽ ሃይል መሰረት ልማቶች በቀጣይ ዓመታት በበቂ ይገነባሉ። 

በሁሉም የሀገራችን ክፍል የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲስፋፋ እና ተደራሽ እንዲሆን ይደረጋል። ለኤክስፖርት ንግድ የሚበቃ የኤሌክትሪክ አቅርቦት በማሳደግ፤ ለቀጠናዊ የኢኮኖሚ ትስስር መሰረት ይጣላል። የቴሌኮሚኒኬሽን ሽፋን በማስፋት አገልግሎቱ ለመላው ማህበረሰባችን ተደራሽ እንዲሆን ይደረጋል። 

የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የመስኖ እና የፈሳሽ ልማት እንዲሁም የውሃ ኃይል ጥናትና ዲዛይን የመንግስት ዋነኛ ትኩረት መስኮች ይሆናሉ። በከተማ እና በገጠር የንጹህ ውሃ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማሻሻል ይሰራል። ማህበራዊ ትስስራችን ለማጠናከር ነባር እና አዳዲስ ማህበረሰባዊ ጸጋዎቻችንን በመትከል፣ የነበሩትንም ከፍ አድርጎ በማቆየት ለቀጣዩ ትውልድ እንዲሸጋገሩ መንግስት አበክሮ ይሰራል። 

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ፤ መንግስት ደረጃቸውን የጠበቁ ቅድመ መደበኛ እና መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታን ያስፋፋል። የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያስፈልጉ ክህሎት ያላችው እና ውጤታማ ባለሙያዎች በሚያፈሩ መልኩ ይቃኛሉ። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካዳሚክ ነጻነታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ፤ የአስተዳደር እና የሰው ኃይል ልማታቸው የተሻሻሉ እንዲሆን ይደረጋል።

በአርብቶ አደር አካባቢ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋፋት በልዩ ሁኔታ የተቀረጸ እቅድ የተነደፈ ሲሆን የቅድመ አንደኛ፣ አንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ እንዲሁም የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ እንዲሻሻል ይደረጋል። 

የጤና ተቋማትን ተደራሽነትና ጥራት በማሳደግ በተለይ የአገልግሎት ችግር ባለባቸው የአርብቶ አደር አካባቢዎች ልዩ ትኩረት ይሰጣል። በሰለጠኑ ባለሙያዎች የሚሰጠውን የወሊድ አገልግሎት በማሳደግ ሁሉም እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ እና ሁሉም ህጻናት እንዲከተቡ ይደረጋል። ወረርሽኞችን በብቃት ለመከላከል የሚያስችል ልዩ ስርዓትም ይዘረጋል።

የማህበራዊ ዋስትና መርሃችን፤ በራሳችን አቅም ለተቸገሩና ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች መድህን መሆን ነው። ተጋላጭ ዜጎችን በዘላቂነት በማቋቋም፣ ወደ አምራችነት በማሸጋገር የተረጂነት ባህል ለመቀነስም ይሰራል። ዓይነ ስውራንና አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መሰረተ ልማቶች እንዲስፋፉ ይደረጋል። 

ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት ለመግታት በጥናት ላይ የተመሰረቱ መፍትሔዎች ተግባራዊ ይሆናሉ። አረጋውያን የሚጦሩባቸው እና የሚደገፉባቸው ማእከላትን በማደራጀት ዘላቂ ድጋፍ እንዲያገኙም ይደረጋል። ወጣቶች እና ሴቶች በሀገራችን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት እንዲሳተፉና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዘመኑን የሚመጥን እውቀት ክህሎት እና ብቃት እንዲኖራቸው ይደረጋል። 

የህጻናትን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ሁኔታ ይሰራል። የህጻናት ትምህርት፣ ጤናማ እድገት እና የተመጣጠነ ምግብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት ይደረጋል። የመንግስት ፖሊሲዎች ወጣቶችን ማእከል ያደርጋሉ። በጥናት ላይ የተመሰረቱ የስራ እድሎችም ለከተማ እና ለገጠር ወጣቶች ተደራሽ ይሆናሉ። 

የተከበሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ የተከበሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት፣ ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች እና ክቡራትና ክቡራን!

ዓለማችን በተለዋዋጭ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች። አህጉራችን አፍሪካም ሆነ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከዚህ ኡደት ውጭ ሊሆኑ አይችሉም። በዚህ የዓለም ሁኔታ ውስጥ ሀገራዊ ሰላምን እና ደህንነትን ለማስጠበቅ፣ እድገትና ብልጽግናችን ለማረጋገጥ በዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ እና የሰላ ተጽዕኖ ማሳረፍ ይገባናል። 

በዚህ ረገድ አራት ጉዳዮች በቀዳሚነት ይከናወናሉ። የመጀመሪያው ዜጋን ማዕከል ያደረገ ብሔራዊ ደህንነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው። ብሔራዊ ደህንነት የሀገራችንን ዳር ድንበር ማስከበር ብቻ ሳይሆን፤ የዜጎችን ደህንነትና ክብርንም ማስጠበቅ ይጨምራል። በማናቸውም ቦታ የሚገኙ ዜጎቻችን ደህንነት እና ክብር የሀገራዊ ደህንነት ጉዳያችን ነው።

በመሆኑም ህገ ወጥ ፍልሰትን መቆጣጠር፣ ዜጎች በህጋዊ መንገድ መበታቸው ተጠብቆ እንዲንቀሳቀሱና የሥራ እድል ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ማድረግ፣ በሚኖሩበትና በሚሰሩባቸው አገራት መብታቸውን ማስከበር ዋና ትኩረት የሚሰጠው ተግባር ይሆናል። ባልተመቻቸ የስራ ሁኔታ ውስጥ የነበሩትን ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራም በቀጣይነትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

ሁለተኛው፦ ኢትዮጵያ በአባይ እና በቀይ ባህር መሀከል የምትገኝ አገር ነች። ዕጣ ፋንቷዋ እና መጻይ እድሏም ከሁለቱ ውኃዎች ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ፍትህን ባልተከተለ መንገድ እና ህዝብን ባላማከልና ባላሳተፈ አግባብ ተገልላ ቆይታለች። 

ኢትዮጵያ ወደ እነዚህ ውሃዎች እንድትመለስና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚ እንድትሆን መንግስት በመስራት ላይ ይገኛል። ከሶስት አስርት ዓመታት በኋላ የባህር በር ጉዳይ አለም አቀፍ የመነጋገርያ ሃሳብም ማድረግ ተችሏል። በቀጣይነትም የቀጠናችንን የጋራ የመልማት ፍላጎት ያገናዘበ ትብብር እና ትስስርን ለማጠናከር ዲፕሎማሲያዊ እና ሰላማዊ ጥረቶች ይደረጋሉ።

መንግስት ፍትሃዊ እና አስተማማኝ የባህር በር ለማግኘት ከቀጠናው አገራት ጋር በዲፕሎማሲያዊ እና በሰላማዊ መንገድ ይሰራል። በአባይ ወንዝም ላይ የጋራ መተባበር እና መተማመን እንዲዳብር፣ የአባይ ተፋሰስ ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን ያከናውናል፣ በንቃትም ይሳተፋል።

ሶስተኛው፦ መንግስት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው “ቅድሚያ ለጎረቤት” የሚለውን መርህ አጠናክሮ ይቀጥላል። ባለፉት ዓመታት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ዘርፈ ብዙ ትብብር ለማድረግ ጥረት ተደርጓል። ከጎረቤት ሀገር ጋር ግጭት እንዳይፈጠርና ችግሮችም በመልካም ጉርብትና መርህ እና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። ቀጠናዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ የመሰረት ልማት ስራዎችም ተከናውነዋል። 

በቀጣይነትም ኢኮኖሚያዊ ትብብርን የሚያጎልብቱ የመሰረት ልማት ዝርጋታ እና የንግድ ልውውጥ እንዲጠናከሩ ይደረጋል። በዚህ ረገድ መንግሥት የጀመራቸውን ትብብሮች አጠናክሮ ይቀጥላል። በአካባቢችንም ሰላምን ለማረጋገጥ አለመግባባቶችን በዲፕሎማሲ መንገድ ለመፍታት አበክሮ ይሰራል።

አራተኛው፦ መንግስት በዓለም አቀፍ የኃይል አሰላለፎች ውስጥ ሚዛኑን በመጠበቅ፤ ትብብርና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፈንና ለማስፋት ይተጋል። መንግስት በዓለም መድረኮች የኢትዮጵያ ተሳትፎና ተደማጭነት እንዲያድግ፣ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት፣ በዓለም ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ሀገራችን ጉልህ ሚና እንዲኖራት በትኩረት ይሰራል። ለዚህም አስፈላጊውን ተቋማዊ ጥንካሬ፣ ፖሊሲ እና አቅጣጫዎች ተግባራዊ ይደረጋሉ።

በመጨረሻም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈ፣ በላቀ ትጋት ፈርጀ ብዙና አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል። እነዚህ ውጤቶችም የሀገራችንን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ጂኦ ስትራቴጂያዊ ቁመና በማሻሻል፣ የቀደመው የታዛቢነት ታሪክ ማብቂያ፣ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መክፈቻ እና የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት ይሆናሉ። 

በቀጣይ ዓመታትም እነዚህን ስኬቶች በማጎልበት እና በማስፋት የኢትዮጵያ መነቃቃት እና እድገት ወደማይቀለበስበት ምዕራፍ እንዲሸጋገር፣ ሀገራችንን በአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት እንድትሆን መንግስት አበክሮ ይሰራል። 

በያዝነው ዓመት በሀገራችን የሚካሄደው ሰባተኛ ሀገራዊ ምርጫ፤ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ እና በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተዓማኒ ይሆን ዘንድ መንግሥት በኃላፊነት ይሰራል።

መላው የአገራችን ህዝብ ኢትዮጵያ ያቀደቻቸውና የጀመረቻቸውን ግዙፍ የለውጥ እርምጃዎች አበርትቶ እንዲደግፍ እና በትጋት እንዲሳተፍ ጥሪዬን እያቀረብኩ፤ የኢትዮጵያ ወዳጆች እና የብልፅግና አጋሮችም ከኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ጎን በመቆም የዚሁ ስኬት ሁነኛ አጋዥ እንዲሆኑ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። 

መልካም የተግባር እና የስኬት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ። ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራ እና ተከብራ ለዘላለም ትኑር። አመሰግናለሁ።

[በ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተጠናቀረ]