ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለሃብቶች በችግር ጊዜ “ወደ ዱባይ የሚሸሹ መሆን የለባቸውም” አሉ 

በኢትዮጵያ የሚሰሩ ባለሀብቶች በተግዳሮት ወቅት ከመንግስት እና ከህዝብ ጋር የሚቆሙ “ታማኞች” መሆን እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሳሰቡ። በደህናው ጊዜ “ሀብት የሚያካብቱ” ባለሃብቶች፤ በችግር ጊዜ “ወደ ዱባይ የሚሸሹ መሆን የለባቸውም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

አብይ ይህን ያሉት ትላንት ማክሰኞ መስከረም 27፤ 2018 ለታማኝ ግብር ከፋዮች ሽልማት በሰጡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ነው። በዚሁ መርሃ ግብር ላይ 700 ግብር ከፋዮች እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ፤ መንግስት ከታማኝ የግብር ከፋዮች ጋር “በጹሁፍ ያልሆነ ስምምነት” መፈጸም እንደሚፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናግረዋል። ስምምነቱ ከያዛቸው ሶስት ነጥቦች መካከል የመጀመሪያው “ለማህበራዊ ዓላማ” መስራት የሚለውን እንደሆነም አስረድተዋል።  

“የግሉ ሴክተር ከትርፍ በላይ ማህበራዊ ዓላማን ያነገበ ስራ የእያንዳንዱ ኩባንያ፣ የስራ ኃላፊዎች እና ባለቤቶች አንዱ ዋነኛ ተልዕኮ መሆን አለበት። ሰርቶ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ግብር የሚከፍል ሰው፤ ከትርፍ በላይ ለማህበራዊ ዓላማ ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

አብይ በሁለተኛነት ያነሱት ነጥብ፤ ባለሃብቶች በችግር ጊዜ ከመንግስት ጋር አብረው መቆም ያለባቸው መሆኑን ነው።   “በታማኝነት ልናገለግላችሁ ስለወሰንን በስኬትም፣ በተግዳሮትም ከመንግስት እና ከህዝብ ጋር የምትጋሩ ታማኞች መሆን አለባችሁ። በደህናው ዘመን የምትሰበስቡ እና ሀብት የምታካብቱ፤ በችግር ጊዜ ደግሞ ወደ ዱባይ የምትሸሹ መሆን የለባችሁም። በመከራውም ጊዜ፣ በስኬቱም ጊዜ በጋራ ጸንተን የምንቆም መሆን አለብን” ሲሉ አሳስበዋል። 

ባለሃብቶች “የሀገርን ጥቅም እና ትውልድን የሚያስቀድሙ መሆን አለባቸው” የሚለው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበ ሶስተኛ የስምምነት ነጥብ ነው። “ ‘የምንሰራው ለእኛ ብቻ ሳይሆን፣ ለትውልድ ጭምር ነው’ የሚለውን አምናችሁ፣ ከልብ ተቀብላችሁ፣ የምትተግብሩ መሆን ይጠበቅባችኋል። ያ ሲሆን ከሰፈሮቻችን ወጥተን ላቅ ያለ ስራ ለመስራት በእጅጉ ያግዘናል” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)