ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” መስራቾች አንዱ የሆነው ተስፋለም ወልደየስ፤ ዓለም አቀፉ የፕሬስ ኢንስቲትዩት (IPI) እና ዓለም አቀፍ ሚዲያ ሰፖርት (IMS) የተባሉ ሁለት ተቋማት በትብብር ለሚሰጡት የዓለም ፕሬስ ነጻነት ጀግና ሽልማት ተመረጠ። የእዚህን ዓመት ሽልማት እንዲቀበሉ የተመረጡት ተስፋለምን ጨምሮ ሰባት ጋዜጠኞች እና አርታዒያን ናቸው።
ዓለም አቀፉ ሽልማት ለሚዲያ ነጻነት ወይም ያልተገደበ የዜና እና የመረጃ ፍሰት በተለይ ግለሰባዊ ደህንነታቸው ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ሆኖ ጉልህ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ጋዜጠኞች የሚሰጥ ነው። ተስፋለም ለሽልማቱ የተመረጠው “ለገለልተኛ ጋዜጠኝነት ባለው የማይናወጥ ቁርጠኝነት” እንደሆነ ሸላሚዎቹ ዛሬ ሐሙስ መስከረም 29፤ 2018 ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ጋዜጠኛው “ከባለስልጣናት ለሚሰነዘር ቀጥተኛ የበቀል እርምጃ” ዒላማ ከመሆኑ ባሻገር በሥራው ምክንያት “የግል ሕይወቱን በተደጋጋሚ ለአደጋ እንዳጋለጠ” ሸላሚዎቹ በመግለጫቸው ጠቁመዋል። ከአንድ ዓመት በላይ የሚረዝመውን ጨምሮ ለተደጋጋሚ የዘፈቀደ እስራት የተዳረገው ተስፋለም፤ “ከጊዜ ወደ ጊዜ ለነጻ ሚዲያ አስቸጋሪ በሆነ ምህዳር ውስጥ ለሕዝብ ለሚጠቅም ጋዜጠኝነት ቦታ ለመፍጠር ባለው ቁርጠኝነት” ተሰድዶ ከነበረበት ሀገር ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን ተቋማቱ በመግለጫቸው አመልክተዋል።

ተስፋለም “ለዚህ ታላቅ ሽልማት በመመረጤ ታላቅ ክብር ይሰማኛል” በማለት ደስታውን ገልጿል። ሁለቱ ተቋማት እና ዓለም አቀፍ መራጭ ኮሚቴ “ለጥረቱ እውቅና በመስጠታቸው” ምስጋናውን አቅርቧል። የእዚህን ዓመት ተሸላሚዎች ከመረጡት ዓለም አቀፍ የዳኞች ኮሚቴ አባላት ውስጥ የፊንላንድ፣ የፓኪስታን እና ሜክሲኮ ጋዜጠኞች ይገኙበታል።
“ይህ ክብር ለእኔ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ እና በስደት ላይ ለሚገኙ ብርቱ ጋዜጠኞች ጭምር ነው” ያለው ተስፋለም፤ ሽልማቱ “በየዕለቱ በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር ለሚውሉ፣ ለሚታሰሩ፣ ማስፈራራት፣ ወከባ፣ ዛቻ ለሚገጥማቸው፣ ለሚከሰሱ እና ጥቃት ለሚፈጸምባቸው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ድፍረት እና ለሙያቸው ያላቸው ታማኝነት ምስክር” እንደሚሆን ገልጿል።
የኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች “የማይናወጥ ቁርጠኝነት እና ጥንካሬ” በሁለቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሽልማት ቦታ ማግኘቱን የገለጸው ተስፋለም፤ “ለሚያከናውኑት ጠቃሚ ሥራ እና ለሚፈታተኗቸው ተግዳሮቶች የበለጠ ትኩረት እንዲሰጥ ያደርጋል” የሚል ተስፋ አለው። ለሽልማቱ መመረጡ የጋዜጠኝነት ስራውን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እንዳነሳሳውም ገልጿል።

ለዘንድሮው ሽልማት ከተመረጡ ጋዜጠኞች መካከል ሁለቱ በስራቸው ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ ናቸው። በጋዛ የተገደለችው ፍልስጤማዊ የፎቶ ጋዜጠኛ ማርያም አቡ ዳጋ እና በሩሲያ እስር ቤት ሕይወቷን ያጣችው ዩክሬናዊት ጋዜጠኛ ቪክቶሪያ ራሺና፤ በህይወት በሌሉበት ሽልማቱ የሚበረክትላቸው ይሆናል።
ባለፈው ነሐሴ እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ በድሮን በፈጸመችው ጥቃት የተገደለችው ማርያም፤ ህይወቷ በተደጋጋሚ ለአደጋ እየተጋለጠ ባነሳቻቸው ፎቶግራፎች የጋዛን ሰቆቃ ለዓለም ማሳየት ችላለች። ሩሲያ በዩክሬን በፈጸመችው ወረራ የተፈጠረውን ነባራዊ ሁኔታ ትዘግብ የነበረችው ቪክቶሪያ፤ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው በመስከረም 2017 ዓ.ም. ነው።
ጆርጂያዊቷ ዚያ አማግሎቤሊ እና በሆንግ ኮንግ የጋዜጣ አሳታሚው ጂሚ ላይ በእስር ቤት የሚገኙ የሽልማቱ አሸናፊዎች ናቸው። የቀድሞው የዋሽንግተን ፖስት እና የቦስተን ግሎብ ጋዜጦች ስመ-ጥር አርታዒ ማርቲን ባሮን እና ፔሩቪያዊው ጉስታቮ ጎሪቲም የዘንድሮው ሽልማት ተመራጮች ናቸው።

የዓለም አቀፉ የፕሬስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ስኮት ግሪፌን፤ ሰባቱ ጋዜጠኞች “የፕሬስ ነጻነትን ለማስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ” መሆናቸውን ገልጸዋል። ተሸላሚዎቹ “በአምባገነንነት መስፋፋት እና ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ላይ አዳዲስ ፈተናዎች በተፈጠሩበት” እንዲሁም “ጋዜጠኞች በአሁኑ ወቅት እየገጠሟቸው በሚገኙ ስጋቶች” ወቅት ልምዶቻቸውን ለዓለም ማስተማር የሚችሉ አርአያዎች እንደሆኑ ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።
የዓለም አቀፉ ሚዲያ ሰፖርት ዋና ዳይሬክተር የስፐር ሆበርግ “የዘንድሮው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ጀግና ሽልማት ተሸላሚዎች እያንዳንዳቸው ስራቸውን በመስራታቸው ብቻ ከባድ አደጋዎች እና ዛቻዎች ገጥሟቸዋል” ብለዋል። ማርያም አቡ ዳጋ እና ቪክቶሪያ ራሺና ለስራቸው ህይወታቸውን ዋጋ እንደከፈሉ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ተሸላሚዎቹ “በታላቅ ድፍረት እና ጽናት ሙስናን፣ የጦር ወንጀሎችን፣ በተጋላጭ ቡድኖች ላይ የሚፈጸሙ ማሳደዶችን እና ሌሎች በርካታ በደሎችን እንዳጋለጡ” ጠቅሰዋል። “ባለስልጣኖች ሊደብቁት የሚፈልጉትን ለማጋለጥ በድፍረት ላሳዩት ቁርጠኝነት” የስፐር ሰባቱን ተሸላሚዎች አመስግነዋል።
የዘንድሮው ተመራጮች ሽልማታቸውን የሚቀበሉት ስመ-ጥር ጋዜጠኞች፣ አርታዒያን እና የመገናኛ ብዙኃን ሥራ አስፈጻሚዎች ዓለም አቀፍ ጥምረት የሆነው ዓለም አቀፉ የፕሬስ ኢንስቲትዩት (IPI) 75ኛ ዓመቱን በሚያከብርበት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ነው። ጉባኤው ከጥቅምት 13 እስከ 15፤ 2018 በኦስትሪያ ዋና ከተማ ቪዬና ይካሔዳል።
ዓለም አቀፉ የፕሬስ ኢንስቲትዩት (IPI) ባለፉት ዓመታት ከ75 በላይ የፕሬስ ነጻነት ጀግና ሽልማቶችን ሰጥቷል። ከጎርጎሮሳዊው 2015 ወዲህ ሽልማቱ የሚሰጠው መቀመጫውን በዴንማርክ ካደረገው ዓለም አቀፍ ሚዲያ ሰፖርት (IMS) ጋር በመተባበር ነው።

ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ የሽልማቱ አሸናፊ ሲሆን ተስፋለም ወልደየስ ሁለተኛው ነው። በዓለም አቀፉ የፕሬስ ኢንስቲትዩት የፕሬስ ነጻነት ጀግና ሆኖ የተመረጠው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ነበር።
እስክንድር በ2009 ዓ.ም. ለሽልማቱን ሲመረጥ የቀድሞውን የጸረ-ሽብር ሕግ በመተቸቱ ምክንያት በእስር ላይ ነበር። መስከረም 2004 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር የዋለው እስክንድር ለስድስት ዓመታት ገደማ በእስር ቤት አሳልፏል።
የዘንድሮው ተሸላሚ ተስፋለም ለመጀመሪያ ጊዜ ለእስር የተዳረገው በሚያዝያ 2006 ዓ.ም. ነበር። “ሽብርተኝነትን በመደገፍ” ከተከሰሱ ሶስት ጋዜጠኞች እና “ዞን 9” በመባል ከሚታወቁት ስድስት ጦማሪዎች ጋር የፍርድ ሂደቱን ሲከታተል ቆይቷል። ጋዜጠኛው ክሱ ተቋርጦ ከእስር የተለቀቀው አንድ ዓመት ከሶስት ወራት በወህኒ ቤት ከቆየ በኋላ ነበር።

ተስፋለም ከእስር ከተለቀቀ በኋላ ወደ ጀርመን በማምራት በጀርመን ድምጽ (Deutsche Welle) የአማርኛ አገልግሎት በሪፖርተርነት፣ የፕሮግራም አዘጋጅነት እና በአርታዒነት ለሶስት ዓመታት ገደማ ሰርቷል። ጋዜጠኛው ከሌላ የሙያ አጋሩ ጋር በመሆን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃንን ያቋቋመው ከጀርመን ወደ ሀገር ቤት ከተመለሰ በኋላ ነበር።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከመጋቢት 2012 ጀምሮ ዜናዎችን፣ በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ትንታኔዎችን እና የምርመራ ዘገባዎችን ስታቀርብ ቆይታለች። በድረ-ገጽ፣ በፌስቡክ፣ በዩቲዩብ፣ በቲክቶክ እና በቴሌግራም የሚሠራጩት ዘገባዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ እና የዓለም ክፍሎች በሚገኙ ተከታታዮች ዘንድ ተቀባይነት ቢያገኙም “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እና ባልደረቦቿ ሥራቸውን በነጻነት ለማከናወን ተደጋጋሚ ጫና ለመጋፈጥ ተገድደዋል።
ዋና አርታዒው ተስፋለም ወልደየስ በመስከረም 2014 ዓ.ም. ለሶስት ቀናት እንዲሁም በነሐሴ 2017 ዓ.ም. ደግሞ ለአምስት ቀናት በእስር አሳልፏል። “የኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ሌሎች ዘጋቢዎችም የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ዘገባዎች ለመስራት ባደረጓቸው ሙከራዎች ለሰዓታት በጸጥታ አስከባሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ነበር።

ከእስር በተጨማሪ ሐምሌ 9፤ 2015 “የኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢሮ እና በውስጡ የነበረ ካዝና ተሰብሮ ካሜራዎች፣ ሌንሶች፣ ላፕቶፖች እና ስማርት ስልክ ተዘርፈዋል። ዘረፋው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር”ን አቅም ለማጠናከር እና ዘገባዎቿን ለማስፋፋት የሚደረጉ ጥረቶችን የተገዳደረ ክስተት ነው።
ዓለም አቀፉ የፕሬስ ኢንስቲትዩት (IPI) እና ዓለም አቀፍ የሚዲያ ሰፖርት (IMS) ተስፋለም ወልደየስን ከ2025 አሸናፊዎች መካከል አንዱ አድርገው የመረጡት ለጥቂት ጊዜ ተደናቅፎ የቆየውን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የዕለት ተለት ሥራ በመደበኛነት ለማስቀጠል ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ነው።
ተስፋለም ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስቀድሞ ለሁለት አመት ስራ ወደ ኡጋንዳ በሄደበት ወቅት “ሀበሻዊ ቃና” የተሰኘ ጋዜጣ አቋቁሞ በምስራቅ አፍሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መረጃዎችን በማሰራጨት የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። ጋዜጠኛው ከጥቅምት 16፤ 2000 ዓ.ም እስከ ህዳር 19፤ 2002 በህትመት ላይ ቆይታ በመንግስት ጫና ከተዘጋችው ከ“አዲስ ነገር” ጋዜጣ ሰባት መሥራቾች መካከልም አንዱ ነበር።

ጋዜጠኝነትን በአዲስ አበባ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ይታተም በነበረው “ሰብ-ሰሐራን ኢንፎርመር” ጋዜጣ ላይ የጀመረው ተስፋለም፤ በሳምንታዊው “ፎርቹን” ጋዜጣ በልዩ ዘጋቢነት ለበርካታ ዓመታት ሰርቷል። በቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዜና አገልግሎት (IRIN) በወኪልነት የሰራው ተስፋለም፣ በ“አዲስ ስታንዳርድ” እና “ዋዜማ” የበይነ-መረብ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ በተባባሪ ዘጋቢነት ጽሁፎቹ ሲታተሙ ቆይተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)