የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልሎች ባሉ መንገዶች ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች፣ እገታዎች፣ የንብረት ዘረፋዎች እና ውድመቶች የሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነጻነት መብት “አደጋ ላይ መውደቁን” አስታወቀ። በእነዚሁ ክልሎች በሚጣሉ ኬላዎች፣ የመንገድ መዘጋት እርምጃዎች፣ የሰዓት እላፊ የእንቅስቃሴ ገደቦች እና በመንገዶች ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች የሚደርሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች “አሳሳቢ” ሆኖ እንዳገኘው ኢሰመኮ ገልጿል።
ኮሚሽኑ ይህን የገለጸው፤ “በግጭት ዐውድ” ውስጥ እና “ከግጭት ዐውድ ውጪ” ባሉ አካባቢዎች ያደረገውን የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ግኝት በተመለከተ ባወጣው ዛሬ ቅዳሜ ጥቅምት 1፤ 2018 ባወጣው መግለጫ ነው። ኢሰመኮ ክትትል እና ምርመራውን ያከናወነው ከሚያዝያ 2017 ዓ.ም. እስከ መስከረም 2018 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት መሆኑን አስታውቋል።
በአራት ክልሎች በተደረገው በዚህ ክትትል እና ምርመራ፤ በየአካባቢዎቹ የሚገኙ ነዋሪዎችን፣ የዓይን ምስክሮችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን እንዲሁም የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላትን በማነጋገር “መረጃ እና ማስረጃዎችን” ማሰባሰቡን ኮሚሽኑ አመልክቷል። ይህንን መሰረት በማድረግም ኮሚሽኑ “የመዘዋወር መብት አፈጻጸምን የሚሸረሽሩ” ናቸው ያላቸውን “አሳሳቢ” የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በመግለጫው ዘርዝሯል።

በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በጋምቤላ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሚጣሉ የሰዓት እላፊ የእንቅስቃሴ ገደቦች፣ በየአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች እና በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች “በመንገዶች ላይ በሚጣሉ ኬላዎች”፣ የመንገድ መዝጋት ትዕዛዞች፤ የሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነጻነት መብት “አደጋ ላይ መውደቁን” ኢሰመኮ በመግለጫው ላይ አስፍሯል።
በእነዚሁ ክልሎች ባሉ በመንገዶች ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች፣ እገታዎች፣ የንብረት ዘረፋዎች እና ውድመቶችም በዜጎች በነጻነት የመዘዋወር መብት ላይ ተመሳሳይ አደጋ መፍጠራቸውን ኮሚሽኑ አስገንዝቧል። እርምጃዎቹ እና ጥቃቶቹ ከመዘዋወር ነጻነት መብቶች ባሻገር፤ በህይወት የመኖር፣ የአካል እና የንብረት ደህንነት መብቶች ላይ “ጥሰቶችን ማስከተላቸውን” ማረጋገጡን ብሔራዊው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም በዛሬው መግለጫው አስታውቋል።
“በእነዚህ ድርጊቶች ተጎጂ በሆኑ ሰዎች ላይ በቀጥታ ከሚደርሱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በተጨማሪ በቤተሰብ ላይ የሚደርሰውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት፣ የስነ ልቡና ጫና እንዲሁም በአጠቃላይ ማህበረሰብ በህግ ስርዓት ላይ ያለውን እምነት የመሸርሸር አደጋ ኢሰመኮ አሳሳቢ ሆኖ አግኝቶታል” ሲልም ኮሚሽኑ በመግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል።
“ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የመጡ የሰዎችን የመዘዋወር መብት አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራትን ለመከላከልና በአስቸኳይ እልባት ለመስጠት መንግስት በተደጋጋሚ ጥቃት፣ እገታ፣ የንብረት ዘረፋና እና ውድመት የሚፈጽምባችው መንገዶች ላይ በቂ የጸጥታ ኃይል ሊያሰማራ ይገባል”
– ብርሃኑ አዴሎ፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር
መንግስት በመንገዶች ላይ በታጠቁ ኃይሎች ለሚደርሱ ጥቃቶች፣ እገታዎች፣ የንብረት ዘረፋዎች እና ውድመቶች “ተገቢውን ትኩረት መስጠት” እንዳለበት ኢሰመኮ በመግለጫው ላይ አመልክቷል። መንግስት በእነዚህ ወንጀሎች የተሳተፉ ግለሰቦችን “በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ” እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ “ተገቢ የሆኑ እርምጃዎችን” ሊወስድ እንደሚገባም ኮሚሽኑ አሳስቧል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የመጡ የሰዎችን የመዘዋወር መብት አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራትን ለመከላከልና በአስቸኳይ እልባት ለመስጠት መንግስት በተደጋጋሚ ጥቃት፣ እገታ፣ የንብረት ዘረፋና እና ውድመት የሚፈጽምባችው መንገዶች ላይ በቂ የጸጥታ ኃይል ሊያሰማራ ይገባል” ማለታቸውንም መግለጫው ጠቅሷል።
“ማናቸውም ህግና ስርዓትን የማስከበር፣ የወንጀል መከላከል እና አጥፊዎችን ተጠያቂ የማድረግ እርምጃ ሙሉ በሙሉ ህግና ስርዓትን በተከተለ እና ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ ብቻ ሊመራ ይገባል” ያለው የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ተቋሙ፤ የክልል እና የፌዴራል አስተዳደር እና የጸጥታ አካላት ሊያረጋገጧቸው የሚገቡ ጉዳዮችንም ዘርዝሯል።

የጸጥታ አካላቱ፤ የእንቅስቃሴ ክልከላዎችን፣ ያለአግባብ የሚጣሉ ኬላዎችን፣ የእንቅስቃሴ ገደብ እርምጃዎችን “አስፈላጊና ተመጣጣኝ መሆናቸውን”፣ “ከመጠን በላይ እንቅስቃሴን የሚገድቡ፣ ከፍተኛ መስተጓጎልን የሚያስከትሉ እና የአስፈላጊ አገልግሎቶችን ተደራሽነት የሚያናጉ አለመሆናቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል” ብሏል ኢሰመኮ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)