“የሊዝ ህግ ተላልፈዋል” የተባሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሶስት ቀናት ውስጥ 45 ሺህ ብር ቅጣት እንዲከፍሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው 

በአዲስ አበባ ከተማ “የመኖሪያ ቤቶቻቸውን ለንግድ ስራ አውለዋል” የተባሉ ነዋሪዎች፤ በሶስት ቀናት ገደብ ውስጥ እስከ 45 ሺህ ብር ቅጣት እንዲከፍሉ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ነዋሪዎቹ የመኖሪያ ቤቶቻቸውን ለሌላ አገልግሎት ለማዋል የሚያስችላቸውን የሊዝ ውል ለውጥ ለማድረግ ከመቶ ሺህዎች እስከ ሚሊዮኖች ብር የሚቆጠር ክፍያ መጠየቃቸውንም ገልጸዋል።

በመዲናይቱ በሚገኙት በአቃቂ ቃሊቲ፣ በለሚ ኩራ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዎች፤ ባለፉት ቀናት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎች እንደደረሷቸው “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጣለች። በአንዳንዶቹ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የንግድ ቤቶች እና አገልግሎት መስጪያዎች ላይ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎች መለጠፋቸውንም የየአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።   

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ዓለም ባንክ አዲሱ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች፤ ከክፍለ ከተማ መምጣታቸውን የገለጹ ሰራተኞች ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤውን ሲሰጡ እንደነበር ገልጸዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ፤ ነዋሪዎቹ መሬት የወሰዱት ለመኖሪያ አገልግሎት ለመዋል እንደሆነ ይጠቅሳል። 

ሆኖም ነዋሪዎቹ “በገቡት የሊዝ ውል መሰረት ለተፈቀደላቸው አገልግሎት ብቻ እየተጠቀሙ አለመሆኑን” በመስክ ክትትል ማረጋገጥ መቻሉን ያትታል። ነዋሪዎቹ ማስጠንቀቂያው ከተሰጠበት አሊያም ከተለጠፈበት ቀን ጀምሮ ባሉት ሶስት የስራ ቀናት ውስጥ፤ ካርታቸውን፣ የሊዝ ውላቸውን፣ ለመጨረሻ ጊዜ የከፈሉበትን የሊዝ ክፍያ ደረሰኝ እንዲሁም የንግድ ፍቃዳቸውን በመያዝ ለክፍለ ከተማ እንዲያቀርቡም ቀነ ገደብ ያስቀምጣል። 

ይህን መሰል የሶስት ቀናት የማሳወቂያ ጊዜ፤ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ላሉ ነዋሪዎች መሰጠቱን አንድ የክፍለ ከተማው ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ሂደቱ “ቀጣይነት ያለው” እና “በከተማ አቀፍ ደረጃ በሌሎችም ክፍለ ከተሞች እየተተገበረ” ያለ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።

ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለነዋሪዎች የተሰጠው ደብዳቤ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለክፍለ ከተማው መሬት ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መረጃዎችን አቅርበው ማስተካከያ ወይም የአገልግሎት ለውጥ ማድረግ እንዳለባቸው ያሳስባል። ይህን በማያደርጉ ነዋሪዎች፤ አሁን በስራ ላይ ባለው የሊዝ አዋጅ እና ደንብ መሰረት እርምጃ እንደሚወሰድባቸውም ያስጠነቅቃል። 

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ነዋሪ፤ የመኖሪያ ቤታቸው አካል የሆነውን ቤት ለንግድ በማዋላቸው በሶስት ቀናት ውስጥ 45 ሺህ ብር ቅጣት እንዲከፍሉ ቀነ ገደብ እንደተሰጣቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ነዋሪው የቅጣት መጠኑ የተገለጻላቸው፤ ከመኖሪያ ቤትነት ወደ ንግድ ለሚደረገው “የአገልግሎት ለውጥ” የተጠየቁትን በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዝብ ለመክፈል “አቅማቸው የማይችል” መሆኑን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ከተቀበሉ በኋላ እንደሆነ አስረድተዋል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይህ ደብዳቤ “አገልግሎት ለውጥ ማድረግ የማንፈልግ በመሆኑ ቅጣት በመክፈል ንግድ ለማቆም ተሰማምተናል” ይላል። ደብዳቤው የተዘጋጀው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር፣ በመሬት ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት፣ የወሰን ማስከበር፣ መሬት ባንክና ማስተላለፍ ዳይሬክቶሬት መሆኑም በግልጽ ተመልክቷል። 

በዚሁ ደብዳቤ ላይ ነዋሪው ለመኖሪያ የተፈደቀላቸውን ካርታ (የይዞታ ማረጋገጫ) “ለንግድ እየተጠቀሙበት” እንደሆነ የሚገልጽ ዐረፍተ ነገር ተካትቷል። ነዋሪው “ያለ ፍቃድ” የሰሩበትን ቅጣት ከፍለው “በተፈቀደላቸው አገልግሎት ብቻ የሚገለገሉ መሆኑን” በፊርማቸው እንዲያረጋግጡም ደብዳቤው ያስገድዳል። 

ተመሳሳይ ደብዳቤ ባለፈው ሐሙስ የተቀበሉ ሌላ የአካባቢው ነዋሪ፤ “አገልግሎት ለመለወጥ” የተጠየቁት 4.5 ሚሊዮን ብር ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ይገልጻሉ። በመኖሪያ ቤታቸው ካሬ ሜትር ልክ የተሰላው የገንዝብ መጠን፤ በአካባቢያቸው በቅርቡ ከተካሄደ የሊዝ ጨረታ ዋጋ በላይ መሆኑንም ያስረዳሉ። 

“በሊዝ ጨረታ አዲስ ቦታ ልግዛ ብትል እንኳ በካሬ ሜትር ይህን ያህል አይጠየቀበትም” የሚሉት ነዋሪው፤ ለአገልግሎት ለውጥም ሆነ ለቅጣት የተጠየቀው ቅጣት የነዋሪዎችን አቅም ያገናዘበ እንዳልሆነ ያብራራሉ። “ብዙ ቤተሰብ ታስተዳድራለህ፣ ግብር ተከፍላለህ፣ አራት አምስት ሰራተኛ አለህ፣ በሶስት ቀን መጥተህ [ክፈል ማለት] ይሄ በጣም ለመግለጽ የሚቸግር ሁኔታ ነው” ሲሉ ነዋሪው ስሜታቸውን አጋርተዋል።

የተሰጣቸው ቀነ ገደብ የደረሰባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በሰሚ ሰሚ የሰሙትን መረጃ ይዘው፤ የንግድ ቤቶቻቸውን ማፍረስ መጀመራቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ያልተረጋገጠው መረጃ “እያንዳንዱ ነዋሪ የይዞታውን 30 በመቶ ለንግድ አገልግሎት መዋል ይችላል” የሚል እንደሆነ የሚገልጹት ነዋሪዎቹ፤ የንግድ ቤታቸውን በዚሁ መልኩ ለማስተካከል እየሞከሩ እንደሆነ አስረድተዋል።

“ብዙ ቤተሰብ ታስተዳድራለህ፣ ግብር ተከፍላለህ፣ አራት አምስት ሰራተኛ አለህ፣ በሶስት ቀን መጥተህ [ክፈል ማለት] ይሄ በጣም ለመግለጽ የሚቸግር ሁኔታ ነው”

– የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ነዋሪ

የነዋሪዎችን አቤቱታ እና ቅሬታ በተመለከተ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዎች ምላሽ እና ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ትላንት እና ዛሬ ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም። ኃላፊዎቹ በሞባይል ስልኮቻቸው ላይ ለተላኩላቸው አጭር የጹሁፍ መልዕክቶችም ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)