በትግራይ ክልል ዛሬ ቅዳሜ ጥቅምት 1፤ 2018 ምሽት፤ ለሁለት ጊዜያት የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት ገለጸ። ከምሽቱ 1፡01 ላይ የደረሰው ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል 5.3 መለካቱን የገለጸው መስሪያ ቤቱ፤ ከ17 ደቂቃ በኋላ የተከሰተው በሬክተር ስኬል 5.3 መድረሱን አስታውቋል።
ከእነዚህ ክስተቶች አራት ሰዓት አስቀድሞ፤ በሬክተር ስኬል 4.2 የተላከ ሌላ የመሬት መንቀጥቀጥ ከመቐለ ከተማ በሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ 47 ኪሎ ሜትር ርቀት ባለ ቦታ ላይ መድረሱን መስሪያ ቤቱ መዝግቧል። ዛሬ ምሽት ከደረሱት ርዕደ መሬቶች የመጀመሪያው የተመዘገበው ከመቐለ ከተማ 58 ኪሎ ሜትር ርቀት ባለ ቦታ ላይ መሆኑንም ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሁለተኛው የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተው ከውቅሮ ከተማ 32 ኪሎ ሜትር በሚርቅ ቦታ ላይ እንደሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ ርዕደ መሬቶችን የሚመዘግበው “ቮልካኖ ዲስከቨሪ” በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል። ርዕደ መሬቱ ያስከተለው ንዝረት በሻጉባይ፣ በውቅሮ፣ ዶሎ፣ በዕዳጋ ሐሙስ እና በአዲግራት ከተሞች እንደተሰማ ድረ ገጹ ጠቁሟል።
የዛሬው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት፤ ክስተቱ ከተፈጠረበት 92 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የአረርቲ ከተማ ጭምር እንደደረሰ “ቮልካኖ ዲስከቨሪ” ገልጿል። በትግራይ ክልል ርዕደ መሬት ሲያጋጥም ካለፈው የካቲት ወር በኋላ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው።
ባለፈው ዓመት የካቲት ወር መጨረሻ ገደማ ከአዲግራት ከተማ 46 ኪሎ ሜትር በስተምስራቅ ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል። እኩለ ለሊት አቅራቢያ የተከሰተው ይኸው ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል 5.2 የተለካ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)