የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 4፤ 2018 ባካሄደው መደበኛ ስብስባ፤ የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽንን የሚያቋቁም ደንብ አጸደቀ። ደንቡ የጸደቀው ኢትዮጵያ እና ሩሲያ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ “ለማቀድ እና ለመገንባት” የሚያስችል ሰነድ በተፈራረሙ በሁለት ሳምንት ገደማ ልዩነት ነው።
ዛሬ በጸደቀው ደንብ መሰረት የሚቋቋመው ኮሚሽን፤ ኢትዮጵያ የኒውክሊየር ቴክኖሎጂን ከዓለም አቀፍ ማዕቀፎች በተጣጣመ መልኩ “ለሰላማዊ መንገድ” ለመጠቀም የምታደርገውን ጥረት “የመምራት እና የማስተባበር ኃላፊነት” እንደተጣለበት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል። ኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይልን ለኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት፣ ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለምግብ ዋስትና፣ ለጤና አገልግሎት፣ ለሳይንስ እና ምርምር ዘርፎች ለመጠቀም እንዳቀደች ጽህፈት ቤት ዛሬው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በ30 ቢሊዮን ዶላር ሊገነባ ካቀዳቸው “ሜጋ ፕሮጀክቶች” መካከል የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ አንዱ መሆኑን ከሳምንት በፊት ገልጾ ነበር። ይህንን የመንግስት ዕቅድ መስከረም 22፤ 2018 በተከናወነ ስነ ስርዓት ላይ ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶማሌ ክልል ለሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ የመሰረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት ባሰሙት ንግግር፤ የሜጋ ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ተጠንተው፣ ዝግጅት ተደርጎባቸው እንዲሁም የሀብት ምንጫቸው ተለይቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል። የፕሮጀክቱ ግንባታም “ካለምንም ጥርጥር በሚቀጥሉት አምስት እና ስድስት ዓመታት” እንደሚፈጸም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ ቃል ገብተዋል።
የፕሮጀክቱ አንድ አካል የሆነው የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ብቻ “ከአምስት እስከ ሰባት ቢሊዮን ዶላር” እንደሚፈጅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ተናግረው ነበር። የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫውን ለመገንባት፤ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ መስከረም 15፤ 2018 ዓ.ም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱ የተፈረመው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዓለም የአቶሚክ ፎረም ላይ ለመሳተፍ ወደ ሩሲያ አቅንተው ከፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ከተገናኙ በኋላ ነው። አብይ እና ፑቲን፤ በኢትዮጵያ ሊገነባ የታቀደው የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ተስፋዎች እና ቀጣይ እርምጃዎች ላይ መነጋገራቸውን የሩሲያ አቶሚክ ኢነርጂ ኮርፖሬሽን በወቅቱ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ይህን ውይይት ተከትሎ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ እና የሩሲያ አቶሚክ ኢነርጂ ኮርፖሬሽን (ROSATOM) ዋና ዳይሬክተር አሌክሲ ሊክሀቼቭ ስምምነት ተፈራርመዋል። የስምምነት ሰነዱ “በኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ለማሳደግ” ያለመ የድርጊት መርሃ ግብርን የያዘ መሆኑን የሩሲያ አቶሚክ ኢነርጂ ኮርፖሬሽን አስታውቋል።
የድርጊት መርሃ ግብሩ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ግንባታ ፕሮጀክቱን ዝርዝር ማብራሪያ፣ ወደ አዋጭነት ጥናት የሚመራ ፍኖተ ካርታ እና በሁለቱ መንግስታት መካከል የሚፈረም ስምምነት የማዘጋጀት ኃላፊነት የተጣለበት ልዩ የስራ ቡድን ያቋቁሟል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከፊርማ ስነ ስርዓቱ በኋላ በማህበራዊ የትስስር ገጾቻቸው በወቅቱ ባሰፈሩት መልዕክት፤ ስምምነቱ “ለማኅበረሰብ አገልግሎት የሚውል ንጹህ ኃይል ለማቅረብ የጋራ የኒኩሊየር ኃይል ማመንጫ ለማልማት” የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል።
በአፍሪካ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ያላት ብቸኛ ሀገር ደቡብ አፍሪካ ነች። የደቡብ አፍሪካው ኮበርግ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ፤ ወደ ሁለት ጊጋዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም እንዳለው የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ(IAEA) መረጃ ያሳያል። ግብጽ የራሷን የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ግንባታ በማከናወን ላይ የምትገኝ ሲሆን ጋና እና ኬንያ ተመሳሳይ ፕሮግራም ለመጀመር ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ላይ ይገኛሉ።

ይሁንና ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ፍላጎታቸውን ማሳየት ከጀመሩ በርከት ያሉ ዓመታት ተቆጥረዋል። ኢትዮጵያ ከስምንት ዓመታት ገደማ በፊት ከሩሲያ ጋር የኒውክሊየር ኃይልን ለሰላማዊ ግልጋሎት ለመጠቀም የሚያስችላት የመግባቢያ ስምምነት ማዕቀፍ ተፈራርማ ነበር።
ከሁለት ዓመታት በኋላ የኢኖቬሽን እና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በሩሲያ መካከል የአቶሚክ ኢነርጂ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን እና ለሕዝቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ ሌላ ስምምነት ተፈርሟል። ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ የኒውክሊየር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ለመገንባት የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት ለማከናወን ከሩሲያ አቶሚክ ኢነርጂ ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት የተፈራረመው በታህሳስ 2017 ዓ.ም ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]