በአፋር ክልል በመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ 43 ሺህ ገደማ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቀሉ  

በአፋር ክልል፣ ኪልበቲ ረሱ ዞን፣ በርሃሌ ወረዳ ትላንት ምሽት በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ 43,456 ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ሁሴን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ለተፈናቃዮቹ የሚሆን ምግብ እና መጠለያ፤ ከባድ ጉዳት ወደ ደረሰባቸው ቀበሌዎች እየተጓጓዘ መሆኑንም ገልጸዋል። 

በክልሉ ትላንት ቅዳሜ ጥቅምት 1፤ 2018 ምሽቱ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ከበርሃሌ በተጨማሪ በተመሳሳይ ዞን ውስጥ በሚገኙት ኮናባ እና ዳሎል ወረዳዎችም የተከሰተ እንደነበር የአፋር ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ዛሬ ከሰዓት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። በበርሃሌ ወረዳ የመጀመሪያው ርዕደ መሬት ከደረሰበት ከትላንት ምሽት 12 ሰዓት ጀምሮ ለስድስት ጊዜያት ያህል የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን አቶ አሊ አስረድተዋል። 

በወረዳው ካሉ ቀበሌዎች በርዕደ መሬቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው፤ ቡሬ እና አስ ጉቢ አላ ቀበሌዎች መሆናቸውን ዋናው አስተዳዳሪው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በአደጋው ሳቢያ በቀበሌዎቹ ነዋሪ የሆኑ ስድስት ሰዎች መጎዳታቸውን እንዲሁም አንድ የ12 ዓመት አዳጊ ልጅ ህይወት ማለፉንም ገልጸዋል።

ከተጎጂዎቹ ውስጥ ሶስቱ ወደ በርሃሌ ሪፈራል ሆስፒታል ተወስደው ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን አቶ አሊ አመልክተዋል። በሁለቱ ቀበሌዎች የቤቶች መፍረስን ያስከተለው ርዕደ መሬት በተከሰተበት ወቅት አብዛኞቹ ነዋሪዎች ከቤት ውጭ የነበሩ በመሆኑ የተጎጂዎች ቁጥር ሊቀንስ መቻሉንም አብራርተዋል።

በቡሬ እና አስ ጉቢ አላ ቀበሌዎች ያሉ በርካታ ቤቶችን ያፈረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ የደረሰው፤ ትላንት ምሽት 1:18 ደቂቃ ላይ ነበር። በሬክተር ስኬል 5.6 በተለካው በዚህ ርዕደ መሬት የፈረሱ ቤቶች ምን ያህል እንደሆኑ እስካሁን በትክክል አለመታወቁን ተናግረዋል።  

የአፋር ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ዛሬ ከሰዓት ባወጣው መግለጫ፤ በመሬት መንቀጥቀጡ “በርካታ የመኖሪያ ቤቶች እና የመንግስት መዋቅሮች ሙሉ በሙሉ በመፍረሳቸው ከፍተኛ የሆነ የንብረት ውድመት ደርሷል” ብሏል። የበርሃሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ በበኩላቸው በመኖሪያ ቤቶች እና በንብረት ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን ለማጣራት አንድ የጥናት ቡድን ወደ ቀበሌዎቹ መላኩን አስረድተዋል።

በሁለቱ ቀበሌዎች ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው እና የተፈናቀሉ ሰዎች ብዛት 43,456 መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጹት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ፤ ተፈናቃዮቹን ለመርዳት “ኮማንድ ፖስት” ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል። ተፈናቃዮቹ ወደ ሌላ ቦታ ሳይንቀሳቀሱ በዚያው በቀበሌያቸው ባሉ ቦታዎች ላይ እንዳሉም አክለዋል።  

“ወደ አካባቢዎቹ ድጋፍ የሚሆን ምግብ እና መጠለያ እየወሰድን ነው። ድጋፉ ለማስታገሻ ያህል ነው። ሰዎቹ በጣም ብዙ ናቸው” ያሉት አቶ አሊ ነዋሪዎቹ ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመል። ለአካባቢው ነዋሪዎች የሚሆን ድጋፍ ከአፋር ክልል መንግስት እየጠበቁ መሆኑንም አመልክተዋል።

“የአፋር ክልላዊ መንግስት የተከሰተውን ከባድ አደጋ ተከትሎ በአፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እና ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍ ሙሉ አቅሙን አሰባስቧል” ሲል የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በዛሬው መግለጫው አስታውቋል። ለተፈናቀሉ ዜጎች አስቸኳይ ምግብ፣ ጊዜያዊ መጠለያ እና አስፈላጊ የጤና አገልግሎቶች እንዲደርሱ የማድረግ ስራ “በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ” መሆኑንም ቢሮው ገልጿል። 

“ይህ አደጋ በተፈጥሯዊ የጂኦሎጂ አቀማመጥ ምክንያት በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ለሚያጋጥመው የክልሉ ክፍል አዲስ እና ከባድ ፈተና ሆኗል”

– የአፋር ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ

በአፋር ክልል በአዋሽ አካባቢ ባሉ ቦታዎች ባለፈው ዓመት ባጋጠሙ የመሬት መንቀጥቀጦች በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ይታወሳል። በበርሃሌ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ የደረሰው ከስድስት ወራት በፊት እንደነበር የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በትላንትናው ዕለት ያጋጠመው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ፤ “በተፈጥሯዊ የጂኦሎጂ አቀማመጥ ምክንያት በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ለሚያጋጥመው የክልሉ ክፍል አዲስ እና ከባድ ፈተና ሆኗል” ብሏል የአፋር ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በዛሬው መግለጫው። አደጋ የደረሰባቸውን የበርሃሌ ወረዳ ነዋሪዎች ወደ ሌሎች ቦታዎች ለማዘዋወር የተጀመረ እንቅስቃሴ እንዳለ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አሊ፤ ተፈናቃዮችን ሌላ ቦታ ለማስፈር ሙያዊ እገዛ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። 

በአካባቢው ተመሳሳይ አደጋ ቢያጋጥም፤ የአካባቢው ነዋሪዎቹ ሊያደርጓቸው ስለሚገቡ ጥንቃቄዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ለመስጠት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አክለዋል። ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ የሚሰራው ከሰመራ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር እንደሆነም ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)