ለሁለት ዓመት የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ (chief of staff) ሆነው ያገለገሉት አቶ ሳንዶካን ደበበ፤ በዛሬው ዕለት የማቋቋሚያ ደንቡ የጸደቀለትን የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽንን በኮሚሽነርነት እንዲመሩ ተሾሙ። አቶ ሳንዶካን ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት ሹመት ሲያገኙ በአምስት ዓመት ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አቶ ሳንዶካንን ከዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 4፤ 2018 ጀምሮ የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ኮሚሽነር አድርገው መሾማቸውን ያስታወቀው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ነው። ጽህፈት ቤቱ ይህን ሹመት ይፋ ከማድረጉ ሁለት ሰዓት አስቀድሞ ባሰራጨው መረጃ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባደረገው መደበኛ ስብሰባ አዲሱን የኮሚሽን መስሪያ ቤት የሚያቋቋም ደንብ ማጽደቁን አስታውቆ ነበር።
ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ የኒውክሊየር ቴክኖሎጂን ከዓለም አቀፍ ማዕቀፎች በተጣጣመ መልኩ “ለሰላማዊ መንገድ” ለመጠቀም የምታደርገውን ጥረት “የመምራት እና የማስተባበር ኃላፊነት” የተጣለበት ነው። አቶ ሳንዶካን ይህንን መስሪያ ቤት እንዲመሩ ከመሾማቸው አስቀድሞ፤ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ላለፉት 14 ዓመታት ሰርተዋል።
በ2001 ዓ.ም. ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በምግብ ሳይንስ እና በምርት አሰባሰብ ቴክኖሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት አቶ ሳንዶካን፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምግብ ሳይንስ እና ኒዩትሪሽን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል። በዚሁ ዓመት የብዝሀ ህይወት ጥበቃ ኢንስቲትዩት የሚባለውን መንግስታዊ ተቋም በምርምር ሰራተኝነት ተቀላቅለዋል።
በኢንስቲትዩቱ ሶስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የቆዩት አቶ ሳንዶካን፤ ቀጣይ ማረፊያቸው የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (አስቱ) ነበር። በዩኒቨርሲቲው ለአንድ ዓመት ከአራት ወራት ያስተማሩት አቶ ሳንዶካን፤ ወደ መንግስት የስራ ኃላፊነት ከመጡበት ከህዳር 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በሰባት መስሪያ ቤቶች ተሹመው ሰርተዋል።
የአቶ ሳንዶካን የመጀመሪያውን ሹመት ያገኙት በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል ነው። ማዕከሉን ለአንድ ዓመት ከሶስት ወራት በዋና ዳይሬክተርነት ከመሩ በኋላ በተመሳሳይ የሹመት ደረጃ ወደ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ተዛውረዋል።

አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከልን በዋና ዳይሬክተርነት መምራታቸው አይዘነጋም። ይኸው ማዕከል ስያሜውን ወደ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ከቀየረ በኋላም፤ አቶ ሳንዶካን በዋና ዳይሬክተርነት ለሁለት ዓመታት መርተውታል።
አቶ ሳንዶካን በግንቦት 2010 ዓ.ም. ወደ ቀደመው መስሪያ ቤታቸው ከመመለሳቸው በፊት የነበሩትን ሁለት ዓመታት፤ በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት እና በኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አሳልፈዋል። ጽህፈት ቤቱን በዋና ዳይሬክተርነት ለአንድ ዓመት፣ ኢንስቲትዩቱን ደግሞ በምክትል ዳይሬክተርነት ለሁለት ዓመት ከሁለት ወር ጊዜ በኃላፊነት መርተዋል።
ወጣቱ የመንግስት የስራ ኃላፊ የብዙዎቹን ትኩረት የሳቡት፤ ሌላኛዋን ወጣት ባለስልጣን ለሊሴ ነሜን በመተካት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ በመሆን በሰኔ 2012 ዓ.ም. ሲሾሙ ነበር። በኮርፖሬሽኑ ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ የቆዩት አቶ ሳንዶካን፤ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው የተሾሙት በጥቅምት 2015 ዓ.ም ነበር።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለአንድ ዓመት ብቻ በኃላፊነት የሰሩት አቶ ሳንዶካን፤ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው በጥቅምት 2016 ዓ.ም. ተሹመዋል። አቶ ሳንዶካን ለሁለት ዓመት በኃላፊነት የመሩት ልዩ ጽህፈት ቤት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስር ካሉ ስድስት መዋቅሮች አንዱ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስር ያሉ ሌሎች መዋቅሮች የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት፣ የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት፣ የፕሬስ ሴክሪተሪያት፣ የፖሊሲ እና የአፈጻጸም ክትትል ክፍል እንዲሁም የሪፐብሊኩ ጠባቂ ናቸው።
በስራቸው ጸባይ ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚገኙባቸው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት ሁነቶች እና ጉብኝቶች ላይ ከአጠገባቸው የማይጠፉት አቶ ሳንዶካን፤ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር የኒውክሊየር የኃይል ማመንጫ ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት በተፈራረመችበት ወቅትም በቦታው ተገኝተዋል። ሁለቱ ሀገራት ስምምነቱን የተፈራረሙት መስከረም 15፤ 2018 ዓ.ም ነበር።

የስምምነት ሰነዱ “በኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ለማሳደግ” ያለመ የድርጊት መርሃ ግብርን የያዘ መሆኑን የሩሲያ አቶሚክ ኢነርጂ ኮርፖሬሽን አስታውቋል። የድርጊት መርሃ ግብሩ፤ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ግንባታ ፕሮጀክቱን ዝርዝር ማብራሪያ፣ ወደ አዋጭነት ጥናት የሚመራ ፍኖተ ካርታ እና በሁለቱ መንግስታት መካከል የሚፈረም ስምምነት የማዘጋጀት ኃላፊነት የተጣለበት ልዩ የስራ ቡድን ያቋቁሟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)