በጋምቤላ ከተማ የሰዓት እላፊ እንዲታወጅ መንስኤ የሆነው ምንድነው? 

ብሔራዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋምቤላ ክልል በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶች አሳሳቢ መሆናቸውን በተለያየ ጊዜ በሚያወጣቸው መግለጫዎች እና ሪፖርቶች ሲገልጽ ቆይቷል። የኮሚሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ከሦስት ሳምንት በፊት በክልሉ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት፤ ይኸው ጉዳይ ተነስቶ ነበር። 

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ ከጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጋር አለሚቱ ኡሙድ እና ከሌሎች የስራ ኃላፊዎች ጋር በነበራቸው ውይይት፤ በክልሉ “አልፎ አልፎ” ይከሰታሉ ያሏቸው “ግጭቶች” እና “ጥቃቶችን” ለማስቀረት፤ “ጠንካራ የቅድመ መከላከል ሥራ እንዲሠራ” ጠይቀው ነበር። ኮሚሽነሩ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በክልሉ ዳግም በተፈጸመ ጥቃት ሳቢያ በጋምቤላ ከተማ የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል። 

የክልሉ መንግስት መቀመጫ በሆነችው የጋምቤላ ከተማ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ በሚደረግ የተሽከርካሪ እና የሰው እንቅስቃሴ ላይ ክልከላ የተጣለው ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ህዳር 30፤ 2018 ነው። የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከጸጥታ አካላት ውጭ በሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ላይ ገደብ የጣለው “በወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ” ምክንያት እንደሆነ አስታውቋል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በትላንትናው ዕለት ያነጋገረቻቸው በክልሉ በቢሮ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ፤ በከተማይቱ ባለው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት እርሳቸው በሚገኙበት አካባቢ ትምህርት ቤቶች እና ባንኮች ዝግ መሆናቸውን ተናግረዋል። የሰዎች እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ባይቆምም፤ በከተማው የመኪና እንቅስቃሴ እንደቀነሰ አስረድተዋል። 

እኚሁ ግለሰብ እርሳቸው በሚሠሩበት የመንግሥት ተቋም ሥራ ላይ እንደነበሩ ቢገልጹም፤ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት ሌላኛዋ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ ግን በትላንትናው ዕለት በሥራ ገበታቸው ላይ እንዳልተገኙ እና ልጆቻቸውንም ወደ ትምህርት ቤት እንዳልላኩ ተናግረዋል።

“ልጆቼ ትምህርት ቤት አልሄዱም። ሰው ይፈራል፣ ልጆቹንም አይልክም። [ማክሰኞ] ማታም ‘ጥንቃቄ አድርጉ፣ ልጆቻችሁን ያዙ’ ተብሎ በተለያየ ቋንቋ በይፋ በድምጽ ማጉያ ሲነገር ነበር። ስለዚህ ይህንን እየሰማሽ ልጅሽን አትልኪም” ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል። 

እኚሁ ነዋሪ ረፋድ ላይ ወደ መሀል ከተማ ሞባይል ስልክ ለመግዛት በሄዱበት ወቅት፤ ባንኮች እና የኤሌክትሮኒክስ ሱቁች ዝግ ሆነው መመልከታቸውን ጠቅሰዋል። በሰዓቱም ሱቆች ተዘግተው እንደነበርና እርሳቸውም የፈለጉትን ሳያገኙ መመለሳቸውን፣ ገንዘብ ለማውጣትም ወደ ባንክ ሲያቀኑ፣ ባንኮች መዘጋታቸውን እንደታዘቡ አስረድተዋል። 

ሆኖም ሽንኩርት፣ አትክልቶች እና የምግብ ግብዓቶችን የሚሸጡ ሱቆች አንድ በር ከፍተው ሲሸጡ እንደነበርም መመልከታቸውን አክለዋል። በከተማው በሚገኝ ሆስፒታል የሚሠሩ የጤና ባለሙያ፤ እስከ ትላንት ረፋዱ አምስት ሰዓት ድረስ በከተማው መሃል የነበሩ ባንኮች እና ሱቆች ዝግ እንደነበሩ የዓይን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከከተማይቱ አጠቃላይ አመራሮች ጋር ትላንት እና በዛሬው ዕለት ባደረገው ውይይት፤ የንግድ እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ክፍት ሆነው አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ አሳስበው ነበር። በትላንቱ ውይይት ሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ ውሳኔ መተላለፉን የከተማይቱ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገልጿል። 

በዛሬው ዕለት የተወሰነ የሰዎች እንቅስቃሴ መኖሩን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት የከተማዋ ነዋሪ፤ ሆኖም እርሳቸው የሄዱበት በአቅራቢያቸው የሚገኝ ባንክ አሁንም ዝግ እንደሆነ እና ልጆቻቸውን ዛሬም ወደ ትምህርት ቤት አለመላካቸውን ገልጸዋል። በከተማይቱ የክልሉ እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ተሰማርተው መመልከታቸውንም አስረድተዋል። 

በጋምቤላ ከተማ ባለፉት ቀናት ለተከሰተው “የጸጥታ መደፍረስ” ምክንያት የሆነው፤ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ምሽት በከተማው ቀበሌ 03 ኢትዮ-ቴሌኮም በሚገኝበት አካባቢ የተፈጠረ ክሥተት እንደሆነ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የከተማይቱ የፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በዚሁ ዕለት አንድ ግለሰብ በሁለት ሰዎች ላይ በሽጉጥ ጉዳት ካደረሰ በኋላ የአንደኛው ሕይወት ማለፉን እና ሌላኛው ሕክምና እየተደረገለት እንደሚገኝ አስረድተዋል። ጉዳት ያደረሰው ግለሰብ ሮጦ ማምለጡን የገለጹት ኃላፊው፤ በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የፖሊስ ኃላፊው ለዚህ ክስተት መነሻ ሳይሆን አይቀርም የሚሉት፤ ባለፈው እሁድ ከኢታንግ ወረዳ ወደ ጋምቤላ 16 ሰዎች አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አውቶብስ ላይ የደረሰውን ጥቃት ነው። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽኑ ይህንኑ ክስተት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፤ አውቶብሱ “ታርፓም” የሚባል ቦታ ላይ ሲደርስ፤ ተሳፋሪዎችን ወደ ሌላ አውቶብስ በማዘዋወር ላይ እያለ ጥቃት እንደደረሰበት ገልጾ ነበር። 

በዚህም የ22 ዓመት ወጣት ሴት ሕይወት እንዳለፈ እና የ24 ዓመት ወጣት ሴት ከባድ ጉዳት ደርሶባት በጋምቤላ አጠቃላይ ሆስፒታል በጽኑ ሕሙማን ክፍል ሕክምና እየተከታተለች መሆኑን ኮሚሽኑ ማስታወቁ አይዘነጋም። ይህን ጥቃት ፈጽሟል የተባለው ተጠርጣሪ በጊዜው በሥራ ላይ በነበረ የትራፊክ ፖሊስ ላይ ለመተኮስ ሲሞክር መሣሪያው ስለከሸፈበት ማምለጡን ኮሚሽኑ ገልጿል። 

እኚሁ ኃላፊ ከትላንት በስቲያ በከተማው የደረሰው ጥቃት፤ ከሶስት ቀናት በፊት የተገደለችውን ወጣት “ደም ለመመለስ የተደረገ ነው” የሚል ግምት አላቸው። ወጣቷ የተገደለችበትን የመሰለ በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ የሚሰነዝር ጥቃት ለጋምቤላ ክልል እንግዳ አይደለም። 

ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ በጋምቤላ ከተማ እና በአቦል ከተማ መካከል በሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ላይ በተከፈተ ተኩስ “የተወሰኑ” ተሳፋሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጾ ነበር። ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመለየት የክልሉ ፖሊስ እና የፈደራል የጸጥታ አካላት ባደረጉት ክትትል፤ የተጠርጣሪዎቹ ማንነት መለየቱንም ኮሚሽኑ በወቅቱ ማስታወቁም አይዘነጋም።

ለእሁድ የአውቶብስ ጥቃት “ምላሽ ነው” የተባለው የጋምቤላ ከተማው ክስተት በተፈጸመበት ዕለት፤ በላሬ ወረዳ ላይ የመንግሥት አመራሮች ላይ ጥቃት ደርሶ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል። በጋምቤላ ከተማ 90 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ላሬ ወረዳ ከትላንት በስቲያ የደረሰው ጥቃት አድራሾች እስካሁን አለመለየታቸውን ምንጮች አክለዋል። 

ባለፈው ማክሰኞ በጋምቤላ ከተማ የተፈጠረው አይነት ክስተት ተከትሎ፤ አንዱ ብሔር ሌላውን መወንጀሉ የተለመደ መሆኑን  ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የከተማይቱ የፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ያስረዳሉ።  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፉት ዓመታት ያወጣቸው መግለጫዎች እና ሪፖርቶች ይህንኑ የሚያረጋግጡ ክሰተቶችን ይዘዋል። 

በግንቦት 2015 ዓ.ም. በኢታንግ ልዩ ወረዳ ሥር በሚገኝ ፒኝዋ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ አንድ ግለሰብ መጥፋታቸውን ተከትሎ በአካባቢው የተቀሰቀሰ ግጭት፤ ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ ወደ ሌሎች ቦታዎች በመዛመት የ138 ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ ምክንያት መሆኑን ኢሰመኮ በየካቲት 2016 ባወጣው ሪፖርት አስታውቆ ነበር። በዚህ ግጭት በግለሰቦች እና ተቋማት ንብረት ላይ ተጨማሪ ጉዳት መድረሱን ኢሰመኮ በወቅቱ ገልጿል። 

ይህንን ግጭት ተከትሎ የጋምቤላ ክልል ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ እስከ ጥዋት 12 ሰዓት ድረስ በሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ የሚደረግ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥሎ እንደነበር ይታወሳል። በጋምቤላ ክልል ከሰሞኑ የተፈጠሩ ሁነቶች “አሳሳቢ” መሆናቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጸው ኢሰመኮ፤ ክስተቶችን በተመለከተ “ክትትል እያደረገ” መሆኑን አስታውቋል። ኮሚሽኑ በክትትሉ የደረሰበትን ውጤት ወደፊት ይፋ እንደሚያደርግም ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)