የአሜሪካዊቷ ሚኒስትር ክሪስቲ ኖም ውሳኔ በቦስተን ከተማ ለምትኖረው ኢትዮጵያዊቷ ነርስ *ሜላት ገብረ እግዚያብሔር “መርዶ” ሆኖባታል። የአሜሪካ ዲፓርትመንት ኦፍ ሆምላንድ ሴኪዩሪቲ (Department of Homeland Security) ሚኒስትር የሆኑት ክሪስቲ ከትላንት በስቲያ አርብ ያስተላለፉት ውሳኔ፤ እንደ እርሷ ሁሉ “ጊዜያዊ ከለላ” አግኝተው በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን አስደንግጧል።
የ54 ዓመቷ ሚኒስትር የአርብ ዕለት ውሳኔ፤ ሜላትን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ለመቆየት የሚያስችላቸውን ሕጋዊ ከለላ ያሳጣ ነው። ውሳኔው ይፋ ከተደረገ በኋላ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጋር አጭር ቆይታ የነበራት ሜላት “እንዴት እንደምተኛም አላውቅም” ስትል ጭንቀቷን አጋርታለች።
ሜላትን ለጭንቀት እና ፍርሃት የዳረጋት ውሳኔ የተላለፈው፤ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታ “ጊዜያዊ ከለላ” ለመስጠት የሚያስፈልገውን “ቅድመ ሁኔታ” እንደ ቀደሙት ጊዜያት “የሚያሟላ አይደለም” በሚል ምክንያት ነው። በአሜሪካ ለተወሰነ ጊዜ መቆየት የሚያስችለውን “ጊዜያዊ ከለላ” የሚያገኙት፤ ግጭት እየተካሄደባቸው ከሚገኙ፣ የተፈጥሮ አደጋ ወይም ሌሎች ፖለቲካዊ ቀውሶች ከገጠማቸው ሀገራት ለሚጓዙ ዜጎች ነው።

ከለላው የተሰጣቸው ሰዎች ወደ ትውልድ ሀገራቸው በግዳጅ ከመመለስ በህግ የሚጠበቁ ሲሆን በአሜሪካ ለመስራት የሚያስችላቸው ፈቃድ ያገኛሉ። ኢትዮጵያውያን ይህን የሰብአዊ ጥበቃ ያገኙት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ወቅት በታህሳስ 2015 ዓ.ም ነበር።
በወቅቱ ከለላውን ለማግኘት ብቁ የሆኑ 26,700 ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ይገኛሉ ተብሎ ይገመት እንደነበር የአሜሪካ ሀገር ውስጥ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰነድ ያሳያል። ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠው “ጊዜያዊ ከለላ” የሚቆየው እስከ ግንቦት 2016 ድረስ እንደሆነ አስቀድሞ ቢገለጽም፤ ቀነ ገደቡ ከማብቃቱ አንድ ወር በፊት ለተጨማሪ 18 ወራት ተራዝሟል።
በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ወቅት የዲፓርትመንት ኦፍ ሆምላንድ ሴኪዩሪቲ ሚኒስትር የነበሩት የአሌሀንድሮ ማዮርካስ ውሳኔ፤ 2,300 ገደማ ኢትዮጵያውያን የተሰጣቸው ከለላ እንዲራዘም አድርጓል። ከሚያዝያ 03፤ 2016 በፊት ወደ አሜሪካ የገቡ ሌሎች 12,800 ኢትዮጵያውያን ወይም ዜግነት የሌላቸው እና ለመጨረሻ ጊዜ በኢትዮጵያ የኖሩ ሰዎችም ከለላው እንዲሰጣቸው ለማመልከት በር ከፍቷል።

በፈረንጆቹ 1990 በአሜሪካ ኮንግረስ በጸደቀው የአሚግሬሽን ህግ እንዲካተት የተደረገውን “የጊዜያዊ ከለላ” የሚያገኙ ሀገራት ዜጎች የትኞቹ እንደሆኑ የመወሰን ስልጣን የተሰጠው የአሜሪካ ዲፓርትመንት ኦፍ ሆምላንድ ሴኪዩሪቲ ነው። ይህ ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት፤ መስሪያ ቤቱን በሚኒስትርነት የሚመሩት ግለሰብ ከሌሎች የመንግስት ተቋማት መመካከር እንደሚገባቸው በህግ ተደንግጓል።
ምክረ ሃሳብ መስጠት የሚጠበቅባቸው ተቋማት የትኞቹ እንደሆኑ በህግ ባይዘረዘርም፤ በተለምዶ ባለው አሰራር ግን ጉዳዩ ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ ከብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት እንዲሁም ከሀገሪቱ የፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመመካከር ውሳኔ የሚሰጥበት ነው። ክሪስቲ ኖም ባለፈው አርብ ታህሳስ 3፤ 2018 ያስተላለፉት ውሳኔ፤ የኢትዮጵያን ሁኔታ በመገምገም እና የሚመለከታቸው የዩናይትድ ስቴትስ ተቋማት በማማከር የተደረገ እንደሆነ የአሜሪካ የዜግነት እና ፍልሰት አገልግሎት ያወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በመግለጫው የተጠቀሱት የእዚሁ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ፤ ለኢትዮጵያውያን ተሰጥቶ የነበረው ከለላ “በጊዜ የተወሰነ” መሆኑን ጠቁመው፤ አሰራሩ ቀድሞም ቢሆን “ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ” ማግኘት የሚቻልበት እንዳልሆነ አስረድተዋል። በዚህ መሰረት በዩናይትድ ስቴትስ ለመቆየት የሚያስችል “ሌላ ህጋዊ መሰረት” የሌላቸው ኢትዮጵያውያን፤ ሀገሪቱን “በፈቃደኝነት” ለቅቀው ለመውጣት 60 ቀናት እንዳላቸው መስሪያ ቤቱ አሳውቋል።

በፈቃዳቸው የአሜሪካ ጉምሩክ እና የድንበር ጥበቃ መስሪያ ቤት ያዘጋጀውን የሞባይል መተግበሪያ በመጠቀም ከዩናይትድ ስቴትስ ለቅቀው ለሚወጡ ኢትዮጵያውያን፤ የአውሮፕላን በረራ ትኬት እና የመውጫ አንድ ሺህ ዶላር ጉርሻ እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸዋል። በዚህ መልኩ አሜሪካንን ለቅቀው የሚወጡ ኢትዮጵያውያን፤ ለወደፊት በህጋዊ መንገድ ወደ አሜሪካ ተመልሰው የመግባት ዕድል ሊኖራቸው እንደሚችልም በመስሪያ ቤቱ መግለጫ ላይ ሰፍሯል።
ሁሉም የአሜሪካ መንግስት ማባበያዎች ግን ሜላትን የሚያሳምኑ አይደሉም። “መመለስ አልፈልግም። ለምንድነው የምመለሰው?” ስትል ትጠይቃለች ሜላት። የአርቡን ውሳኔ ይፋ የተደረገበት የአሜሪካ የዜግነት እና ፍልሰት አገልግሎት መግለጫ፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ወደ ሀገራቸው ለሚመለሱ ዜጎች “በግል ደህንነታቸው ላይ ከባድ ስጋት አይፈጥርም” ቢልም፤ ሜላት በዚህ አትስማማም።
ሜላት በዚህ ምክንያት ወደ ሀገር ቤት መመለስ ባትፈልግም፤ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በአሜሪካ የሚገኙ ፍልሰተኞችን ለማስወጣት የሚከተለው ኃይል የቀላቀለ አካሄድ ያሰጋታል። በምትኖርበት ቦስተን ከተማ የአሜሪካ የፍልሰት እና የጉምሩክ መስሪያ ቤት ጸጥታ አስባሪዎች (ICE agents) እንደ እሷ ከሌሎች ሀገራት የመጡ ሰዎችን “እያባረሩ እና እያዳፉ ሲያስሯቸው” ተመልክታለች።

ተመሳሳይ እጣ ፈንታ “እኔም ሊገጥመኝ ይችላል” ብላ የምትሰጋው ሜላት፤ በምታውቃቸው ሰዎች በኩል የሰማቻቸው እርምጃዎች ፍርሃቷን ከፍ ያደርገዋል። “ሔሺያን ጓደኛ አለችኝ። እነሱ ላይ ደርሶባቸዋል። ሚኒሶታም ተመሳሳይ ነገር ነግረውኝ ነበር” ትላለች ሜላት። የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ባለፉት ወራት የተሰጣቸው “ጊዜያዊ ከለላ” ካነሳባቸው ሀገራት መካከል ሔይቲ አንዷ ናት።
የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆኑት ደቡብ ሱዳን በጥቅምት ወር መጨረሻ እና ሶማሊያ ደግሞ ባለፈው ወር አጋማሽ ላይ የተመሳሳይ እርምጃ ሰለባ ሆነዋል። “በጊዜያዊ ከለላ” በአሜሪካን ሀገር ያሉ የማይንማር፣ የሶሪያ እና የቬኒዙዌላ ዜጎችም ሀገሪቱን በ60 ቀናት ለቅቀው እንዲወጡ ባለፉት ወራት ተመሳሳይ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።
እስካለፈው ዓመት መጋቢት ወር ድረስ “ጊዜያዊ ከለላ” ተሰጥቷቸው በአሜሪካ የሚኖሩ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ብዛት 1.3 ሚሊዮን ገደማ እንደነበር የፍልሰተኞች ጉዳይ የሚከታተለው የአሜሪካ ኢሚግሬሽን ካውንስል መረጃ ያመለክታል። በዚሁ ተቋም መረጃ መሰረት እስካለፈው ህዳር ወር ድረስ የዚሁ ከለላ ተጠቃሚ የሆኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 ሀገራት ነበሩ።

ሜላት የተሰጣት “ጊዜያዊ ከለላ” ከመገባደዱ በፊት ጥገኝነት ለማግኘት ጥያቄ ብታቀርብም፤ የአሁኑ ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት እንኳን ሂደቱ መቼ እንደሚጠናቀቅ እርግጠኛ አልነበርችም። በአርቡ ውሳኔ ምክንያት ግን የተገን ማመልከቻዋ ተቀባይነት ከማግኘቱ በፊት፤ ተጠርንፋ ወደ ኢትዮጵያ የመላክ አደጋ ከፊቷ ተጋርጦባታል።
የአሜሪካ መንግስት የሰጣቸው ከለላ ያበቃ ኢትዮጵያውያንን፤ ከየካቲት 6፤ 2018 በኋላ ወደ ሀገራቸው በግዳጅ እንደሚልክ አስታውቋል። ታስረው በግዳጅ ወደ ሀገራቸው የተላኩ ዜጎች ከዚህ በኋላ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መመለስ “ፈጽሞ ያለመመለስ” ዕጣ ፈንታ ሊገጥማቸው እንደሚችል የሀገሪቱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስጠንቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
* በዚህ ዘገባ የተጠቀሰችው ኢትዮጵያዊት የግል መረጃውን ለመጠበቅ ሲባል ስሟ ተቀይሯል። (አዘጋጁ)































