የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አራት አዳዲስ ኮሚሽነሮች ተሾሙለት 

ብሔራዊው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተጓደሉ ኮሚሽነሮች ምትክ አራት አዳዲስ አመራሮች ተሾሙለት። ዛሬ በፓርላማ ሹመታቸው ከደጸቀላቸው ኮሚሽነሮች መካከል ሶስቱ በተቋሙ እያገለገሉ የቆዩ ናቸው። 

በ2012 ዓ.ም የተሻሻለው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ተቋሙ አንድ ዋና ኮሚሽነር እና አንድ ምክትል ዋና ኮሚሽነር እንዲሁም የሕጻናትና የሴቶች ጉዳዮችን በበላይነት የሚመሩ ኮሚሽነርን ጨምሮ ከአራት ያላነሱ የልዩ ልዩ ሰብአዊ መብቶች ዘርፍ ኃላፊዎች እንደሚኖሩት ይደነግጋል።  በአዋጁ መሰረት ለኮሚሽነርነት የታጩ ግለሰቦች የሚመለመሉት በገለልተኛ ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ አማካኝነት ነው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤን በሰብሳቢነት እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትን በምክትል ሰብሳቢነት የሚይዘው ይህ ኮሚቴ፤ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከምርጫ ቦርድ፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ከሲቪል ማኅበራት የተውጣጡ አባላት እንደሚኖሩት በአዋጁ ተቀምጧል። ኮሚቴው የራሱን መንገድ በመጠቀም እንዲሁም ግልጽ አሳታፊ አሰራር መዘርጋት በሕዝብ ጥቆማ ከቀረቡ ግለሰቦች ውስጥ “መስፈርቱን የሚያሟሉ” እና “በአብላጫ ድምጽ የተደገፉ ዕጩዎችን” ለፓርላማ እንደሚያቀርብም አዋጁ ያትታል።

በዚህ መሰረት ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 15፤ 2018 መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት፤ ለምክትል ዋና ኮሚሽነርነት የኃላፊነት ቦታ እንዲሁም የተቋሙን የተለያዩ ዘርፎችን ለመምራት በዕጩነት የቀረቡ ግለሰቦችን ሹመት መርምሮ አጽድቋል። ባለፈው ሐምሌ ወር በገዛ ፍቃዳቸው ስራቸውን በለቀቁት የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ምትክ፤ በቦታው የተሾሙት ዶ/ር ሚዛኔ አባተ ናቸው።

ዶ/ር ሚዛኔ በኢሰመኮ ውስጥ የሰብአዊ መብቶች ማሳደግ ከፍተኛ አማካሪ፣ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ዲፓርትመንቶችን በዳይሬክተርነት እና በከፍተኛ ዳይሬክተርነት መርተዋል። ከአሁኑ ሹመታቸው በፊትም የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ አማካሪ ሆነው ሲሰሩ ነበር። 

በህግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኙት አዲሱ የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር፤ በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው ፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ ይዘዋል። የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በኢንተርዲሲፕሊነሪ ጥናት በአሜሪካው አላባማ ዩኒቨርሲቲ የሰሩት ዶ/ር ሚዛኔ፤ ረጅም የስራ ዘመናቸውን በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት በማስተማር አሳልፈዋል።

ፎቶ፦ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤትን ለሁለት ዓመት ከስምንት ወር በዳይሬክተርነት የመሩት አዲሱ ተሿሚ፤ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተማሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብቶች ህግን ሲያስተምሩ ቆይተዋል። እንደ እርሳቸው ሁሉ የህግ ትምህርት ተመራቂ የሆኑት ወ/ሮ አሸነፈች አበበ፤ የኢሰመኮ የሴቶች እና ህጻናት ጉዳዮች ዘርፍን በኮሚሽነርነት እንዲመሩ በዛሬው ዕለት ተሹመዋል።

ይህንን ዘርፍ ከአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ጉዳዮች ዘርፍ ጋር ደርበው ሲመሩ የቆዩት ርግበ ገብረሐዋርያ ነበሩ። ርግበ እንደ ቀድሟዋ የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ሁሉ ስራቸውን በገዛ ፍቃዳቸው የለቀቁት ባለፈው ሐምሌ ወር ነበር። ሁለቱ ኮሚሽነሮች የስራ መልቀቂያቸውን ያስገቡት፤ አቶ ብርሃኑ አዴሎ ተቋሙን በዋና ኮሚሽነርነት እንዲመሩ ከተሾሙ ከስድስት ወራት በኋላ ነው።

አዲሷ የኢሰመኮ የሴቶች እና ህጻናት ጉዳዮች ዘርፍ ኮሚሽነር ወ/ሮ አሸነፈች፤ ወደዚህ የኃላፊነት ቦታ ከመምጣታቸው በፊት የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው በመስራት ላይ ነበሩ። በምክትል ፕሬዝዳንትነት ኃላፊነት ሰባት ዓመታት የሰሩት ወ/ሮ አሸነፈች፤ በዚሁ ፍርድ ቤት እና በአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት በዳኝነት አገልግለዋል።

ፎቶ፦ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት

ተሿሚዋ በፍትህ ሚኒስቴር በዓቃቤ ህግነት እንዲሁም በአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ በሕግ ረቂቅ ዝግጅት ኦፊሰርነት የስራ ልምድም አላቸው። ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ የያዙት ወ/ሮ አሸነፈች፤ ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በአመራር እና አስተዳደር የማስተርስ ዲግሪ አግኝተዋል።

በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ጉዳዮች ዘርፍ ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት አቶ መሐመድ ሀሰንም በተመሳሳይ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ያገኙት ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ነው። አቶ መሐመድ በህግ ዲፕሎማቸውን ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ከያዙ በኋላ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ለማግኘት ችለዋል።

በአፋር ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ዳኛ የነበሩት አቶ መሐመድ፤ ከአሁኑ ሹመታቸው በፊት በኢሰመኮ ለሶስት ዓመታት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሰርተዋል። አቶ መሐመድ የኮሚሽኑ የክትትል ምርመራ አስተባባሪ፣ የሰመራ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ዳይሬክተር እንዲሁም የክልል ክትትል እና ምርመራ ዳይሬክተር በመሆን ሲሰሩ ቆይተዋል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ላለፉት ስምንት ወራት የሰሩት አቶ በዳሳ ለሜሳ ሌላው ተሿሚ ናቸው። ከሹመታቸው በፊት በኢሰመኮ የክትትል እና ምርመራ ከፍተኛ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ በዳሳ፤ በዚሁ ክፍል ውስጥ በክልል ዳይሬክተርነት ሰርተዋል። የኮሚሽኑ የትምህርት እና ስልጠና ዘርፍ ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት አቶ በዳሳ፤ በህግ ዲፕሎማ እና ዲግሪያቸውን ከአልፋ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የህግ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]