እስራኤል ለሶማሌላንድ እውቅና መስጠቷን ተከትሎ ማን ምን አለ?

ላለፉት 34 ዓመታት ራሷን ከሶማሊያ ነጥላ ነጻ እና ሉዓላዊ ሀገር አድርጋ የምትቆጥረው ሶማሌላንድ፤ ዛሬ ዓርብ ታኅሣሥ 17፤ 2018 የመጀመሪያውን ይፋዊ የሀገርነት እውቅና ከእስራኤል አግኝታለች። እስራኤል ለሶማሌላንድ የነጻ ሀገርነት እውቅና መስጠቷን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ከሶማሌላንዱ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ ጋር በሞባይል ስልክ የቪዲዮ መስመር እየተነጋገሩ ዕውቅና በሰጡበት ሰነድ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል። ለሶማሌላንድ ዕውቅና በመስጠት “ቀዳሚዋ ሀገር ትሆናለች” በሚል ከዚህ ቀደም የሀገሬው ሰዎች ተስፋቸውን የጣሉት በኢትዮጵያ ላይ ነበር።

ይህ ተስፋቸው ይበልጥ ጎልቶ የተስተዋለው፤ ልክ እንዳሁኑ የዛሬው ሁለት ዓመት ታህሳስ ወር ላይ የቀድሞው የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሒ አብዲ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር “የአጋርነት እና የትብብር የመግባቢያ ስምምነት” ከተፈራረሙ በኋላ ነበር። የመግባቢያ ስምምነቱ ተግባራዊ ሲሆን ኢትዮጵያ ለሶማሌንድ እውቅና እንደምትሰጥ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሒ በወቅቱ  መናገራቸው ለዚህ በማስረጃነት ሲጠቀስ ቆይቷል። 

ባለፈው ዓመት ምርጫ አሸንፈው የሶማሌላንድን ፕሬዝዳንት መንበርን የተረከቡት ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ፤ ለመግባቢያ ስምምነቱ ድጋፋቸውን ማሳየታቸውም አይዘነጋም። ይሁን እንጂ የመግባቢያ ስምምነቱ በኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድን የግዛቷ አካል አድርጋ በምትቆጥራት ሶማሊያ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ማስከተሉ የዕውቅና ተስፋው እንዲደበዝዝ ምክንያት ሆኗል።   

ሁለቱ ሀገራት በቱርክ ፕሬዝዳንት አሸማጋይነት የሻከረ ግንኙነታቸውን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት በአንካራ ከተማ ስምምነት ካደረጉ በኋላ ደግሞ ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ ዕውቅና የማግኘቷ ጉዳይ እውን መሆኑ ይበልጥኑ አጠራጥሯል። ከኢትዮጵያ ይልቅ አሜሪካ ለሶማሌላንድ ዕውቅና በመስጠት “ቀዳሚዋ ሀገር ትሆናለች” የሚለው ተስፋ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጠንከር ብሎ መደመጡም ቀጥሎ ነበር።

ዓለም አቀፍ መነጋገሪያ ሆኖ የቆየው የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነት ሁለተኛ ዓመቱን ሊደፍን የአምስት ቀናት ብቻ ዕድሜ ሲቀሩት፤ እስራኤል ያልተጠበቀ እና ታሪካዊ ውሳኔ ማስተላለፏን ይፋ አደረገች። እስራኤል ያሳለፈችው ውሳኔ፤ ሀገሪቱ ለሶማሌላንድ የነጻ እና ሉዓላዊ ሀገርነት እውቅናን በይፋ በመስጠት ቀዳሚነቱን እንድትወስድ ያደረገ ነው።   

እስራኤል እና ሶማሌላንድ ምን አሉ?

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳአር እና “የሶማሌላንድ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት” የጋራ ስምምነት መግለጫ መፈራረማቸውንም አስታውቋል። ኔታንያሁ በቪዲዮ የስልክ ንግግራቸው ወቅት፤ አብዲራህማን ኢሮ በተሰኘው የቅጽል ስማቸው ይበልጡኑ የሚታወቁትን የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት “እንኳን ደስ አልዎት” ብለዋቸዋል። ፕሬዝዳንቱ እስራኤልን እንዲጎበኙም ጋብዘዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ “ታሪካዊ” ሲሉ የገለጹትን እስራኤል ለሶማሊላንድ እውቅና የመስጠቷን እርምጃ የወሰደችው፤ “በፕሬዚዳንት ትራምፕ አነሳሽነት በተፈረመው የአብርሃም ስምምነት መንፈስ ነው” ሲሉ አስረድተዋል። እስራኤል በግብርና፣ በጤና፣ በቴክኖሎጂ እና በኢኮኖሚ መስኮች ሰፊ ትብብር በማድረግ “ከሶማሌላንድ ሪፐብሊክ ጋር ያላትን ግንኙነት “በፍጥነት የማሳደግ” እቅድ እንዳላትም ተናግረዋል።

ኔታንያሁ እና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት “ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ለመፍጠር የሚያስችል” ስምምነት መፈራረማቸውን የገለጹት የእስራኤሉ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳአር፤ ይህም “የአምባሳደሮች ሹመት እና ኤምባሲዎችን መክፈት” እንደሚያካትት አስታውቀዋል። “የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በተለያዩ መስኮች ተቋማዊ ለማድረግ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቴን አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ አዝዣለሁ” ሲሉም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በይፋዊ የኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

የሶማሊላንዱ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ኢሮ፤ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ለ“ሶማሌላንድ ሪፐብሊክ” እውቅና መስጠታቸውን “ታሪካዊ” ካሉ በኋላ፤ ሶማሌላንድም የአብርሃም ስምምነትን ለመቀላቀል ዝግጁ መሆኑኗን አረጋግጠዋል። ይህ እርምጃ “የጋራ ጥቅሞችን የሚያጎለብት፣ ቀጣናዊ ሰላምና ፀጥታን የሚያጠናክር፣ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎናፅፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የተጀመረበት ነው” ሲሉም አሞካሽተውታል።

ሌሎች ሀገራት የእስራኤልን ውሳኔ እንዴት ተቀበሉት?

ሶማሌላንድን “የግዛቴ አካል ነች” የምትለው ሶማሊያ፤ ይህን አቋሟን ወደ ጎን በማድረግ እስራኤል የሰጠችውን የነጻ ሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና በተመለከተ እስካሁን በይፋ ያለችው ነገር የለም። ትላንት ምርጫ ስታካሂድ የዋለችው ሶማሊያ ይፋዊ መግለጫ ባትሰጥም፤ በጉዳዩ ላይ ለመወያየት የሀገሪቱ መንግስት ካቢኔ ዛሬ ምሽቱን አስቸኳይ ስብሰባ እንደሚቀመጥ ተዘግቧል።

ከሶማሌላንድ ጋራ በፈጸመችው የመግባቢያ ስምምነት ምክንያት ከሶማሊያ ጋራ የተካረረ ውጥረት ውስጥ ገብታ የነበረችው እና በርካታ ተቃውሞዎችን ያስተናገደችው ኢትዮጵያም፤ በእስራኤል እርምጃ ዙሪያ እስካሁን በይፋ መግለጫ አልሰጠችም። ኢትዮጵያ እስካሁን በይፋ ምንም ባትልም፤ የቀድሞው የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ብርሃኑ ሌንጂሶ ለሶማሌላንድ “የእንኳን ደስ አላችሁ” መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ባላንጣ ተደርጋ የምትወሰደው ግብጽ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቷ በኩል ዛሬ ምሽት ባወጣችው መግለጫ፤ እስራኤል ለሶማሌላንድ የሰጠችውን የሀገርነት እውቅና ተቃውማለች። ግብጽ መግለጫውን ያወጣችው፤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ባድር አብደልላቲ በጉዳዩ ላይ ከጅቡቲ እና ቱርክ አቻዎቻቸው ጋር በጉዳዩ ዙሪያ የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።  

ሶስቱ ሀገራት የእስራኤል ድርጊት የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚጥስ ነው” ማለታቸውን የጠቀሰው የግብጽ ውጭ ጉዳይ  መስሪያ ቤት፤ በጉዳዩ ላይ ከሞቃዲሾ ጎን እንደሚቆሙ ማሳወቃቸውንም አክሏል። እነዚሁ ሀገራት ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋራ የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት፤ በ“ጽኑ በማውገዝ” ለሶማሊያ አጋርነታቸውን ከገለጹ ሀገራት መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ለሶማሌላንድ ዕውቅና የምትሰጥ “የመጀመሪያዋ ሀገር ትሆናለች” የሚል ተስፋ ተጥሎባት የነበረችው አሜሪካ፤ የእስራኤልን ዕውቅና መስጠት ተከትሎ እስካሁን በጉዳዩ ላይ በይፋ አቋሟን አላሳወቀችም። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሶማሌላንድን በፕሮጀክት 2025 ሰነዳቸው ውስጥ ጭምር ማካተታቸውን ተከትሎ፤ ለራስ ገዝ አስተዳደሯ ዕውቅና ሊሰጡ እንደሚችሉ ለወራት ጭምጭምታዎች ሲናፈሱ ቆይተዋል። 

ምንም እንኳን እውቅና ስለመስጠት በአሜሪካ በኩል እስካሁን ምንም አይነት ይፋዊ እርምጃ ባይወሰድም፤ ሴናተር ቴድ ክሩዝን ጨምሮ በሪፐብሊካን ፓርቲ ውስጥ ያሉ ታዋቂ ሰዎች ለሶማሌላንድ እውቅና እንዲሰጥ ሲወተውቱ ነበር። ሶማሌላንድ ራሷን ከሶማሊያ ነጥላ ሉዓላዊ ሀገር መሆኗን ያወጀችው በግንቦት 1983 ዓ.ም ነበር።

የራስ ገዝ አስተዳደሯ የአፍሪካ ህብረት ይፋዊ እውቅና እንዲሰጣት እና በአባልነት እንደሚዘግባት ጥያቄ ካቀረበች 20 ዓመት ሞልቶታል። ይህን ጥያቄ ካቀረበች ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ፤ አጥብቃ ስትሻው የነበረውን ይፋዊ የሀገርነት እውቅና ከአፍሪካም ሆነ ከአሜሪካ ሳይሆን ከመካከለኛው ምስራቅ ለማግኘት በቅታለች። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)