ለአንድ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ የፕላስቲክ ምርቶችን (ፌስታል) ከአንድ ወር በኋላ መጠቀም የሚከለክለው አዋጅ የትግበራ ጊዜ እንዲራዘምላቸው ሱፐርማርኬቶች እና አምራቾች ጠየቁ። የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በበኩሉ አዋጁ ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድሞ የተሰጠው የስድስት ወራት የሽግግር ጊዜ እንደማይራዘም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል።
በግንቦት 2017 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ የጸደቀው ይህ አዋጅ፤ “የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድን” የሚመለከት ሲሆን ለ13 ዓመታት በስራ ላይ የቆየውን ነባር ህግ የተካ ነው። አዲሱ አዋጅ ከተዘጋጀባቸው ዓላማዎች አንዱ፤ “ለአካባቢ ብክለት የሚዳርጉ” እና “አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ምርቶች” በሥነ ምህዳር ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት መከላከል እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
አዲሱ አዋጅ “ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክ ማምረት፣ ለገበያ ማቅረብ፣ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት፣ መሸጥ፣ ማከማቸት ወይም መጠቀምን” ከልክሏል። “የፕላስቲክ ከረጢት” ማለት “አነስተኛ ጥግግት ያለው፣ በቀላሉ በስብሶ ከአፈር ጋር የማይዋሃድ እና ሌሎች ምርቶችን ለመያዝ የሚያገለግል” እንደሆነ በአዋጁ ላይ ተገልጿል።
ክልከላውን ተላልፈው በተገኙ አምራቾች እና ተገልጋዮች ላይ የህግ ተጠያቂነት የሚያስከትለው የእዚህ አዋጅ አፈጻጸም፤ በረቂቅ ደረጃ ለፓርላማ ከቀረበ ጊዜ አንስቶ ሲያነጋግር ቆይቷል። ስስ ፌስታሎችን በብዛት የሚጠቀሙ የንግድ መደብሮች፤ ለአንድ ጊዜ አገልግሎት የሚውሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን የሚተኩ “አማራጭ ምርቶች” “በገበያ ላይ እንደልብ አለመኖራቸው” አዋጁን በተቀመጠለት ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅፋት እንደሚሆን ያስረዳሉ።
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር ካሉ የንግድ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የኩዊንስ ሱፐር ማርኬት ዋና ስራ አስኪያጅ ሰሚራ ሸረፋ፤ አዋጁ መውጣቱን ተከትሎ ስስ ፌስታሎችን ላለመጠቀም የሚችሉትን ቢያደርጉም፤ እስካሁን “ምትክ ምርት” ማግኘት አለመቻላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ስራ አስኪያጇ ያለ ስስ ፌስታል አገልግሎት መስጠት ፈታኝ ነው ባይ ናቸው።
“ይህ አዋጅ ከመተግበሩ አስቀድመን ስስ ፌስታሎችን የሚያስቀሩ እና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆኑ ተኪ ምርቶችን ለመጠቀም ሞክረን ነበር። ነገር ግን ፌስታልን የሚተካ ምርት ማግኘት አልቻልንም” ሲሉ ወ/ሮ ሰሚራ ችግሩን አስረድተዋል። ድርጅታቸው በአዋጁ መሰረት አማራጭ የእቃ መያዣዎችን “ቢፈልግም”፤ “ቋሚ” እና “ለደንበኞች ተስማሚ” የሆነ ምርት ማግኘት እንዳልቻሉም አክለዋል።

አማራጭ ፍለጋ ከሀገር ውስጥ አምራቾች እስከ ውጭ ድርጅቶች ድረስ “በማነጋገር ላይ መሆናቸውን” ስራ አስኪያጇ አመልክተዋል። ስስ ፕላስቲኮችን የሚተካ እስኪገኝ “ከሶስት ጊዜ እና ከዚያ በላይ የሚያገለግሉ”፣ “በምርቶቹ ላይ የአምራቾቹ አድራሻ በግልጽ የተጻፈባቸው” ፌስታሎችን “እንድንጠቀም ቢፈቀድልን የተሻለ ነው” ሲሉም አማራጭ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል። ከፌስታል ጎን ለጎን ከጨርቅ የተሰሩ የዕቃ መያዣዎችን እየተጠቀሙ አማራጮችን ማለማመድ እንደሚቻልም ወ/ሮ ሰሚራ ጠቁመዋል።
ኩዊንስ ሱፐርማርኬት ፌስታልን ለሸማቾቹ የሚያቀርበው በነጻ መሆኑን የሚገልጹት ስራ አስኪያጇ፤ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅ መውጣት ምርቱን ለመግዛት የሚያወጡትን ወጪ እንደሚያስቀርላቸው በበጎ ጎን አንስተዋል። ድርጅቱ በስሩ ባሉት መደብሮች በዓመት “ስድስት ሚሊዮን ደንበኞችን” እንደሚያስተናግድ የሚናገሩት ስራ አስኪያጇ፤ ለአንድ ጊዜ አገልግሎት ለሚሰጥ ስስ ፌስታል ግዢ በዓመት እስከ 60 ሚሊዮን ብር ድረስ ወጪ እንደሚያደርግ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በ2002 ዓ.ም የተቋቋመው ኩዊንስ ሱፐርማርኬት፤ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ 13 ቅርንጫፎች አሉት። እንደ ኩዊንስ ሁሉ በመዲናይቱ የተለያዩ ቦታዎች ሸቀጣ ሸቀጦችን በማቅረብ ከሚታወቁ ትላልቅ የንግድ መደብሮች አንዱ የሆነው ሰንሲቲ ሱፐርማርኬት፤ ሸማቾች የሚገዟቸውን ምርቶች እንዲይዙበት አሁንም በዋነኛነት የሚያቀርበው ስስ ፌስታልን ነው።

የሰንሲቲ ሱፐርማርኬት ተቆጣጣሪ የሆኑት አቶ ሳሙኤል አቀበ፤ የአዋጁ መተግበሪያ ቀን ከመገባደዱ በፊት እጃቸው ላይ ያሉ የፌስታል ምርቶችን ለመጨረስ እየሞከሩ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “ከጥር መጨረሻ ቀናት ጀምሮ ፌስታል መጠቀም እንደማንችል እናውቃለን። ተጨማሪ የፌስታል ምርቶችን ከአከፋፋዮች መረከብ አቁመናል” ሲሉም አቶ ሳሙኤል አክለዋል።
“ለደንበኞቻችን አማራጭ ዕቃ መያዣ ምርት እስካሁን አልመረጥንም” የሚሉት የሱፐርማርኬቱ ተቆጣጣሪ፤ በአማራጭነት “ይህን ምርት ተረከቡን ብሎ እስካሁን ወደ እኛ የመጣ አምራችም የለም” ሲሉም አሁን ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል። አቶ ሳሙኤል ገበያ ላይ ባደረጉት ቅኝት፤ የሚስማማቸውን ተኪ ምርት “አልተመለከቱም”።
“የተወሰኑ ያየናቸው አሉ። ነገር ግን በአንድ ፍሬ 50 ብር እና ከዚያ በላይ የሆኑ ውድ ዋጋ ያላቸው ሆነውብናል” የሚሉት የሰን ሲቲ ሱፐርማርኬት ተቆጣጣሪ፤ ደንበኞቻቸውን ለአንድ ዕቃ መያዣ ከረጢት ይሄንን ያህል ዋጋ ማስከፈል ተገቢ እንዳልሆነ ያስረዳሉ። ከወረቀት የተሰሩ አማራጭ ዕቃ መያዣ ምርቶች “ጠንካራ እንዳልሆኑ” የሚገልጹት አቶ ሳሙኤል፤ ደንበኞች እነዚህን ምርቶች የመጠቀም “ፍላጎት እንደሌላቸውም” አመልክተዋል።

አቶ ሳሙኤል በአዋጁ መሰረት የቀረው የመሸጋገሪያ ጊዜ አጭር መሆኑን ጠቅሰው፤ “ምን እንደምናደርግ አላውቅም” ሲሉ በሁኔታው ግራ መጋባታቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ፕላስቲክ እና ጎማ አማራቾች ማህበር ሰብሳቢ አቶ በረከት ገብረህይወትም፤ አምራቾች ለአንድ ጊዜ አገልግሎት የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶችን ወደ ተኪ እና ሌሎች ምርቶች ለመቀየር የተሰጣቸው የስድስት ወራት ጊዜ “በጣም አጭር እና በቂ አይደለም” ሲሉ ሃሳቡን ይጋራሉ።
አምራቾች ጤናማ የምርት ሽግግር ለማድረግ በትንሹ “ከሶስት እስከ አምስት ዓመታት እንደሚያስፈልጋቸው” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት አቶ በረከት፤ “የፕላስቲክ ማምረቻዎችን በቀላሉ ወደ ሌሎች ምርቶች ማሸጋገር አይቻልም። ተኪ ምርቶችን ለማምረት የግድ አዲስ ኢንቨስትመንት ይፈልጋል” ሲሉ የጊዜውን አጭርነት ያስረዳሉ።
ለሽግግር የተሰጠው ጊዜ እና አዋጁ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ የሚወሰደው እርምጃ፤ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰራተኞችን “ከስራ ውጪ የሚያደርግ ነው” ሲሉ የማህበሩ ሰብሳቢ ይተቻሉ። ይህ አካሄድ አምራቾችን “ለኪሳራ”፣ የሀገርን ኢኮኖሚ ደግሞ “ለከፋ ጉዳት” የሚዳርግ እንደሆነም አቶ በረከት አጽንኦት ይሰጣሉ።

ይህንን ቅሬታ አንስተን ምላሽ የጠየቅናቸው የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ኮሙንኬሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ ተሾመ አቡኔ፤ ፌስታል አምራች ድርጅቶች ወደ ተኪ ምርቶች እንዲሸጋገሩ የተሰጣቸው የስድስት ወራት የሽግግር ጊዜ “በቂ እንደሆነ” ገልጸዋል። “ከዓመታት በፊት በኬንያ እና ሩዋንዳ የታገዱ የፕላስቲክ ማምረቻ ማሽኖች ወደ ኢትዮጵያ ተጓጉዘው ጥራታቸውን ያልጠበቁ እና ለጤና ጎጂ የሆኑ ምርቶችን በማምረት ላይ መሆናቸውን እናውቃለን” ሲሉም አቶ ተሾመ አክለዋል።
አዋጁ ለአንድ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ የፕላስቲክ ምርቶችን “መጠቀም፣ ማምረት እና ማዘዋወር እንደማይቻል” ከመግለጹ ባለፈ አማራጭ “አላቀረበም”፤ በአማራጭነት የሚታሰቡትም ቢሆኑ “ዋጋቸው ውድ ነው” የሚሉ ቅሬታዎችን በተመለከተም አቶ ተሾመ ምላሽ ሰጥተዋል። በምላሻቸውም “እንደ አቡጀዴ ያሉ ከጨርቅ የሚሰሩ ከረጢቶችን ማግኘት በኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሊሆን አይችልም” ብለዋል።
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የኮሙንኬሽን ስራ አስፈጻሚ “አማራጭ እና ርካሽ ምርት አጣን በሚል አዋጁን አለመፈጸም አይቻልም” ሲሉ ከህግ ተጠያቂነት መዳን እንደማይቻል አስገንዝበዋል። የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅ ከጥር 23፤ 2018 ጀምሮ “አስገዳጅ ሕግ” እንደሚሆንም አቶ ተሾመ አጽንኦት ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































