አሜሪካ ለሶማሌላንድ ዕውቅና የምትሰጥ “የመጀመሪያዋ ሀገር ትሆናለች” የሚል ተስፋ እንዳላቸው የራስ ገዝ አስተዳደሯ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዲላሒ ተናገሩ። አዲሱ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፤ ሶማሊያ “ግዛቴ ናት” ለምትላት ሶማሌላንድ ዕውቅና ከሰጠ ሌሎች ሀገራት ይከተላሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
አዲሱ የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ይህን ያሉት፤ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 4፤ 2017 በዱባይ በተካሄደ የዓለም የመንግስታት ጉባኤ ውይይት ላይ ነው። አብዲራህማን ኢሮ በሚል ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት አዲሱ ፕሬዝዳንት የዛሬ ሶስት ወር ገደማ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው አስቀድሞ፤ ለሶማሌላንድ ዕውቅና በመስጠት ቀዳሚዋ ሀገር ትሆናለች የሚል ተስፋ የተጣለው በኢትዮጵያ ላይ ነበር።
ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር “የአጋርነት እና የትብብር የመግባቢያ ስምምነት” የተፈራረሙት የቀድሞው የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሒ አብዲ፤ ውሉ ተግባራዊ ሲሆን “ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ ዕውቅና እንደምትሰጥ” በይፋ መናገራቸው ለዚህ ተስፋ በማስረጃነት ሲጠቀስ ቆይቷል። በምርጫ አሸንፈው የሶማሌላንድን ፕሬዝዳንት መንበር የተረከቡት አብዲራህማን ኢሮ፤ ለመግባቢያ ስምምነቱ ድጋፋቸውን ማሳየታቸውም አይዘነጋም።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ውጥረት ፈጥሮ የቆየው ይህ የመግባቢያ ስምምነት፤ ሁለቱ ሀገራት በቱርክ ፕሬዝዳንት አሸማጋይነት በአንካራ ከተማ ካደረጉት ስምምነት በኋላ እውን የመሆኑ ጉዳይ አጠራጥሯል። “የአንካራ ቃል ኪዳን” የሚል ስያሜ ያለው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ስምምነት፤ “አንዳቸው የሌላውን ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ነጻነት እና የግዛት አንድነት ለማክበር ቁርጠኝነታቸውን” ያረጋገጡበት ነው።
የሶማሌላንድ ልሂቃን ከፍተኛ ተስፋ የሰነቁበት የኢትዮጵያ የመግባቢያ ስምምነት ወደ ተግባር ሳይቀየር ቢዘገየም፤ የራስ ገዝ አስተዳደሯ አጥብቃ የምትሻውን ዕውቅና ከአሜሪካ ልታገኝ እንደምትችል ለትራምፕ አስተዳደር ቅርበት ያለው ተቋም ከወር በፊት ጥቆማ ሰጥቶ ነበር። አዲሱ የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት በዛሬው የዱባይ ጉባኤ ላይ ይህንኑ የሚያጠናክር አስተያየት አንጸባርቀዋል።
ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ኢሮ የተካፈሉበትን የጉባኤው ክፍል የመራው የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ጆን ዴፍቶሪዮስ ጊዜው “ለሶማሌላንድ ወሳኝ ወቅት” እንደሆነ ተናግሯል። የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር “ለሶማሌላንድ እውቅና ስለመስጠት እየተነጋገረ ይገኛል” ያለው ጋዜጠኛ ጆን ዴፍቶሪዮስ፤ ከጉዳዩ ጋር “የተያያዙ ቅድመ-ሁኔታዎች” ምንነት እና ሶማሌላንድ በምላሹ ምን መስጠት ሊኖርባት እንደሚችል ጥያቄ አቅርቧል።

የሶማሌላንዱ ፕሬዝዳንት በምላሻቸው፤ በጉዳዩ ላይ ከአሜሪካ መንግስት ጋር የተደረገ ንግግር ወይም የተደረሰ ስምምነት ስለ መኖሩ በቀጥታ ማረጋገጫ አልሰጡም። ይሁንና በኤደን ባህረ ሰላጤ 850 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የባህር ጠረፍ ያላት ሶማሌላንድ፤ “በስትራቴጂክ አቀማመጧ ተፈላጊ ልትሆን እንደምትችል” እምነታቸውን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ኢሮ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሶቭየት ህብረት እና አሜሪካ የበርበራ ወደብን በተለያየ ወቅት ይጠቀሙበት እንደነበር ለዚህ በማሳያነት አንስተዋል። በግንቦት 1983 ዓ.ም. ከሶማሊያ በመነጠል ነጻነቷን ያወጀችው ሶማሌላንድ፤ ዕውቅና ባታገኝም ራሷን የቻለች ምርጫ የምታካሄድ እና ስልጣን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚሸጋገርባት “ዴሞክራሲያዊት ሀገር” መሆኗን ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ምላሻቸው ላይ ተናግረዋል።
ከአሜሪካ፣ ከታላቋ ብሪታኒያ እና ከሌሎች ሀገራት ጋር “ጥሩ ወዳጅነት አለን” ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሮ፤ “ምን አልባት ዩናይትድ ስቴትስ ለሶማሌላንድ ዕውቅና የምትሰጥ የመጀመሪያዋ ሀገር ትሆናለች” ሲሉ በፈገግታ ተሞልተው ለጋዜጠኛው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። በዱባዩ ውይይት ከሶማሌላንድ ዕውቅና በተጨማሪ ኢትዮጵያ የምትገለገልበት የበርበራ ወደብ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶታል።

በቀይ ባህር ላይ ከሚገኙ ሁሉ በዕድሜ አንጋፋ እንደሆነ የሚነገርለት የበርበራ ወደብ፤ በሶማሌላንድ መንግስት እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ንብረት በሆነው “ዲፒ ወርልድ ኩባንያ” የማስፋፊያ ግንባታ የተደረገለት የባህር በር ለሌላቸው የአፍሪካ ሀገራት ታስቦ ነበር። ይሁንና አዲሱ የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት የበርበራ ወደ ጉዳይ ሲነሳ “ዋና ደንበኛችን፣ ጎረቤታችን እና ወዳጃችን” ሲሉ የጠሩት ሀገር ኢትዮጵያን ነው።
የበርበራ ወደብን ለመጠቀም የሚያስፈልገውን “የትራንዚት የንግድ ስምምነት” (transit trade agreement) እስከተያዘው የፈረንጆች አመት መጨረሻ ድረስ የማጠናቀቅ ዕቅድ እንዳላቸው ፕሬዝዳንቱ ለጉባኤው ተሳታፊዎች አስረድተዋል። ወደቡን በ400 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያስፋፋው የዲፒ ወርልድ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሱልጣን አህመድ ቢን ሱላዬም፤ “በርበራ ማንኛውንም አይነት መርከብ ማስተናገድ ይችላል። አስፈላጊ ከሆነ ሊስፋፋ የሚችልበት ምዕራፍ አለ” ሲሉ ተደምጠዋል።
“ዲፒ ወርልድ” በበርበራ ላይ መዋዕለ ንዋዩን ያፈሰሰው፤ የኢትዮጵያ የወደብ ፍላጎትን የተመለከተ ጥናት ካከናወነ በኋላ እንደሆነ በዛሬው ውይይት ላይ ተጠቅሷል። በዚህ ጥናት መሰረት “ኢትዮጵያ ዕድገቷ የሚጠይቀውን ለማሟላት ቢያንስ አምስት ወደቦች ያስፈልጓታል” የሚል ድምዳሜ ላይ ኩባንያው መድረሱን ሱልጣን አህመድ ቢን ሱላዬም ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያ ዕድገቷ የሚጠይቀውን ለማሟላት ቢያንስ አምስት ወደቦች ያስፈልጓታል”
– ሱልጣን አህመድ ቢን ሱላዬም፤ የዲፒ ወርልድ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ
ግዙፉ “ዲፒ ወርልድ” ኩባንያ በመላው ዓለም 80 በሚደርሱ ሀገሮች የወደብ አስተዳደር እና የካርጎ ማጓጓዝ የመሳሰሉ አገልግሎቶችን በአሁኑ ወቅት እየሰጠ የሚገኝ ነው። ኩባንያው የሶማሌላንድ መንግስት ባቀረበው መሬት ላይ፤ በተለይ በኢትዮጵያ ገበያ ያተኮሩ ፋብሪካዎች እየገነባ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)