እስራኤል ከትላንት በስቲያ አርብ ለራስ ገዝ አስተዳደሯ ሶማሌላንድ የሰጠችው የነጻ ሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና በኢትዮጵያ ላይ የሚኖረውን አንድምታ በተመለከተ ሁለት የፖለቲካ ምሁራን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የመጀመሪያው ኢትዮጵያ ከአረቡ ዓለም ጋር ባላት ግንኙነት ዙሪያ በርካታ ጥናቶችን በማድረግ የሚታወቁት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶ/ር ዮናስ አሽኔ ናቸው።
ፕሮፌሰር አደም የእስራኤል እርምጃ ለኢትዮጵያ አዎንታዊ ተጽእኖ እንዳለው ይገልጻሉ። ምሁሩ የእርምጃውን ተጽእኖ የሚያስረዱት የኢትዮጵያ ባላንጣ እንደሆነች ከሚያነሷት ከግብፅ አንጻር በዋናነት በመቃኘት ነው።
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የዛሬ ሁለት ዓመት “የአጋርነት እና የትብብር ስምምነት” መፈራረሟ፤ “ግብፅ ወደ ሶማሊያ እንድትመጣ “ዋነኛው ምክንያት” እንደነበር ፕሮፌሰር አደም ያስታውሳሉ። የሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር “በሰላም ማስከበር ስም” ወደ ሶማሊያ መምጣቷ “ከቅንነት የመነጨ አይደለም” ብለው የሚያምኑት ምሁሩ፤ የግብጽ ተሳትፎ በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የምታደርገው ጥረት አንዱ አካል እንደሆነ ያስረዳሉ።
ግብጽ በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ውስጥ የሚሳተፉ አምስት ሺህ ወታደሮችን ለማወጣት ቃል መግባቷ ይታወሳል። ሀገሪቱ ከዚህ ተልዕኮ ሌላ፤ ተጨማሪ አምስት ሺህ ወታደሮችን በሶማሊያ ለማሰማራት አቅዳለች። ግብፅ በሶማሊያም ሆነ በኤርትራ እና በጅቡቲ በኩል እየሞከረች ያለችው፤ ኢትዮጵያን “ለማስጨነቅ” እና “ድክመቶቿን ለመጠቀም” እንደሆነ ፕሮፌሰር አደም ያስረዳሉ።
የእስራኤል ወደ አፍሪካ ቀንድ መምጣት ሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌሎች ፍላጎቶቿን ማሳኪያ መንገድ የምታገኝበት እንደሆነ የሚገልጹት ምሁሩ፤ ይህ ለግብጽ ትልቅ “ኪሳራ” እንደሆነ ይገልጻሉ። እስራኤል ለሶማሌላንድ እውቅና መስጠቷ “ለግብፅ ትልቅ የዲፕሎማሲ እና ፖለቲካ ክስረት ነው” የሚሉት ፕሮፌሰር አደም፤ ግብፆች ይህን መቀበል እንደሚቸገሩ ያነሳሉ።
በእርግጥም የከትላንት ወዲያው የእስራኤል እርምጃ ግብፅን አስቆጥቷል። የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደልላቲ የእስራኤልን ውሳኔ ተከትሎ ከጅቡቲ እና ቱርክ አቻቸው ጋር ወዲያውኑ ነበር የስልክ ውይይት ያደረጉት። ከዚህ ውይይት በኋላ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቷ በኩል መግለጫ ያወጣችው ግብጽ የእስራኤልን እርምጃ ኮንናለች።
የስልክ ውይይቱን ያካሄዱት ሶስቱ ሀገራት “የእስራኤል ድርጊት የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚጥስ ነው” ማለታቸውንም ግብጽ በትላንቱ መግለጫዋ አስታውቃለች። ግብጾች ሁሌም ቢሆን ለችግራቸው “ኢትዮጵያን ተጠያቂ ማድረግ ይፈልጋሉ” የሚሉት ፕሮፌሰር አደም፤ የሶማሌላንድ እውቅናን ተከትሎም የሆነው ተመሳሳይ እንደሆነ ያብራራሉ።
ግብፆች ከሰሞኑ “የኢትዮጵያ እና እስራኤል ግንኙነት በየቀኑ እየተጠናከረ ነው”፤ “የኢትዮጵያ ጦር በጋዛ ሊሰማራ ነው” ሲሉ መቆየታቸውን ፕሮፌሰር አደም ይጠቅሳሉ። የሶማሌላንድ እውቅና ጉዳይም “ኢትዮጵያ የጀመረችውን ነው እስራኤል እየጨረሰች ያለችው” በማለት ላይ መሆናቸውን ያክላሉ።
ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ በታህሳስ 2016 ዓ.ም “የአጋርነት እና የትብብር የመግባቢያ ስምምነት” ከተፈራረሙ በኋላ፤ የቀድሞው የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሒ አብዲ ስምምነቱ ተግባራዊ ሲደረግ ኢትዮጵያ ለሶማሌንድ እውቅና እንደምትሰጥ መናገራቸው ይታወሳል። ይህን ስምምነት “ሶማሌላንድ የግዛቴ አካል ነች” የምትለው ሶማሊያ አጥብቃ ማውገዟን ተከትሎ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያው ግንኙነት ሻክሮ ቆይቷል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ተፈጥሮ የቆየው ውጥረት የረገበው፤ ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር በቱርክ አንካራ ከተማ ከስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ነበር። በቱርክ አሸማጋይነት በተካሄደው በዚህ ስምምነት ሁለቱ ሀገራት “ልዩነቶቻቸውን እና አወዛጋቢ ጉዳዮችን ወደ ኋላ ለመተው” እና “ትብብር ለማበጀት” መስማማታቸው ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር ዮናስ አሽኔ፤ የአንካራው ስምምነት “ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ አቋሟ የተመለሰችበት” እና አስቀድሞ በሶማሌላንድ እና በኢትዮጵያ መካከል “የተደረገውን ስምምነት የሚቃረን ነው” የሚል መረዳት አላቸው። “ከዚያ በኋላ ስለዚያ ስምምነት ሰምተን አናውቅም። የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ግንኙነት እየተሻሻለ ቀጥሏል። ከአንካራ በኋላ ሁለቱ ሀገሮች መሰረታዊ በሆኑ መርሆች ላይ የተስማሙ ይመስለኛል” ይላሉ።
ለዚህ ተጠቃሽ የሚሆነው ከአንካራው ስምምነት በኋላ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነታቸውን “ወደነበረበት ለመመለስ” መስማማታቸው ነው። የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መሪዎች ባለፈው ዓመት ጥር ወር በአዲስ አበባ ከተገናኙ በኋላ፤ በሁለቱም ሀገራት “የተሟላ ዲፕሎማሲያዊ ውክልና” እንዲኖር በማድረግ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት “ለማጠናከር” መስማማታቸውን አስታውቀው ነበር።
ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ የትብብር ስምምነት ጉዳይ ለጊዜው “ተከድኖ ይብሰል” ሆኖ ቆይቷል። ሶማሊያ “ሰሜናዊ ክልሌ ናት” የምትላት የሶማሌላንድ እውቅና ጉዳይም እንዲሁ ጋብ ብሎ ቆይቶ ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ ነበር እስራኤል ላለፉት 34 ዓመታት ራሷን ከሶማሊያ ነጥላ ለቆየችው ለሶማሌላንድ፤ የነጻ እና ሉዓላዊ ሀገርነት ዕውቅና መስጠቷን በድንገት ይፋ ያደረገችው።
ከትላንት በስቲያ አርብ ታኅሣሥ 17፤ 2018 ምሽት የተሰማውን ይህን ውሳኔ ተከትሎ፤ የሶማሊያ ካቢኔ ካካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ የሀገሪቱ መንግስት ባወጣው መግለጫ እርምጃውን አጥብቆ ተቃውሟል። ሶማሊያ በዚሁ መግለጫ የእስራኤል ውሳኔ “ሆን ተብሎ በሉዓላዊነቴ ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው” ስትል አውግዛዋለች።
ሶማሊያ “አንድነቷ የማይከፋፈል” ሉዓላዊ ሀገር መሆኗን እና የትኛውም የውጭ አካል አንድነቷን ወይም ግዛቷን የመቀየር “ስልጣን እንደሌለው” የትላንቱ መግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል። ከሶማሊያ አንድነት፣ አስተዳደር እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሕጋዊ፣ ሕገ-መንግሥታዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት “የሶማሌ ሕዝብ ብቸኛ መብቶች ናቸው” ሲልም የሀገሪቱ መንግስት በመግለጫው አስገንዝቧል።

የእዚህ አይነት “ሕገ-ወጥ ድርጊቶች” የቀጠናውን ሰላም እና መረጋጋት በእጅጉ እንደሚያናጉ፣ በአፍሪካ ቀንድ፣ በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና በአጠቃላይ ቀጣናው ላይ ያለውን የፖለቲካ እና የጸጥታ ውጥረቶችን “እንደሚያባብሱ” የሶማሊያ መንግስት አስጠንቅቋል። የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ዶ/ር ዮናስ እስራኤል ለሶማሌላንድ የሰጠችው የነጻ ሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን “ለሁለት ለሶስት የሚከፋፍል ይመስላል” ሲሉ በቀጠናው ላይ ያለውን ተጽዕኖ ያስረዳሉ።
እስራኤል በአካባቢው የራሷን ፍላጎት ለማሳካት የምታደርገው ጥረት እና ከእስራኤል ተቃራኒ የሚቆሙ ሀገራትም የራሳቸውን ተጽእኖ ለማሳረፍ የሚያደርጉት ፉክክር፤ “በአፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ እውቅና ይሰጠን” የሚሉ “ትንንሽ ተገንጣይ ሀገራት እንዲበራከቱ ሊያበረታታ እንደሚችል” መላምታቸውን ያስቀምጣሉ። ፕሮፌሰር አደም “የቀይ ባህር ደህንነት የተናጋው የዓለማችን ሀያላን ሀገራት ወደ አካባቢው ስለመጡ ብቻ አይደለም” ባይ ናቸው።
“ቀይ ባህር ሞገሱን ያጣው ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር በመራቋ ምክንያት ነው” የሚሉት ፕሮፌሰር አደም፤ “ቀጠናው እንዲረጋጋ” ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት እንዳለባት ይገልጻሉ። የመካከለኛው ምስራቅ ሁለንተናዊ ደህንነት የሚረጋገጠው ቀይ ባህር ሰላማዊ ሲሆን በመሆኑ ኢትዮጵያ “የግድ ወደ ቀድሞ የቀይ ባህር ቦታዋ ለመመለስ የጀመረችውን የዲፕሎማሲ ጥረት መቀጠል አለባት” ሲሉም ይመክራሉ፡፡

የእስራኤል ለሶማሌላንድ እውቅና መስጠት ለኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት መሳካት “አንድ አዎንታዊ እርምጃ” እንደሆነም ፕሮፌሰር አደም ያምናሉ። የቀይ ባህር ደህንነት ተጠብቆ የንግድ መርከቦች በሰላም እንዲንቀሳቀሱ ከማስቻል አንጻር፤ ኢትዮጵያ ያላትን አቅም እና ቁርጠኝነት በማስረዳት የማሳመን ስራ መስራት እንዳለባት ምሁሩ ምክረ ሃሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር “በጥንቃቄ የተሞላ” እና “ሚዛኑን የጠበቀ” ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መከተል ላይ ማተኮር እንደሚገባት ምሁሩ ያስገነዝባሉ፡፡ ዶ/ር ዮናስም ከዚህ ጋር የተመሳሳለ ሃሳብ አላቸው።
የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ እስራኤል ከአረቡ ሀገራት እና ከአፍሪካ ጋር አላት ባሉት “ያልተለሳለሰ” ግንኙነት ምክንያት፤ ኢትዮጵያ “በጣም ጥንቃቄ” ያለው ጉዞ “መራመድ እንዳለባት” ያሳስባሉ። የእስራኤል መምጣት “ለኢትዮጵያ የባሕር በር ተደራሽነት ፋይዳ ቢኖረውም፤ ቀጠናው ላይ በሚያመጣው ተጽዕኖ ግጭትና ጦርነት ሊያስከትል ስለሚችል ኢትዮጵያ ጉዞዋን እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ማድረግ አለባት” ሲሉም ይመክራሉ።

ዶ/ር ዮናስ ኢትዮጵያ በእስራኤል ላይ ያላትን አቋም ወዲያውኑ አለማንፀባረቋ እና በዚያው መቀጠሏ፤ “የተሻለ መስመር” እየተከተለች ነው ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ሀገሪቱ ይህንን ጉዳይ መመልከት የሚገባት “በጥንቃቄ” እና “ጊዜ ተወስዶ ነው” ሲሉም በድጋሚ አጽንኦት ይሰጣሉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው መምህር ሀገሪቱ ይህንን አካሄድ መከተል አለባት ቢሉም፤ ኢትዮጵያ ከአረቡ ዓለም ጋር ባላት ግንኙነት ላይ ጥናቶችን ያደረጉት ፕሮፌሰር አደም ግን ከዚህ የተቃረነ አቋም ነው ያላቸው። ፕሮፌሰር አደም፤ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የነጻ ሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና በመስጠት “በእስራኤል ልትቀደም እና ተከታይ ሀገር ልትሆን አይገባም ነበር” ባይ ናቸው።
ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ የሀገርነት እውቅና ልትሰጥ የሚገባው “የራሷን ጥቅም ብቻ በማሰብ” እንደሆነም ይገልጻሉ። “ከእኛ በፊት ሌሎችም ሀገራት [ከሶማሌላንድ ጋር] በጋራ እየሰሩ ቆይተዋል፡፡ አሁን ደግሞ እስራኤል እውቅና ሰጥታለች፡፡ ሌሎቹ እውቅና የሰጡትን እኛም ብንሰጥ ችግሩ አይታየኝም፡፡ እኛም እውቅና ብንሰጥ የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ” ሲሉም በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም አጋርተዋል

ከእስራኤል እውቅና መስጠት ጀርባ “በእነ አሜሪካ የሚመራው” የምዕራቡ ዓለም ሀገራት እንዳሉ እንደሚያምኑ የገለጹት ፕሮፌሰር አደም፤ እስራኤል በራሷ ብቻ ወስና ለሶማሌላንድ እውቅና ልትሰጥ እንደማትችል ይሟገታሉ። ኢትዮጵያ ከዚህ ጋር በተያያዘ የመካከለኛውን ምስራቅ እንቅስቃሴዎች መከታተል እና ለዚያ የሚመጥን የዲፕሎማሲ ዝግጁነት ማድረግ ላይ ትኩረቷን ማድረግ እንደሚገባትም ያሳስባሉ።
ዶ/ር ዮናስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ካላት ቁመና እና ታሪክ አንጻር በዚህ ጉዳይ ላይ የምታራምደው አቋም “ከአፍሪካ መንፈስ መውጣት የለበትም” የሚል እምነት አላቸው። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ኅብረት የመመስረቻ መርሆች እና ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ባህል አንጻር “በተቻለ መጠን” የሌሎች ሀገሮች ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ውስጥ “ጣልቃ አለመግባት” የሚል የታሪክ “ሸክም እና ኃላፊነት” እንዳለባትም ምሁሩ ያስረዳሉ።
“ኢትዮጵያ ምን አይነት አቋም መውሰድ አለብኝ የሚለው ብቻ ራሱ ከባድ ቦታ ላይ ያስቀምጣታል” የሚሉት ዶ/ር ዮናስ፤ “ ‘ተከትዬ እውቅናውን ልስጥ’ ማለት ከኢትዮጵያ ቁመና፣ የታሪክ ኃላፊነት እና የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫነት እንዲሁም ከራሷም የረጅም ዓመታት መርሆች አንጻር የሚያኬድ አይደለም” ሲሉ ያብራራሉ።

የአፍሪካ ኅብረት ከትላንት በስቲያ አርብ ምሽት ባወጣው መግለጫ እስራኤል ለሶማሌላንድ የሰጠችውን የነጻ ሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና እንደማይቀበለው አስታውቋል። የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ የሱፍ፣ ለሶማሊላንድ የሚሰጥ ማንኛውንም እውቅና “ውድቅ በማድረግ”፤ የአፍሪካ ኅብረት ለሶማሊያ አንድነት እና ሉዓላዊነት ያለውን የማያወላውል ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ከሶማሌላንድ ጋር በተያያዙ ያሉ ለውጦች “በጥልቅ እንዳሳስሰባቸው” የገለጹት የኮሚሽኑ ሊቀመንበር፤ በአፍሪካ ኅብረት ማቋቋሚያ ሕግ ውስጥ በተደነገጉ መርሆዎች መሰረት ኅብረቱ የሀገራት ሉዓላዊነት መከበር እንዳለበት የፀና አቋም እንዳለው ገልጸዋል። ሶማሌላንድ የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ አካል መሆኗን በመግለጫቸው የጠቀሱት የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ፤ የሶማሊያን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አሃድነት ለመናድ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ ከአፍሪካ ኅብረት መሰረታዊ መርሆች ጋር የሚቃረን እና “በአህጉሪቱ ሰላም እና መረጋጋት ላይ ትልቅ አንድምታ ያለው አደገኛ ምሳሌ ሊሆን ይችላል” ሲሉ አውግዘዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ከአፍሪካ ኅብረት አቋም ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው መግለጫ በትላንትናው ዕለት አውጥቷል። የአረብ ሊግም እንዲሁ የእስራኤልን ውሳኔ በመቃወም አቋሙን አሳውቋል። እንደዚህ ውግዘት የበዛበት የሶማሌላንድ እውቅና ጉዳይ፤ ለኢትዮጵያ “ከባድ ፈተና” እንደሆነ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ “እውቅና አልሰጥምም ይሁን እውቅና እሰጣለሁ” ማለት “ከባድ” ሁኔታ ውስጥ ይከታታል ሲሉ ዶ/ር ዮናስ ይገልጻሉ። በሰሞነኛው ሁኔታ ከሚፈተኑት አንዱ ኢትዮጵያ “ከሶማሌላንድ ጋር ያላት ወዳጅነት” እንደሆነም ያክላሉ። በትላንቱ የእስራኤል ውሳኔ ደስታቸውን አደባባይ በመውጣት የገለጹት የሶማሌላንድ ሰዎች ግን በቅርቡ ሌሎች ሀገራትም እውቅና ይሰጡናል በሚል ተስፋ ወደ አካባቢው ሀገራት ማማተራቸውን ቀጥለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































