የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፤ “ለታክስ”፣ “ለቀረጥ” እና “ለአካባቢ ልማት” በሚል ሽፋን “በየሰፈሩ እና በመንገድ ዳር የተቋቋሙ” ህገ ወጥ ኬላዎች ሙሉ በሙሉ እንዲነሱ ውሳኔ አስተላለፈ። በክልሉ ተግባራቸውን የሚቀጥሉ ኬላዎች፤ “የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል” እና “ለጸጥታ ስራ አጋዥነት” በክልሉ መንግስት ወይም በፌዴራል አካል የተፈቀዱ ብቻ እንደሆኑ ገልጿል።
ክልሉ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፤ በየአካባቢው የተቋቋሙ ኬላዎች በክልሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ “ከፍተኛ ጫና”በማሳደራቸው እንደሆነ አስታውቋል። የክልሉ መንግስት ዛሬ አርብ ህዳር 5፤ 2018 ባወጣው መግለጫ ህገ ወጥ ኬላዎች ምርት “በነጻነት እና በተቀላጠፈ ሁኔታ ለገበያ እንዳይቀርብ” በማድረግ፤ ዜጎች በስራቸው ልክ እንዳይጠቀሙ “እንቅፋት ሆነዋል” ብሏል።
በየአካባቢው ኬላዎችን ማቋቋም “ኢኮኖሚን የሚያዳክም አሰራር” መሆኑን የገለጸው ክልሉ፤ ይህንን “ሙሉ በሙሉ ለማስቆም” የተላለፈውን ውሳኔ ተቀብሎ ወደ ተግባር የማይለውጥ ማንኛውም የመንግሥት መዋቅር፣ የስራ ኃላፊ ወይም አካል “ተጠያቂነቱን ይወስዳል” ሲል በመግለጫው አስጠንቅቋል። ውሳኔውን ለማስፈጸም፤ ክልሉ “አስፈላጊ” እና “የማያዳግም” ያለውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ከሌሎች የመንግስት ተቋማት ጋር በመሆን ባለፈው ዓመት ባደረገው ጥናት፤ በኢትዮጵያ የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎችን ሳይጨምር 297 የሚሆኑ ህገወጥ ኬላዎች እንዳሉ ይፋ አድርጎ ነበር። ኮሚሽኑ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ለፓርላማ ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት፤ እነዚህ ህገ ወጥ ኬላዎች፤ በህብረተሰቡ እንቅስቃሴ፣ በገቢ እቃዎች እና በወጪ ምርቶች ላይ “ተጽዕኖ” መፍጠራቸውን መግለጹ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)


































