– የወላይታ ጉዳይ ወደፊት ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሏል
– ጌዲኦ “ልዩ ዞን” እንዲሆን ከውሳኔ ላይ ተደርሷል
በተስፋለም ወልደየስ
በህዝበ ውሳኔ ክልል መሆኑ የተረጋገጠው የሲዳማ ዞንን ጨምሮ የደቡብ ክልልን በአራት የሚከፍለው አዲስ አወቃቀር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲተላለፍ ከስምምነት ላይ መደረሱን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ውሳኔው የተላለፈው የደቡብ ክልል የዞን እና የልዩ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 2፤ 2012 ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ ነው ተብሏል።
በስብሰባው የተሳተፉ አንድ አመራር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት በዛሬው ስብሰባ ውሳኔ ላይ ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች ከተቋጩ በኋላ አዲሱ አወቃቀር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይላካል። ምክር ቤቱ አዲሱን አወቃቀር በተቀበለ በ30 ቀናት ውስጥ ከሕገ መንግስቱ ጋር አገናዝቦ ምላሽ እንዲሰጥ ቀነ ገደብ ተቀምጧልም ብለዋል።
አምስት ሰዓት ገደማ በፈጀው በዛሬው ስብሰባ ላይ የደቡብ ክልልን መልሶ መዋቀርን የተመለከቱ የተለያዩ ጥናቶች መቅረባቸውን አመራሩ ገልጸዋል። በደቡብ ክልል የተነሱ የክልልነት ጥያቄዎች “በሳይንሳዊ ጥናት” እንዲመልስ በክልሉ የተቋቋመው የምሁራን ቡድን ያዘጋጀው ሰነድ በዛሬው ስብሰባ ላይ መቅረቡን ምንጩ ገልጸዋል።
የምሁራን በድኑ ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠት ሶስት መፍትሔዎችን በአማራጭነት ማቅረቡ ቀደም ሲል ተገልጾ ነበር። ከመፍትሔዎቹ መካከል ክልሉን ከሁለት እስከ አምስት ቦታዎች በመክፈል መልሶ ማደራጀት የሚለው ይገኝበታል።
በዛሬው ስብሰባ ቀረበ የተባለው ሌላኛው ሰነድ “የሰላም አምባሳደሮች” በሚል ስያሜ የተቋቋመው ቡድን የጥናት ውጤት ነው። በቀድሞው የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ የሚመራው ይህ ቡድን የደቡብ ክልልን አራት ቦታ የሚከፍል ምክረ ሃሳብ ማቅረቡ ሲነገር ሰንብቷል።
ሰማንያ አባላትን የያዘው ይህ ቡድን ያዘጋጀው ምክረ ሃሳብ፤ በግንቦት ወር መጀመሪያ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሀፈት ቤት ለውይይት በቀረበ ወቅት፤ በተወሰኑ ብሔሮች ተወካዮች ቅሬታ በማስነሳቱ፤ በክልሉ ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተጨማሪ ውይይቶች እንዲደረጉ ምክንያት ሆኖ ነበር።
ከውይይቶቹ የተገኙ ግብዓቶች ተካተውበታል የተባለው እና በዛሬው ስብሰባ የቀረበው ምክረ ሃሳብ የደቡብ ክልልን ለሶስት የሚከፍል እንደሆነ የስብሰባው ተሳታፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። በዛሬው ስብሰባ ወደፊት የሚቋቋሙት ክልሎች ስያሜም ሆነ ሌሎች ዝርዝር ነገሮች አለመነሳታቸውን የሚናገሩት የስብሰባው ተሳታፊ ሆኖም የትኛው ዞን እና ልዩ ወረዳ፣ በየትኛው ክልል እንደተካተተ ይፋ መደረጉን ገልጸዋል።
በተለምዶ “ምዕራብ ዞን” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ያሉ ሸካ፣ ቤንች፣ ማጂ፣ ከፋ እና ዳውሮ ዞኖች በአንድ ክልል ስር እንዲሆኑ በምክረ ሀሳቡ ላይ ቀርቧል ተብሏል። “ማዕከላዊ ዞን” በመባል በሚታወቀው አካባቢ ያሉት የጉራጌ፣ ስልጤ፣ ሀድያ፣ ከምባታ፣ ሀላባ ዞኖች እና የም ልዩ ወረዳ በጋራ ሆነው ሁለተኛ ክልል እንዲመሰርቱ በምክረ ሀሳቡ መቀመጡ ታውቋል።
አዲስ ከሚቋቋሙት ክልሎች “ሰፋ ያለ ቦታ የሚያካልል ነው” የተባለለት “ኦሞቲክ” በሚል መጠሪያ የሚታወቀው አካባቢ ነው። በዚህ አካባቢ የሚገኙት የጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ደራሼ፣ ቡርጂ፣ አማሮ እና ኮንሶ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል እንዲጠቃለሉ በዛሬው ስብሰባ ከውሳኔ ላይ መደረሱ ተነግሯል።
የወላይታ ዞን በዚህኛው ክልል ስር እንዲካተት በሀሳብ ደረጃ ቢቀርብም በስብሰባው ተሳታፊዎች ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን በስፍራው የነበሩት የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ ተናግረዋል። የስብሰባው ተሳታፊዎች ወላይታ ዞን ለብቻው ተነጥሎ የራሱን ክልል እንዲመሰረት ሀሳብ ማቅረባቸውንም ጠቁመዋል።
የወላይታን ጉዳይ በአንክሮ የተከታተሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “በጉዳዩ ላይ ከየብሔሩ ሽማግሌዎች ጋር ለመምከር አቅጣጫ አስቀምጠዋል” ብለዋል የስብሰባው ተሳታፊ
የወላይታ ዞን ላይ ጠንከር ያለ ቅሬታ በተለይ ሲያቀርቡ የነበሩት ከዞኑ ጋር የአስተዳደር ወሰን የሚጋሩት የጋሞ እና ዳውሮ ተወካዮች ነበሩ ተብሏል። ጉዳዩን በአንክሮ የተከታተሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “በጉዳዩ ላይ ከየብሔሩ ሽማግሌዎች ጋር ለመምከር አቅጣጫ አስቀምጠዋል” ብለዋል የስብሰባው ተሳታፊ። በዚህ ምክንያትም የወላይታ ጉዳይ ወደፊት ውሳኔ ይሰጥበታል በሚል በይደር መቆየቱን እኚሁ የስብሰባው ተሳታፊ ገልጸዋል።
በዛሬው ስብሰባ እንደ ወላይታ ሁሉ እልባት ያላገኘው ጉዳይ የጌዲኦ ዞን ጉዳይ እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል። የ“ሰላም አምባሳደሮች” የተሰኘው ቡድን ያዘጋጀው የቀደመ ምክረ ሃሳብ ላይ የጌዲኦ ዞን፣ ከቡርጂ እና አማሮ ወረዳዎች ጋር በመሆን አንድ ክልል እንዲመስርት ሀሳብ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ከአካባቢው ህዝቦች ተቃውሞ በመነሳቱ አማራጩ ውድቅ መደረጉን ምንጮች አስረድተዋል። በዛሬው ስብሰባ ላይ ጌዲኦ በልዩ ዞን እንዲደራጅ ከስምምነት ላይ ቢደረስም “በየትኛው ክልል ይካተት?” የሚለው ግን ወደፊት ይወሰናል መባሉንም አክለዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የነበረው የደቡብ ክልል አመራሮች ስብሰባ የተጠናቀቀው የደቡብ ክልልን አዲስ አወቃቀር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲተላለፍ ውሳኔ በማሳለፍ እንደነበር በስፍራው የነበሩ ተሳታፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩን ከሕገ መንግስቱ አንጻር ለሚመረምረው ቋሚ ኮሚቴው ይመራዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። ምክር ቤቱ ጉዳዩ ውሳኔውን በ30 ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቅ ቀነ ገደብ መቀመጡንም አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)