ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በታዛቢዎች ሚና አልተስማሙም

ግብጽ የህዳሴ ግድብ ድርድር ሶስቱ አገሮች በዋሽንግተኑ ስብሰባ ከስምምነት በደረሱባቸው ጉዳዮች መሠረት እንዲቀጥል ጠየቀች። የግብጽ ጥያቄ የቀረበው ከኢትዮጵያ እና ሱዳን የመስኖ እና ውሃ ሃብት ሚኒስትሮች ትላንት ሰኔ 2፤2012 ባደረጉት በኢንተርኔት አማካኝነት ባደረጉት የቪዲዮ ኮንፍረንስ ውይይት ነው። 

የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ ሶስቱ አገሮች “የድርድር ስነ-ስርዓትን፣ ስለ ታዛቢዎች፣ ስለ ድርድሩ አካሄድ እና ዋና ዋና ያልተቋጩ የድርድር ጉዳዮችን በተመለከተ ተነጋግረዋል” ብሏል። የሶስትዮሽ ስብሰባው የተካሔደው የአሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና የደቡብ አፍሪካ ታዛቢዎች በተገኙበት ነው።

የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር ያሲር አባስ የትላንቱ ውይይቱ ከተጠናቀቀ በኋላ “አዎንታዊ እና ፍሬያማ” ነበር ሲሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። ሚኒስትሩ እንዳሉት ድርድሩን በአፋጣኝ ለመቀጠል የሚያስፈልጉ እርምጃዎች እና ሶስቱም አገራት በተናጠል ያነሷቸው ዋነኛ የልዩነት ነጥቦች ውይይት ተደርጎባቸዋል። 

“እያንዳንዱ ሀገር ዋና ዋና የድርድር ጉዳዮች ናቸው ያሏቸውን ሃሳቦች በዝርዝር አቅርበዋል” ያለው የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በታዛቢዎች ሚና ላይ ከስምምነት አለመድረሳቸውን ገልጿል። የሱዳን መስኖ ሚኒስትርን የጠቀሰው የግብጹ “አህራም” ድረ ገጽ፤ ኢትዮጵያ በዋሽንግተን ስምምነት በተደረሰባቸው ጉዳዮች ድርድር ለመቀጠል ፈቃደኛ ብትሆንም መሰረታዊ የልዩነት ነጥቦች እንዳሏት ይፋ አድርጋለች ሲል ዘግቧል።  

ሶስቱ ሀገራት ከአርብ እና ከእሁድ በቀር የሶስትዮሽ ውይይቱን በየቀኑ ለመቀጠል መስማማታቸውን የሱዳን ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የኢትዮጵያ መንግሥት “የሶስቱ ሀገራት ድርድር የግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት እና ዓመታዊ አለቃቅ ላይ ብቻ የተወሰነ ይሆናል” ብሏል። 

እንደ ትናንትናው ሁሉ ዛሬም በቪዲዮ ኮንፍረንስ ይቀጥላል የተባለው ውይይት በመጪው ሰኞ አሊያም ማክሰኞ ይገመገማል። ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ የሚመሩት የግብጽ ብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት ከትናንትናው ስብሰባ በፊት ድርድሩ የሚካሄድበትን የጊዜ ሰሌዳ ጠይቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)