የህዳሴው ግድብ ያለስምምነት ከተሞላ “የሮሴይረስ ግድቤን አደጋ ውስጥ ይከትታዋል” ስትል ሱዳን ለጸጥታው ምክር ቤት አቤት አለች

566

በሐይማኖት አሸናፊ 

ሱዳን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ባስገባችው ደብዳቤ፤ የህዳሴው ግድብ ያለስምምነት ከተሞላ “የሮሴይረስ ግድቤን ብሎም በተፋሰሱ ላይ የተመሰረቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቼን ህይወት አደጋ ውስጥ ይከታል” ስትል አቤቱታ አቀረበች። ሀገሪቱ ደብዳቤውን ለምክር ቤቱ ያስገባችው ትላንት ረቡዕ ሰኔ 17፤ 2012 ነው።   

የሱዳኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስማ መሃመድ ለምክር ቤቱ በላኩት በዚሁ ደብዳቤ ላይ በሶስቱ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ስምምነት ባይደረስም ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ሙሌት ለመጀመር እቅድ መያዟ ሀገራቸውን በጥልቀት እንዳሳሰባት ገልጸዋል። ሚኒስትሯ ለስጋታቸው እንደማሳያ ያቀረቡት ከህዳሴው ግድብ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የሮሴይረስ ግድብን የህልውና ጉዳይ ነው። 

በ1988 ዓ. ም. ግንባታው የተጠናቀቀው የሮሴይረስ ግድብ በ290 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ላይ ያህል ቦታን በውሃ ይሸፍናል። በመገንባት ላይ ያለው የህዳሴው ግድብ የሮሴይረስን 10 እጥፍ እንደሚያህል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰዋል። 

የኢትዮጵያ ጠንክር ያለ አካሄድ ያሳሰባት የምትመስለው ሱዳን ያለ ስምምነት ሊደረግ ታቅዷል ያለችውን የህዳሴ ግድቡን የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌትን ጨምሮ “በሁሉም አካላት የሚወሰዱ ማንኛቸውም ተናጠል እርምጃዎች ይከልከሉልኝ” ስትል የጸጥታው ምክር ቤትን ተማፅናለች። “በግድቡ ላይ ስምምነት ለመድረስ የቀረው ጥቂት ነገር ብቻ ነው” የምትለው ሱዳን አገራቱ የቀራቸውን ጉዳይ እንዲያጠናቅቁ ጠይቃለች።

ሱዳን በጠቅላይ ሚኒስትሯ አብደላ ሃምዶክ አማካኝነት የግድቡ ሙሌትን የተመለከቱ ውይይቶች እንዲጀመሩ ጥረት ማድረጓን በዚሁ ደብዳቤዋ ላይ ጠቅሳለች። የድርድሩን ሂደት እና አስፈላጊነት በሰፊው በዳሰሰው ደብዳቤ ላይም ሃምዶክ ደቡብ አፍሪካን፣ የአውሮፓ ህብረትን እና አሜሪካንን ለታዛቢነት መጋበዛቸውን አንስቷል። 

ሶስቱ የአባይ ተፋሰስ አገራት በስድስት ዙር በቴክኒክ እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ የቪዲዮ ውይይቶች ማድረጋቸውን የገለጸችው ሱዳን የውይይቶቹን ውጤቶች የያዘ 18 ገጽ ሰነድ ከደብዳቤው ጋር በማያያዝ አቅርባለች። ድርድሩ  “የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሷል” የሚል እምነቷን በደብዳቤዋ ላይ አጽንኦት ሰጥታ ያንጸባረቀችው ሱዳን የሶስቱም አገራት መሪዎች የፖለቲካ ቁርጠኝነት በማሳየት በድርድሩ የሚደረሰውን ስምምነት እንዲፈርሙ የጸጥታው ምከር ቤት ግፊት እንዲያደርግ ጠይቃለች። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)