ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከደቡብ ክልል አራት ዞኖች አመራሮች ጋር ሊወያዩ ነው

በተስፋለም ወልደየስ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከደቡብ ክልል አራት ዞኖች አመራሮች ጋር ነገ ቅዳሜ ሐምሌ 25፤ 2012 ዕለት እንደሚወያዩ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር”ተናገሩ። ውይይቱ፤ ከክልል አደረጃጀት ጋር በተያያዘ በወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ እና ዳውሮ ዞኖች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለማርገብ ያለመ መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል።

በውይይቱ ላይ እንዲገኙ ለአራቱም ዞኖች አስተዳዳሪዎች እና የድርጅት አመራሮች ጥሪ እንደተላለፈ ምንጮች ገልጸዋል። የስብሰባው ዋና አጀንዳ “የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማጠናከር ነው” የሚሉት ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ በውይይቱ ላይ “የደቡብ ክልል አወቃቀር ጉዳይ በተጨማሪ አጀንዳነት ሊቀርብ ይችላል” ብለዋል።      

ለነገው ውይይቱ መጠራት ዋነኛ ምክንያት የሆነው ባለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዳራሽ በተካሄደው ስብሰባ ላይ በወላይታ ዞን እና በቀሪዎቹ ሶስት ዞኖች መካከል ታይቶ የነበረው “የተካረረ የሃሳብ ልዩነት ነው” ተብሏል። ሰኔ 2፤ 2012 በተካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ የደቡብ ክልልን ለሶስት የሚከፍለው አዲስ የአወቃቀር እቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ነበር።

በሰኔው ውይይት በአራቱ ዞኖች አመራሮች መካከል ልዩነት የተፈጠረው፤ የወላይታ ዞን አዲስ ከሚቋቋሙት ክልሎች በየትኛው ይካተት በሚለው ሀሳብ ላይ እንደነበር በስብሰባው የተሳተፉ ምንጮች በወቅቱ ገልጸዋል። የደቡብ ክልልን አዲስ አወቃቀር ያጠናው ቡድን፤ የወላይታ ዞን “ኦሞቲክ” የሚል ጊዜያዊ መጠሪያ በተሰጠው ክልል ስር እንዲካተት ሀሳብ አቅርቦ ነበር። 

ፎቶ፦ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የፌስቡክ ገጽ የተወሰደ

የ“ኦሞቲክ” ክልል የጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ደራሼ፣ ቡርጂ፣ አማሮ እና ኮንሶ ዞኖችን እና ልዩ ወረዳዎችን ይዞ እንዲደራጅ ምክረ ሃሳብ ቢቀርብም የወላይታ ዞን መካተት ግን ተቃውሞ ገጥሞታል። በስብሰባው ላይ ጠንከር ያለ ተቃውሞ ያሰሙት ከወላይታ ዞን ጋር ወሰን የሚጋሩት የጋሞ እና የጎፋ ዞኖች አመራሮች እንደነበሩ የነበሩ የሰኔውን ስብሰባ የታደሙ ተሳታፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። 

ከወላይታ ዞን ጋር ወሰንተኛ የሆነው የዳውሮ ዞን አመራሮችም ሌለኞቹ ቅሬታ አቅራቢዎች እንደነበሩ ተነግሯል። የ“ምዕራብ ዞን” አካባቢዎችን ባካተተው አዲስ ክልል ስር የተመደበው የዳውሮ ዞን አመራሮች፤ ከወላይታ ዞን ጋር አብሮ መደራጀቱን በመቃወም በስብሰባው ላይ አቋማቸውን በግልጽ አሳውቀው ነበር።  

በአራቱ ዞኖች አመራሮች መካከል የተፈጠረውን የሃሳብ ልዩነት በአንክሮ የተከታተሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ወደ ስፍራው በማቅናት “ከየብሔሩ ሽማግሌዎች ጋር” በጉዳዩ ላይ እንደሚመክሩ በስብሰባው ላይ ቢናገሩም እቅዳቸውን ሳያሳኩ ቀርተዋል። የነገው ስብሰባ ከዚሁ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እቅድ ጋር የተያያዘ መሆኑን ምንጮች “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  

የነገውን ስብሰባ በሚመለከት ከዞን እና ድርጅት አመራሮች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም። በነገው ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዙ ከነበሩ አመራሮች መካከል፤ የወላይታ ዞን የብልጽግና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጥበቡ ዮሃንስን የያዘ ተሽከርካሪ ላይ የመገልበጥ አደጋ መድረሱን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ቡታጅራ አካባቢ በደረሰው በዚህ አደጋ በአቶ ጥበቡ ላይ ጉዳት አለመድረሱን ምንጮች አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)