በሐይማኖት አሸናፊ
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፤ በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን በሁለት ዙር የታገቱ 16 ተማሪዎችን ጠልፈዋል ባላቸው 17 ሰዎች ላይ፤ ሐምሌ 7፤ 2012 በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መስርቷል። ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በክሱ እንደገለጸው ተከሳሾች ያገቷቸውን ተማሪዎች “በጃል መሮ ለሚመራው የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን አሳልፈው ሰጥተዋል”።
ከደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት በመሸሽ ላይ የነበሩ ተማሪዎችን በማገት የተጠረጠሩት ግለሰቦች ክስ የቀረበባቸው በአንድ መዝገብ ነገር ግን በሶስት ቡድን ተከፍለው ነው። በአንደኛው ቡድን ላይ 14 ተከሳሾች ተካትተዋል።
የመጀመሪያው ክስ፤ 13ኛ ተከሳሽ ጌታቸው ዮናስ እና 14ኛ ተከሳሽ ኢብሳ ፉፋ ከሌሎች ስምንት የኦነግ ሸኔ አባላት እና አመራሮች ጋር ሕዳር 22፤ 2012 ስለ ድርጊቱ ተወያይተው መስማማታቸውን ያስረዳል። ጃል ኡርጂ፣ ጃል ጉቱ፣ ገመዳ ረጋሳ፣ ግርማ ይገዙ፣ አሕመዲን ይተፋ፣ ሞሌ ዱጉማ፣ ኢብሳ በቀለ እና ኬኔሳ ዮናስ አብረው ያቀዱ ናቸውም ተብሏል።
“ተከሳሾች ምክክር ካደረጉ ከሁለት ቀናት በኋላ ህዳር 24፤ 2012 ከቀኑ 7 እስከ 8 ሰዓት ባለው ውስጥ በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን፣ ሶዮ ወረዳ፣ ሜንኮ ቀበሌ ቧንቧ ከተባለው አካባቢ የአማራ ብሄር ተወላጆች የሆኑ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ጠልፈዋል” ሲል አቃቤ ሕግ ጠቅሷል። በዕለቱ ተጠለፉ የተባሉት አምስት ሴቶች ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል አንዷ የአካባቢው ነዋሪ መሆኗም ተገልጿል።
ሞንሞን በላይ፣ ጤናለም ሙላቴ፣ ሳምራዊት ቀሬ እና አሳቤ አያል የተባሉት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን እና ትዕግስት መሳይ የተባለች የአካባቢው ነዋሪ ተሳፍረውበት ከነበሩበት ቀይ ዶልፊን መኪና “በዱላ እና በጦር መሳሪያ በማስፈራራት፤ ደብድበው በማውረድ ጠልፈዋል” ሲልም አቃቤ ሕግ ከስሷል። ስማቸው ከተጠቀሰው ሴቶች ባሻገርም ለጊዜው በውል ያልተለዩ ሴቶች ታግተው መወሰዳቸውን ክሱ አረጋግጧል።
ተማሪዎቹ የተሳፈሩበትን መኪና በማስቆም ጠለፋውን ያካሂዱት በክሱ መዝገብ ላይ ከ1ኛ እስከ 8ኛ የተዘረዘሩት ተከሳሾች ማለትም ከሊፋ አብድራሕማን፣ ሬድዋን ተማም፣ አብዶ ኢብራሂም፣ ናስር መሃመድ፣ ዮሴፍ ጅራታ፣ አወል ጂብሪል፣ ነቢዩ ባባከር እና ጋዲሳ ገለቱ መሆናቸውም አቃቤ ሕግ አብራርቷል።
“አወል ጂብሪል የመኪናውን ቁልፍ ሲነቅል ሌሎች ተከሳሾች ኦሮምኛ ቋንቋ የማይችሉ ወይም አማርኛ ቋንቋ ብቻ የሚናገሩትን በመለየት በመደብደብ ጠልፈዋል ወይም አግተዋል”
– የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ
“አወል ጂብሪል የመኪናውን ቁልፍ ሲነቅል ሌሎች ተከሳሾች ኦሮምኛ ቋንቋ የማይችሉ ወይም አማርኛ ቋንቋ ብቻ የሚናገሩትን በመለየት በመደብደብ ጠልፈዋል ወይም አግተዋል” ያለው አቃቤ ሕግ ተከሳሾች አግተዋቸዋል የተባሉትን እነዚህን ሴቶች “ወደ ጫካ በመውሰድ ለኦነግ ሸኔ የበላይ አመራሮች አስረክበዋል” ሲል ወንጅሏል።
በቀጣይ ቀንም ከቀኑ ሰባት ሰአት አካባቢ በቄለም ወለጋ ዞን፣ አንፊሎ ወረዳ ሱዲ ቀበሌ በተመሳሳይ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያጋጠመውን አለመረጋጋት ሸሽተው ወደ ጋምቤላ ከተማ አቅጣጫ በሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ ተሳፍረው በመሄድ ላይ ሳሉ አምስት ሴት እና አንድ ወንድ ተማሪዎችን እንዲሁም ለጊዜው በውል ያልተለዩ ተማሪዎችን መታገታቸውን አቃቤ ሕግ ገልጿል።
“ደበላ ቀናአ፣ ኩዩሼ ባይሳ፣ አቦ አስፋው ገመዳ፣ ዳዊት ታዬ እና ሌሎች ለጊዜው ያልታወቁ የኦነግ ሸኔ አባላት በጋራ በመሆን እገታውን አከናውነዋል። የታገቱ ተማሪዎችንም 12ኛ እና 14ኛ ተከሳሾችን ጨምሮ ለሌሎች የኦነግ ሸኔ አባላት ተላልፈው ሰጥተዋል” ሲል ከሳሽ አቃቤ ሕግ በክስ መዝገቡ አስፍሯል።
“ለኦነግ ሸኔ አሸባሪ ቡድን የበላይ አመራሮች ተሰጥተዋል” የተባሉት እና ተለይተው የታወቁ ተማሪዎች ቁጥር 16 መሆኑ በክሱ ላይ ተጠቅሷል። ተከሳሾቹ “በትግል ስማቸው ጃል መሮ፣ ጃል ሮባ፣ ጃል ጉራራ፣ ጃል ኡርጂ፣ ጃል ፈንድሼ ለተባሉ እና ለጊዜው ላልታወቁ የቡድኑ አባላት [ተማሪዎችን] አሳልፈው በመስጠት በዋና ወንጀል አድራጊነት ጠርጥረናቸዋል” ብሏል አቃቤ ሕግ።
አስራ አራቱ ተከሳሾች ክስ የተመሰረተባቸው የወንጀል ሕጉን እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን ድንጋጌዎች በመተላለፍ ነው። በ15ኛ ተከሳሽነት፣ በተመሳሳይ መዝገብ ስማቸው የተቀመጡት ተፈራ ሂካ፤ ለብቻቸው ክስ ተመስርቶባቸዋል።
አቶ ተፈራ “በሱዲ ቀበሌ የኦነግ ሸኔ አስተባባሪ በመሆናቸው በሁለተኛ ዙር የታገቱትን ተማሪዎችን በመቀበል በሕዳር 25፤ 2012 በቤቱ አሳድሯል። የሽብር ወንጀል ድርጊት መሆኑን እያወቀ በቂ ምክንያት ሳይኖረው ለፖሊስ ወይም አግባብነት ላለው የሕግ አስፈፃሚ ባለማሳወቁ የሽብር ድርጊትን ባለማሳወቅ ወንጀል ተከስሷል” ሲል የአቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ አብራርቷል።
በሶስተኛ ቡድን የተካተቱት በ16ኛ እና 17ኛ ተከሳሽነት የተዘረዘሩት ርስቁ አብደላ እና ሃምዲ አረቢሴን ናቸው። ሁለቱ ተከሳሾች በተመሳሳይ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጁን በመተላለፍ ክስ ተመስርቶባቸዋል። ተከሳሾቹ በህዳር 24፤ 2012 በሜንሶ ቀበሌ በመጀመሪያ ዙር የታገቱ ተማሪዎች በአካባቢው ወዳለ ጫካ ተይዘው መወሰዳቸውን እያወቁ፤ ለሕግ አካላት ባለማሳወቃቸው ምክንያት የተከሰሱ መሆኑን አቃቤ ሕግ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)