በተስፋለም ወልደየስ
በወላይታ ሶዶ ከተማ የሚገኘው የዎጌታ የማህበረሰብ ራዲዮ ጣቢያ ስርጭት ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ በጸጥታ ኃይሎች ትዕዛዝ እንዲቋረጥ መደረጉን የጣቢያው ጋዜጠኞች አስታወቁ። ትዕዛዙን የሰጡት፤ ጣቢያው ወደሚገኝበት ግቢ የገቡ የታጠቁ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ለደህነንታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የጣቢያው ጋዜጠኛ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት ክስተቱ የተፈጠረው ዛሬ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ገደማ የጣቢያው ጋዜጠኞች በዜና ዝግጅት ላይ ባሉበት ወቅት ነበር። በሰዓቱ አራት የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ የለበሱ ወታደሮች ጣቢያው ወደሚገኝበት የጉተራ አዳራሽ ግቢ በመዝለቅ ጋዜጠኞቹ ስራቸውን እንዲያቆሙ ትዕዛዝ መስጠታቸውን አስረድተዋል።
በግቢው የጥበቃ ሰራተኞች አማካኝነት ትዕዛዝ የደረሳቸው ሰባት የሬድዮ ጣቢያው ሰራተኞች መደበኛ ስርጭቱን አቋርጠው ግቢውን ለቅቀው መውጣታቸውን ጋዜጠኛው ገልጸዋል። ጋዜጠኞቹ ስራቸውን እንዲያቆሙ የሆነበት ምክንያት በግልጽ ባይነገራቸውም፤ ጣቢያውን የመዝጋት እርምጃ የተወሰደው፤ ባለፉት ቀናት ከነበሩ ዘገባዎቻቸው ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም የሚል ጥርጣሬ አላቸው። ለዚህም የወላይታ ዞን የሰላም እና የጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎች በጣቢያው የሰሞኑ ዘገባዎች ደስተኛ አለመሆናቸውን በተደጋጋሚ መግለጻቸውንም በማስረጃነት ያነሳሉ።

ራዲዮ ጣቢያው፤ ባለፈው እሁድ ነሐሴ 3፤ 2012 በስብሰባ ላይ እያሉ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የተደረጉ የወላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች ግለሰቦችን ጉዳይ በተከታታይ ሲዘግብ ቆይቷል። የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤን ጨምሮ የታሰሩት ግለሰቦች ትላንት ሐሙስ ነሐሴ 7፤ 2012 በፍርድ ቤት ውሳኔ በዋስ እንዲፈቱ ሲወሰንም ጣቢያው ሂደቱን በቀጥታ ሲያስተላልፍ ነበር።
ውሳኔውን ተከትሎ፤ የሶዶ ከተማ ነዋሪዎች እና ከሌሎች የወላይታ ዞን አካባቢዎች የመጡ ሰዎች በአደባባይ ደስታቸውን ሲገልጹ፤ ጣቢያው በቀጥታ ስርጭት ሽፋን ሰጥቷል። ምሽቱን ከእስር የተለቀቁት የወላይታ ዞን አስተዳዳሪን እና የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ጢሞቲዮስን መልዕክትም ለአድማጮቹ በቀጥታ አቅርቧል።
በወላይታ ልማት ማህበር አማካኝነት የተቋቋመው የዎጌታ የማህበረሰብ ራዲዮ ጣቢያ፤ ከታህሳስ 2010 ዓ. ም. ጀምሮ በ96.6 ሜጋ ኸርዝ ለወላይታ ዞን እና አካባቢው ዜናዎችን እና ሌሎችንም ዝግጅቶች ሲያስተላልፍ ቆይቷል። መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገውን የሸገር ኤፍ ኤም ዜናዎችን በቅብብሎሽ የሚያሰራጨው ራዲዮ ጣቢያው፤ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽት ሁለት ሰዓት ድረስ በአየር ላይ ይቆያል።
“ስርጭቱ የተቋረጠው በጸጥታ ኃይሎች ነው ወይንስ በሌሎች አካላት ነው የሚለው ክትትል ያስፈልገዋል። ከዚህ በፊት ጣቢያው ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎች ነበሩ። እርሱን የማጣራት ስራዎች እየሰራን ባለንበት ወቅት ነው ስርጭቱ መቆሙን የሰማነው።”
የሺወርቅ ግርማ – በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የብሮድካስት ሚዲያ ክትትል ዳይሬክተር
በዛሬው ዕለት ስርጭቱ በጸጥታ ኃይሎች አስገዳጅ ትዕዛዝ መቋረጡን ተከትሎ፤ የጣቢያው ጋዜጠኞች እና ኃላፊዎች ሁኔታውን ወዲያውኑ ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ማሳወቃቸውን ተናግረዋል። ለማህብረሰብ ሬድዮ ጣቢያዎች ፍቃድ የሚሰጠው እና መደበኛ ክትትል የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አቤቱታው እንደደረሰው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል።
በባለስልጣኑ የብሮድካስት ሚዲያ ክትትል ዳይሬክተር የሆኑት የሺወርቅ ግርማ የራዲዮ ጣቢያው ስርጭት መቆሙን እንደሚያውቁ ተናግረዋል። ሆኖም “ስርጭቱ የተቋረጠው በጸጥታ ኃይሎች ነው ወይንስ በሌሎች አካላት ነው የሚለው ክትትል ያስፈልገዋል” ሲሉ መስሪያ ቤታቸው ነገሩን በማጣራት ላይ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። “ከዚህ በፊት ጣቢያው ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎች ነበሩ” የሚሉት ዳይሬክተሯ “እርሱን የማጣራት ስራዎች እየሰራን ባለንበት ወቅት ነው ስርጭቱ መቆሙን የሰማነው” ብለዋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወላይታ ዎጌታን ጨምሮ 49 የማህበረሰብ ራዲዮ ጣቢያዎች በባለስልጣኑ ፍቃድ ተሰጥቷቸው ስራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ። እስካሁን ድረስ አንድም የማህበረሰብ ራዲዮ ጣቢያ ስርጭት በዚህ አይነት መልኩ ተቋርጦም ሆነ ፍቃዱ ተሰርዞ እንደማያውቅ የብሮድካስት ሚዲያ ክትትል ዳይሬክተሯ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)