በተስፋለም ወልደየስ
የምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ ልደቱ አያሌው በ100 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተፈትተው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ትዕዛዝ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን የሰጠው ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 12፤ 2013 ከሰዓት በነበረው የችሎት ውሎው ነው።
ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው የአቶ ልደቱን ዋስትና በተመለከተ በአቃቤ ህግ እና በተከሳሽ ጠበቆች በኩል የተደረገውን ክርክር መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ነው። ባለፈው አርብ በነበረው የችሎት ውሎ፤ የፍርድ ቤቱ ዳኞች ሰኞ ጉዳዩን መርምረው ውሳኔያቸውን ዛሬ ይዘው እንደሚቀርቡ ገልጸው ነበር።
ዘጠኝ ሰዓት ገደማ በተጀመረው በዛሬው የችሎት ውሎ፤ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን የክርክር ጭብጥ በድጋሚ አስታውሷል። ከሳሽ አቃቤ ህግ “አቶ ልደቱ በዋስትና ከእስር እንዲወጡ ከተፈቀደላቸው ውጪ ሀገር የህክምና ቀጠሮ ስላላቸው በዚያው ሄደው ይቀራሉ፤ ፍርድ ቤትም ተመልሰው አይቀርቡም” ሲል በባለፈው የችሎት ውሎ ዋስትናውን ተቃውሞ ነበር።
ይህን የአቃቤ ህግ መከራከሪያ የተመለከተው ፍርድ ቤቱ፤ “ከአቶ ልደቱ የቀደመ ተሞክሮ እና ካላቸው ሰብዕና አንጻር ከፍትህ ስርዓቱ ይሸሻሉ ብለን አናምንም” ሲል እንዳልተቀበለው የዛሬውን የችሎት ውሎ የተከታተሉት የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሆኖም ፍርድ ቤቱ የዋስትና ገንዘቡን ከፍተኛ ማድረጉን ለተከራካሪዎቹ መግለጹን አቶ አዳነ አስረድተዋል። የችሎቱ ዳኞች ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ሁለት ሶስተኛ በሆነ ድምጽ እንደሆነም ፍርድ ቤቱ ማስታወቁንም አክለዋል።
“ዋናው የውሳኔያቸው ጭብጥ አቶ ልደቱ አሁን ካለባቸው የልብ ህመም እና ከወቅቱ የኮሮና ወረርሽኝ አንጻር በጣቢያ ውስጥ ቢቆዩ ለህይወታቸው አስጊ ስለሚሆን፤ ውጪ ቢወጡ በፍርድ ቤት ቀጠሮ ይቀርባሉ ብለን ስለምናምን፣ በዋስ ወጥተው ጉዳዩን እንዲከራከሩ የሚል ነው” ሲሉ የኢዴፓው ፕሬዝዳንት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አብራርተዋል።
የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ልደቱ በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ከሐምሌ 17፤ 2012 ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት በቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ነው። ተቃዋሚ ፖለቲከኛው በቁጥጥር ስር እንዲቆዩ የተደረገው፤ የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ሰኔ 23 እና 24፤ 2012 በቢሾፍቱ ከተማ የተቀሰቀሰውን ሁከት በማስተባበር እና በገንዘብ በመደገፍ በመጠርጠራቸው እንደሆነ የኦሮሚያ ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት ሲገልጽ ቆይቷል።
ተጠርጣሪው ለሁለት ጊዜ ያህል ያቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ ውድቅ ያደረገው የቢሾፍቱ ከተማ ፍርድ ቤት፤ የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን የዘጋው አቃቤ ህግ ክስ እንዲመሰረት በማዘዝ ነበር። ፍርድ ቤቱ የሰጠው ቀነ ገደብ ባለመከበሩ ቅር የተሰኙት አቶ ልደቱ፤ በቢሾፍቱ ከተማ ፍርድ ቤት በሚደረግ የህግ ክርክር ላለመሳተፍ በመወሰን፣ የሚወክሏቸውን ጠበቆች እስከማሰናበት ተጉዘው ነበር።
አቶ ልደቱ ውሳኔያቸውን ባሳወቁ በማግስቱ የኦሮሚያ አቃቤ ህግ በአዳማ ከተማ በሚገኘው የምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ከፍቶባቸዋል። አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ አቶ ልደቱ የተጠረጠሩበትን ዋና የወንጀል ፍሬ በመተው “ህገ ወጥ ሽጉጥ በመያዝ ወንጀል” የቀረበ ነበር። በ2012 ዓ. ም. የወጣውን የጦር መሳሪያ አስተዳደር አዋጅ በመተላለፍ የተከሰሱት አቶ ልደቱ፤ ጉዳያቸውን ለመከታተል መስከረም 20፤ 2013 ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ዛሬ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)