በምዕራብ ሀረርጌ የአንበጣ መንጋን ለመከላከል የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተዘጉ

በበለጠ ሙሉጌታ 

በኦሮሚያ ክልል፤ ምዕራብ ሀረርጌ ዞን፤ በጉባ ቆርቻ ወረዳ በሚገኙ ሁሉም ቀበሌዎች ላይ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል የአካባቢው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተዘጉ። የአንበጣ መንጋው በወረዳው ከሰፈረ አምስት ቀናት ያስቆጠረ ሲሆን የመንግስት መስሪያ ቤቶቹ ዛሬን ጨምሮ ለአራት ቀናት ስራ እንዲያቆሙ ተደርገዋል። 

የጉባ ቆርቻ ወረዳ የአስተዳደር ጽህፈት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታሪኩ ንጉሴ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት የአንበጣ መንጋው በወረዳው በሚገኙ 24 ቀበሌዎችን ሙሉ ለሙሉ ሸፍኗል። የአንበጣ መንጋው እስከ ትላንት ድረስ ያልነካቸው ሶስት ቀበሌዎችንም ዛሬ ሐሙስ፤ ጥቅምት 5 ማዳረሱንም ተናግረዋል። 

አካባቢው በማሽላ እና በቆሎ ምርቶች የታወቀ መሆኑን የሚናገሩት የወረዳው የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ ሳኒ አሊዬ፤ የአንበጣ ወረርሽኙ በስፋት በታየባቸው ሃያ አንድ ቀበሌዎች ውስጥ ያሉ የአርሶ አደር ማሳዎች በሁለቱ የእህል አይነቶች አዝመራ የተሸፈኑ እንደሆኑ ይገልጻሉ። በአሁኑ ወቅት የአንበጣ መንጋው  ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ በቀበሌዎቹ ያለውን አዝመራ መውረሩንም አመልክተዋል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው በወረዳው የሚገኙ አቶ መንግስቱ ብሩ የተባሉ አርሶ አደር፤ የግብርና ቢሮ ኃላፊውን ገለጻ አጠናክረዋል። አቶ መንግስቱ ያለሙት 1.5 ሄክታር የሚሆን የበቆሎ፣ ማሽላ እና ቦሎቄ ምርት በአንበጣው ሙሉ ለመሉ መውደሙን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በጓሮ ሲያለሙት የነበረ የሽንኩርት ማሳ ሙሉ ለሙሉ በአንበጣው እንደተወረረባቸው ተናግረዋል።

ከእርሻ ማሳዎች ባሻገር በወረዳው የሚገኙ “ጫካዎች እና ዛፎች ሳይቀሩ በአንበጣው ተወረርዋል” የሚሉት አርሶ አደሩ፤ መንግስት በአፋጣኝ ድጋፍ ካላደረገላቸው፤ ወደፊት ልጆቻቸውን ለመመገብ እንደሚቸገሩ ገልጸዋል። የወረዳው የግብርና ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው “አንበጣውን ለመከላል ከመንግስት ምንም ድጋፍ አልተደረገልንም” ብለዋል። 

በትላንትናው ዕለት የፌደራል እና የክልል የግብርና ቢሮ የስራ ኃላፊዎች በአካባቢው በመገኘት አንበጣውን ያደረሰውን ጉዳት ተመልክተዋል። ትላንት ረቡዕ የአሮሚያ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በተገኙበት በጥቂት ስፍራዎች በድሮን በመታገዝ የኬሚካል ርጭት ለማከናወን መሞከሩን አቶ መሀመድ ተናግረዋል። 

በጉባ ቆርቻ ወረዳ በ21 ቀበሌዎች ካለው 13,800 ሄክታር የእርሻ መሬት ውስጥ፤ የኬሚካል ርጭት የተደረገለት “ከ5 ሄክታር እንደማይበልጥ” የወረዳው የግብርና ቢሮ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። በስፍራው የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል የሚያስችል የኬሚካል መርጫ መሳሪያዎች እና የኬሚካል ዕጥረት መኖሩን የሚገልጹት አቶ መሀመድ፤ በመንግስት በኩል በአፋጣኝ በቂ ድጋፍ ካልተደረገ አሁን ከደረሰውም በባሰ “የከፋ ጉዳት ሊደርስ ይችላል” ብለዋል።  

የወረዳው አስተዳደር የበረሃ አንበጣውን ለመከላከል በስሩ የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከሰኞ ጀምሮ ዝግ አድርጎ ሰራተኞቹን ወደ ገጠር ማሰማራቱን የወረዳ የአስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊው አመልክተዋል። የመንግስት ሰራተኞቹ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር፣ ባህላዊ መንገዶችን ጭምር በመጠቀም፣ አንበጣውን ለመከላከል ጥረት እያደረጉ እንደሆነም አቶ ታሪኩ አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)