የምግብ ዋስትና ሴፍቲኔት መርሃ ግብር በ72 ከተሞች ሊጀመር ነው

በበለጠ ሙሉጌታ 

በኢትዮጵያ በ11 ከተሞች ሲተገበር የቆየው የምግብ ዋስትና ሴፍቲኔት መርሃ ግብር ተጨማሪ 72 ከተሞችን ሊያካትት ነው። ለከተሞች ሴፍቲኔት መርሃ ግብሩ ለአምስት ዓመት የሚሆን 550 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተመድቧል ተብሏል። 

የፌደራል የከተሞች ስራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ጊዜያዊ የህዝብ ግኑኙነት ኃላፊ አቶ መላኩ ንጉሴ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት ለመርሃ ግብሩ የተመረጡት 72 ከተሞች በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች የሚገኙ ናቸው። ከተሞቹ ያላቸው የህዝብ ብዛት፣ የስራ አጥ ቁጥር እና መሰል ጉዳዮች በመምረጫ መስፈርትነት ማገልገላቸውንም ገልጸዋል። 

መስሪያ ቤታቸው የምርጫው መስፈርቶችን እና መረጃዎች ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ መወሰዱን የጠቆሙት ጊዜያዊ የህዝብ ግኑኙነት ኃላፊው፤ ይህንን ተከትሎም ለየክልሎቹ በተሰጠው ኮታ መሰረት ከተሞቹ መመረጣቸውን አብራርተዋል። በአዲሱ ኮታ መሰረት ከፍተኛውን ድርሻ ያገኙት በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ከተሞች ሲሆኑ ከአጠቃላይ ድልድሉ 29 በመቶውን ወስደዋል።   

በተከታይነት የሚገኘው የአማራ ክልል ከከተሞች ኮታ 16 በመቶ ያገኘ ሲሆን የደቡብ ክልል ደግሞ 14 በመቶውን ድርሻ በመውሰድ በሶስተኛነት ሰፍሯል። የትግራይ እና ሶማሌ ክልሎች በተመሳሳይ ከከተሞች ኮታ አምስት በመቶ ድርሻ ተሰጥቷቸዋል። ጋምቤላ፣ አፋር እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በበኩላቸው እያንዳንዳቸው አንድ በመቶ ድርሻ  አግኝተዋል። 

ከዚህ ቀደም የምግብ ዋስትና ሴፍቲኔት መርሃ ግብር ሲተገበርባቸው ከቆዩት 11 ከተሞች ውስጥ መዲናዋ አዲስ አበባ አንዷ ናት

ከዚህ ቀደም የምግብ ዋስትና ሴፍቲኔት መርሃ ግብር ሲተገበርባቸው የቆዩት ከተሞች አዲስ አበባ፣ አዋሳ ፣ደሴ፣ ጅግጅጋ፣ ሰመራ፣ ድሬዳዋ፣ አዳማ፣ ሀረር፣ አሶሳ፣ መቀሌ እና ጋምቤላ ነበሩ። በእነዚህ ከተሞች 488 ሺህ ገደማ ሰዎች የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች ሆነዋል።

በሴፍቲኔት መርሃ ግብሩ ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ አዳጊዎች እና ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ጎልማሶች፣ አካል ጉዳተኞች እና የአዕምሮ ህሙማን ናቸው። እነዚህ የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች በከተማ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ እርከን ስራ እና አረንጓዴ ልማት ስራዎች ላይ በቀን ለአራት ሰዓታት እንዲሰሩ በማድረግ ክፍያ እንዲያገኙ ይደረጋል። ክፍያው የሚፈጸመው በቀን 115 ብር ሂሳብ ባላቸው የቤተሰብ ቁጥር ልክ ተባዝቶ ነው።

የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች በየወሩ ከሚያገኙት ገቢ 20 በመቶ እንዲቆጥቡ ተደርጎ በመጨረሻም ከፕሮግራሙ ሲወጡ በቤተሰብ ደረጃ የሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ (grant) ተጠቃሚ ይሆናሉ። እያንዳንዱን ተጠቃሚ ከሶስት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እራሱን ይችላል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የህይወት ክህሎት የስራ ፈጠራ እና መሰል የኑሮ ማሻሻያ ስልጠናዎች የመርሃ ግብሩ ክፍሎች ናቸው። 

የፌደራል የከተሞች ስራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ለሴፍትኔት መርሃ ግብሩ የመረጣቸው 72 ከተሞችን የለየው፤ ባላቸው የህዝብ ብዛት፣ የስራ አጥ ቁጥር እና መሰል ጉዳዮችን በመስፈርትነት በመጠቀም መሆኑን አስታውቋል

“የዕለት ጉርስ በማጣት ልጆቻቸውን እንኳን ትምህርት ቤት መላክ ፈታኝ የሆነባቸው ወላጆች፤ ፕሮጀክቱ በፈጠረላቸው ዕድል ልጆቻቸውን በኩራት የማስተማር አቅም ላይ ከመድረስም አልፈው ለነገ ህይወታቸው መቆጠብ ሲጀምሩ የአይን እማኝ መሆን ችለናል” ሲሉ ጊዜያዊ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው መርሃ ግብሩ ያመጣውን ለውጥ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። 

የ2013 የመርሃ ግብር ተጠቃሚዎችን ለመመዝግብ ዝግጀት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ መላኩ፤ በ83 ከተሞች በድምሩ 798, 500 ዜጎች በአካባቢ ልማት ስራ እንዲሳተፉ ይደረጋል ብለዋል። በመጀመሪያ ዙር በታቀፉ ከተሞች የተመዘገበው ውጤት ከዓለም ባንክ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት እንዳስቻለም ገልጸዋል። 

የዓለም ባንክ የስራ አስፈጻሚ የዳይሬክተሮች ቦርድ ከሁለት ሳምንት በፊት መስከረም 20፤ 2013 ባደረገው ስብሰባ ለዚሁ መርሃ ግብር የሚውል 400 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማጽደቁ ይታወሳል። የገንዘብ ድጋፉ የስምምነት ፊርማ በዓለም ባንክ እና በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 4፤ 2013 ተፈጽሟል። በሰባ ሁለቱ ከተሞች ተግባራዊ ለሚደረገው የሴፍቲኔት መርሃ ግብር የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ 150 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል ተብሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)