በአማራ ክልል በዳንሻ በኩል ተጨማሪ ጥቃት ተፈጽሟል- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

በተስፋለም ወልደየስ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአማራ ክልል በዳንሻ በኩል ተጨማሪ ጥቃት መፈጸሙን ገለጹ። በመከላከያ ሰራዊት ላይ በመቀሌ እና በሌሎች አካባቢዎች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት መሰንዘሩንም አስታውቀዋል። ዛሬ ረቡዕ አነጋግ ላይ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለያዩ ቦታዎች እና ከተሞች መሰል ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።  

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሊቱን በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው በጹሁፍ ባሰራጩት መግለጫ ጥቃቱን የፈጸመው ሕወሓት እንደሆነ ቢገልጹም፤ በበቪዲዮ ተቀርጾ በተላለፈ መግለጫቸው ግን የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲን በስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል። ይልቁንም ጥቃቱን የፈጸሙት “ከሀዲ ኢትዮጵያውያን እና የጥፋት ኃይሎች ናቸው” ብለዋል።

ይህ ኃይል በኢትዮጵያ ባለፉት በርካታ ወራት “እኩይ ተግባራት ሲፈጽም ቆይቷል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ትላንት ምሽት ጥቃት ወደ መሰንዘር መሸጋገሩን አመልክተዋል። “ባለፉት ጥቂት ቀናት ያለምንም ሃፍረት በሚዲያ በመውጣት ‘ኢትዮጵያን እወጋለሁ’ ብሎ ሲያውጅ፣ ሲናገር የነበረው ኃይል፤ ይህን ለማመን የሚያስቸግር ንግግር በተግባር በዚህ ምሽት አረጋግጧል” ሲሉ ወንጅለዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል በዳንሻ በኩል “ተፈጽሟል” ያሉትን ጥቃት፤ የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች “መመከታቸውን” ተናግረዋል። በትግራይ ክልል መቀሌን ጨምሮ በበርካታ ስፍራዎች በመከላከያ ሰራዊት ላይ ትላንት ማክሰኞ ምሽት ጥቃት “ያልተጠበቀ ጥቃት” መሰንዘሩን በመግለጫቸው የጠቀሱት አብይ፤ በኢትዮጵያ እስካሁን ከደረሱት ጥቃቶች “እጅግ አስነዋሪ ያደርገዋል” ያሉበትንም ምክንያት አብራርተዋል። 

“ሰላም ለማስከበር በተለያየ ሀገር የተሰማራው የሀገር መከላከያ ሰራዊት እንኳ፤ በውጭ ኃይሎች ያልደረሰበትን ጥቃት በገዛ ወገኖቹ ከጀርባው እንዲመታ ብዙዎች እንዲሰዉ፣ ብዙዎች እንዲቆስሉ፣ ንብረቶች እንዲወድሙ ተደርገዋል” ብለዋል። የመከላከያ ሰራዊት አባላት በሚሰጣቸው ግዳጅ፤ ከዚህ በኋላም መስዋዕትነቶች ሊከፍሉ እንደሚችሉም ጠቁመዋል። 

“ሰላም ለማስከበር በተለያየ ሀገር የተሰማራው የሀገር መከላከያ ሰራዊት እንኳ፤ በውጭ ኃይሎች ያልደረሰበትን ጥቃት በገዛ ወገኖቹ ከጀርባው እንዲመታ ብዙዎች እንዲሰዉ፣ ብዙዎች እንዲቆስሉ፣ ንብረቶች እንዲወድሙ ተደርገዋል”

– ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትላንት ለሊት የጹሁፍ መግለጫቸው የመከላከያ ሰራዊት በሕወሓት ላይ እርምጃ እንዲወስድ መታዘዙን ገልጸው ነበር። ዘግየት ብለው በቪዲዮ ባስተላለፉት መገለጫ ደግሞ፤ ሰራዊቱ “ከጠቅላይ ሰፈር በሚሰጥ ትዕዛዝ መሰረት መለዮውን፣ ሀገሩን እና ህዝቡን እንዲከላከል” ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ህዝብም ወደፊት ሊፈጸሙ ለሚችሉ ጥቃቶች  ራሱን እንዲያዘጋጅም አሳስበዋል።    

“[የጥፋት ኃይሎቹ] በመላ ሀገራችን ቀድመው ባሰለጠኑት፣ ባሰማሩት፣ ባዘጋጁት ኃይል በተለያየ ከተማ፣ በተለያየ ቦታ መሰል በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ሊካሄድ ስለሚችል መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከሚሊሺያ፣ ከፖሊስ ሰራዊት እንዲሁም በአካባቢያቸው ከሚገኝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመተባበር ቀያቸውን፣ ጎረቤታቸውን፣ ሰፈራቸውን፣ ከተማቸውን፣ አካባቢያቸውን በንቃት እንዲጠብቁ [አሳስባለሁ]” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)