በተስፋለም ወልደየስ
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የባንክ ሂሳባቸው እንዲታገድ ያደረገባቸው 34 የትግራይ የመልሶ ማቋቋም ኢንዶውመንት ፈንድ (ኤፈርት) ድርጅቶች ላይ የወንጀል ምርመራ እየተደረገባቸው ነው። ጠቅላይ አቃቤ ህግ የድርጅቶቹን የባንክ ሂሳብ ያሳገደው ትላንት ሰኞ ህዳር 7፤ 2013 ለባንኮች በጻፈው ደብዳቤ ነው።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የጠቅላይ አቃቤ ህግ ደብዳቤ ሰላሳ አራቱ ድርጅቶች የባንክ ሂሳባቸው እንዲታገድ የተደረገው ከተጠረጠሩባቸው ሶስት ወንጀሎች ምርመራ ጋር በተያያዘ መሆኑን ይገልጻል። ድርጅቶቹ ከተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች መካከል “በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች የሚፈጸሙ የዘር ተኮር ጥቃቶችን፣ የሽብር ተግባራትን እና ሕገ መንግስታዊ ስርዓትን በኃይል ለመናድ ከሚሰሩ አካላት ጋር በመመሳጠርና ግንኙነት በመፍጠር በገንዘብ መደገፍ” የሚል ይገኝበታል።
ሰላሳ አራቱ የኤፈርት ድርጅቶች “በሙስና እና በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ” ወንጀሎችም ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የጠቅላይ አቃቤ ህግ ደብዳቤ ያስረዳል። ከድርጅቶቹ መካከል ሱር ኮንስትራክሽን፣ ጉና የንግድ ሥራዎች፣ ትራንስ ኢትዮጵያ፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ፣ ሰላም የህዝብ ማመለሻ፣ ሜጋ ማተሚያ ቤት፣ አልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እና መሶበ ሲሚንቶ ፋብሪካ ይገኙበታል።

መስሪያ ቤቱ የድርጅቶቹን የባንክ ሂሳብ እንዲታገድ ያደረገው፤ በ2007 ዓ.ም. በተሻሻለውን የጸረ- ሙስና ህግ፣ በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ማቋቋሚያ አዋጅ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በ2005 ዓ.ም በወጣ አዋጅ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን በመጥቀስ ነው። ድንጋጌዎቹ መስሪያ ቤቱ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እስኪያወጣ ደረስ የባንክ ሂሳቦቹ ታግደው እንዲቆዩ የሚያስችሉ ናቸው።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ የጠቀሰው የተሻሻለው የጸረ-ሙስና ልዩ የሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ ድንጋጌ “አግባብ ያለው አካል የበላይ ኃላፊ፤ ንብረቱ እንደሚባክን ሲያምንበት፤ በፍርድ ቤት የእግድ ትዕዛዝ እስኪያወጣ ድረስ ለ48 ሰዓት የሚጸና ጊዜያዊ የእግድ ትዕዛዝ መስጠት ይችላል” ይላል።
የፈደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለምርመራው ይረዳው ዘንድ የድርጅቶቹን የባንክ ሂሳብ እንቅስቃሴ የሚያመለክቱ ማስረጃዎች በአስቸኳይ እንዲላክለትም ባንኮችን ጠይቋል። ከዚህም በተጨማሪ ድርጅቶቹ በባንኮቹ ውስጥ በከፈቱት የባንክ ሂሳብ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት ያላቸውን የሀገር ውስጥ ገንዘብ፣ የከበሩ ማዕድናት፣ የውጭ ሀገር ገንዘብ እና በባንክ ውስጥ ያላቸው የአክሲዮን ድርሻ (ሼር) መጠን ማስረጃም አያይዘው እንዲልኩ ጥያቄ አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)