በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ድባጤ ወረዳ ባገረሸው ጥቃት ሶስት ሰዎች ቆሰሉ

በተስፋለም ወልደየስ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ በመተከል ዞን፤ ድባጤ ከተማ ዛሬ ረፋዱን በታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ ሶስት ሰዎች መቁሰላቸውን የወረዳው የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በጽህፈት ቤቱ የሚዲያ ልማት ባለሙያ የሆኑት አቶ ጥላሁን ወየሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ በከተማይቱ አንግቶክ በተባለ ቀበሌ የተኩስ እሩምታ መሰማት የጀመረው ዛሬ ሰኞ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ገደማ ጀምሮ ነው።

በተኩሱ የቆሰሉ ሶስት ሰዎች ወደ ድባጤ ከተማ ጤና ጣቢያ መወሰዳቸውን የሚገልጹት ባለሙያው፤ “የመሳሪያ ድምጽ አለ። አሁንም ቢሆን በህዝቡ ውስጥ የተረጋጋ መንፈስ አይታይም” ሲሉ በአካባቢው ስላለው ሁኔታ አስረድተዋል። ባለሙያው ተኩሱን የከፈቱት “ታጥቀው የገቡ ጸረ -ሰላም ኃይሎች ናቸው” ብለዋል። 

“እነሱ ናቸው እንግዲህ ማህበረሰቡን አደራጅተው ለተለያዩ ሁከት እና ብጥብጥ እየዳረጉ ያሉት። [የአካባቢው] ማህበረሰብ ያልተማረ እንደመሆኑ መጠን በተለያየ ገንዘብ እና መሰል ነገሮች እየተታለሉ ጫካ ገብተው፣ አድፍጠው ህዝቡን እየተዋጉ ነው ያሉት” ሲሉ ባለሙያው ስለ ጥቃቱ አድራሾቹ ማንነት አብራርተዋል። 

በአሁኑ ሰዓት ተኩስ ወደተሰማበት አካባቢ የመከላከያ ሰራዊት መሰማራቱን አቶ ጥላሁን ተናግረዋል። የመከላከያ ሰራዊት በስፍራው ከደረሰ በኋላ “አንጻራዊ ሰላም” እንደሚታይም ጠቁመዋል። 

“ታጥቀው የገቡ ጸረ -ሰላም ኃይሎች ናቸው ማህበረሰቡን አደራጅተው ለተለያዩ ሁከት እና ብጥብጥ እየዳረጉ ያሉት”

አቶ ጥላሁን ወየሳ – የድባጤወረዳ የመንግስት ኮሙዩኔኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ባለሙያ

በድባጤ ወረዳ ካለፈው ሳምንት አርብ ጀምሮ የታጠቁ ኃይሎች ጥቃት ሲያደርሱ እንደነበር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግስት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ከቀናት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል። በጥቃቱ የድባጤ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደበሊ በልጋፎ ጭምር መቁሰላቸውን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረው ነበር።  

በወረዳው ውስጥ በሚገኙት ውብግሽ፣ ያምፕ እና ቂዶ ቀበሌዎች ውስጥ ከቀናት በፊት ጥቃቶች መፈጸማቸውን የገለጸው የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት፤ በዚህም “የንጹሃን ዜጎችን ህይወት አልፏል” ብሏል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ትላንት እሁድ ባወጣው መግለጫ፤ በድባጤ ወረዳ ከወንበራ ወደ ቻግኒ፤ ቅዳሜ ህዳር 5 ፤ በመጓዝ ላይ በነበረ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ በተፈጸመ ጥቃት በትንሹ 34 ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በአውቶብሱ ላይ ጥቃት ፈጽመው፣ “ንጹሃን ሰዎችን ገድለዋል” ያላቸውን 16 ታጣቂዎች “መደምሰሱን” በትላንትው ዕለት አስታውቋል። ጥቃት አድራሾቹ  “የሕወሓት የጥፋት ተልዕኮ አስፈጻሚ ሽፍታዎች ናቸው” ሲል የክልሉ ፖሊስ ወንጅሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)