በተስፋለም ወልደየስ
በትግራይ ያለው ውጊያ በንግግር እንዲፈታ በቀጠና፣ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ መሪዎች የማሸማገል ጥያቄ ቢያቀርቡም፤ በኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ በህወሓት በኩል የሽምግልና ፍላጎት እንደሌለ የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲቦር ናዥ ተናገሩ። የህወሓት አመራሮች ውጊያውን ሲጀምሩ የተከተሉት ታክቲክ፤ “ካቀዱት ተቃራኒውን ውጤት አምጥቷል” ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል።
በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት ቲቦር ናዥ ይህን የተናገሩት በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ትላንት ሐሙስ ምሽት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው የጥያቄ እና መልስ ቆይታ ነው። በስልክ ኮንፈረንስ አማካኝነት በተካሄደው እና “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በቀጥታ በተከታተለችው የጋዜጠኞች የገለጻ መርሃ ግብር ላይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ማይክል ራይነርም ተሳትፈዋል።
ግማሽ ሰዓት ገደማ በወሰደው በዚሁ ገለጻ ላይ በአሜሪካውያን ጋዜጠኞች ተደጋግሞ ከተነሱት ጥያቄዎች አንዱ የሽምግልና ጉዳይን የሚመለከተው ነው። ምክትል ሚኒስትሩ “የሽምግልና ጉዳይ” በትግራይ ውጊያ እንደተቀሰቀሰ ወዲያውኑ የመጣላቸው ጥያቄ እንደሆነ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ለምን በአውሮፕላን ተሳፍረው ወደ አካባቢው በቶሎ እንዳልሄዱ መጠየቃቸውንም አንስተዋል።
“ሽምግልና ታክቲክ መሆኑን አጽንኦት መስጠቱ በጣም አስፈላጊ ነው። ወደ ግብ የሚያደርስ መንገድ እንጂ በራሱ ግብ አይደለም” ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ “የእኛ ግብ ግጭቱ ቶሎ እንዲያበቃ፣ ሰላም ወደነበረበት እንዲመለስ እና የሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ ነው” ሲሉ መንግስታቸው ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች ዘርዝረዋል።
ሽምግልና ጥቅም ላይ የሚውለው በሂደቱ የሚሳተፉ ሰዎች አሊያም ወገኖች ለዚያ ዝግጁ ሲሆኑ መሆናቸውን የጠቀሱት ቲቦር ናዥ፤ በዚያን ወቅት አሜሪካ “በፍጥነት” እንደምትገኝ አስረድተዋል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን በሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በኩል ሂደቱን ያለመፈለግ ሁኔታ እንደሚስተዋል ጠቁመዋል።
“በርከት ያሉ የቀጠናው መሪዎች፣ የአህጉሩ መሪዎች እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ መሪዎች የማሸማገል ሀሳብ ይዘው [ሁለቱንም ወገኖች] ቀርበው ነበር። እንደሰማናቸው ነገሮች ከሆነ፤ በዚህ ጊዜ ማናቸውም ወገኖች ለሽምግልና ፍላጎት የላቸውም” ብለዋል።
ይህንኑ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትሩን አባባል፤ የሀገራቸው አምባሳደርም አረጋግጠዋል። ባለፈው ሳምንት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ከህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር መነጋገራቸውን ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ በውይይታቸው ወቅት ሽምግልና፣ ውይይት ወይም ድርድር አሁን ያለውን ውጊያ ሊያስቆም ይችል እንደው እንዳነሱባቸው ጠቅሰዋል።
“በወቅቱ በነበረው ንግግራችን ላይ ይህን አካሄድ በተመለከተ ምንም ዓይነት የተቀባይነት መንፈስ አልነበረም። በሁለቱም ወገኖች በኩል ወታደራዊ ግጭቱን የመቀጠል ጠንካራ ቁርጠኝነት ነው ያለው። በዚያን ጊዜ ማናቸውም ወገኖች የድርድር አሊያም የሽምግልና መፍትሔ የሚሆን መሰረት ሊኖር እንደሚችል አልተሰማቸውም” ሲሉ አምባሳደሩ አብራርተዋል።
አሜሪካ ሁለቱ ተፈላሚ ወገኖች ወደ ሽምግልናው መድረክ እንዲመጡ፤ በከፍተኛ ባለስልጣኖቿ ደረጃ ግፊት ለማድረግ አስባ እንደው በአሜሪካው የኤቢሲ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ በኩል ጥያቄ ቀርቦ ነበር። ጋዜጠኛው የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር በቅርቡ ተነጋግረው ያውቁ እንደው ጠይቋል።
ፖምፒዩ በተለያዩ ሀገራት ጉብኝት ላይ እያደረጉ መሆናቸውን የጠቀሱት ምክትላቸው፤ ሆኖም ስላለው ሁኔታ ከእርሳቸው ጋር እንደሚወያዩ ተናግረዋል። የክስተቶችን አካሄድ ተከትሎ አሜሪካ በከፍተኛ ባለስልጣን ደረጃ ልታደርገው ስለምትችለው ተሳትፎ በውይይታቸው እንደተነሳም አመልክተዋል።
“እንደማስበው ከእነዚህ ሁለት ወገኖች ጋር የሰራ ማንም አካል፤ ምንም መፈጸም እንደሚፈልጉ እና መቼ ያንን ማድረግ እንደሚፈልጉ ያላቸውን በጣም በጣም ጠንካራ አስተያየት ሊያደንቅ ይችላል” ሲሉ በኢትዮጵያ መንግስትም እና በህወሓት አመራሮች በኩል የሚታየውን በአቋም የመጽናት አካሄድ አንስተዋል።
የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን አሁን ያለው ውጊያ የኢትዮጵያን መፍረስ ሊያስከትል እንደሚችል ለ“ፋይናንሻያል ታይምስ” በዚህ ሳምንት የተናገሩትን የጠቀሰው የኤቢሲ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ፤ በዚህ ፍራቻ ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲነግሩት የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትሩን ጠይቆ ነበር።
በትግራይ ለተቀሰቀሰው ግጭት መነሾ ህወሓትን ተጠያቂ ያደረጉት ቲቦር ናዥ፤ የፓርቲው አመራሮች “ግጭቱን ሲጀምሩ ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል እና ነጻ ሀገር ለመመስረት አስበው አልነበረም” ብለዋል። ለዚህም ለሶስት ዓመታት በአምባሳደርነት ያገለገሉባትን የኢትዮጵያን ሕገ-መንግስት በማስረጃነት አጣቅሰዋል። በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ክልሎች በሰላማዊ መንገድ መገንጠል እንደሚችሉ መደንገጉን አንስተዋል።
“እንደሚመስለኝ የእነርሱ ታክቲክ ቀድመው ካቀዱት ተቃራኒ የሆነ ውጤት አምጥቷል። ይህ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመደገፍ፤ ለጊዜውም ቢሆን ኢትዮጵያውያንን አንድ ላይ ያመጣ ሆኗል። ምክንያቱም የኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ስሜትን በእውነትም ቆስቁሷል”
ቲቦር ናዥ-የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
የህወሓት አመራሮች ሰበበ ድርጊትን በእርግጠኝነት መናገር እንደሚያስቸግር የገለጹት ምክትል ሚኒስትሩ፤ ሆኖም የሚመስለው “ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ከስልጣን በማስወገድ፤ ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ ውስጥ በቁንጮነት ወደቆዩበት ወሳኝ ቦታ ራሳቸውን ለመመለስ ያደረጉት ነው” ብለዋል።
“እንደሚመስለኝ የእነርሱ ታክቲክ ቀድመው ካቀዱት ተቃራኒ የሆነ ውጤት አምጥቷል። ይህ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመደገፍ፤ ለጊዜውም ቢሆን ኢትዮጵያውያንን አንድ ላይ ያመጣ ሆኗል። ምክንያቱም የኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ስሜትን በእውነትም ቆስቁሷል። እነዚህ በጎ ስሜቶች ይቆያሉ የሚል ተስፋ አለኝ” ሲሉ የህወሓት አካሄድ በሌላው የሀገሪቱ ክፍል የፈጠረውን ስሜት ለማስረዳት ጥረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)