ባህር ዳር ለሁለተኛ ጊዜ በሮኬት ተጠቃች

የአማራ ክልል መንግስት መቀመጫ በሆነችው ባህር ዳር ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ የሮኬት ጥቃት መድረሱን የክልሉ መንግስት አስታወቀ። በህወሓት ኃይል እንደተተኮሰ የተነገረው የሮኬት ጥቃት በከተማይቱ የተፈጸመው ከለሊቱ ሰባት ሰዓት ከ40 ገደማ መሆኑን የክልሉን መንግስት የጠቀሰው የአማራ ቴሌቪዥን ዘገባ ያመለክታል። በጥቃቱ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ እስካሁን በግልጽ አልታወቀም ተብሏል።

ባለፈው ሳምንት አርብ በባህር ዳር አውሮፕላን ተመሳሳይ ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል። ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደው ህወሓት፤ ወደ ባህር ዳር የተተኮሰው “ሚሳኤል” መሆኑን ገልጾ ነበር። የኢትዮጵያ መንግስት በበበኩሉ ጥቃቱ የተፈጸመው በሮኬት መሆኑን እና በጥቃቱም የደረሰው ጉዳት “መጠነኛ” እንደነበር በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

የህወሓት ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በጥቃቱ ማግስት በሰጡት መግለጫ፤ በባህር ዳር እና ጎንደር ከተሞች የተፈጸመው ጥቃት በትግራይ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ለተካሄደው የአየር ድብደባ የተሰጠ “አጸፋዊ ምላሽ ነው” ማለታቸው አይዘነጋም። በሁለቱ ከተሞች ተመሳሳይ ጥቃቶች ወደፊትም ሊፈጸሙ እንደሚችሉ አስጠንቅቀው ነበር።

የህወሓት ኃይል ወደ ባህር ዳር፣ ጎንደር እና አስመራ ከተሞች ሚሳኤሎች ማስወንጨፉን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ውግዘት ደርሶበታል። ድርጊቱን አጥብቀው ከኮነኑት መካከል የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ይገኙበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)