የቀድሞ የወላይታ ዞን አመራሮች ክስ ተመሰረተባቸው

በተስፋለም ወልደየስ 

አምስት የቀድሞ የወላይታ ዞን አመራሮች እና ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ተመሰረተ። ከአመራሮቹ ጋር በአንድ መዝገብ የጊዜ ቀጠሮ ጉዳያቸው ሲታይ የቆዩ 13 ተጠርጣሪዎች በነጻ እንዲለቀቁ በፍርድ ቤት ተወስኖላቸዋል። 

ዛሬ ክስ እንደተመሰረተባቸው ከተገለጸላቸው አመራሮች ውስጥ የቀድሞው የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ፣ ምክትላቸው ጎበዜ ጎዳና እና የዞኑ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ ጥበቡ ዩሃንስ ይገኙበታል። የደቡብ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በአመራሮቹ ላይ ክስ መመስረቱን የገለጸው ዛሬ ሰኞ ህዳር 14 ላስቻለው የወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው። 

የአምስቱን የቀድሞ አመራሮች ጨምሮ የ20 ተጠርጣሪዎችን የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ባለፈው ጥቅምት 30 በነበረው የችሎት ውሎው፤ የደቡብ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ ለመመስረት የጠየቀውን 15 ቀናት ፈቅዶ ነበር። የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዛሬ ለችሎት እንደገለጸው፤ በሰባት ተጠርጣሪዎች ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ የተመሰረተው ህዳር 10፤ 2013 ነው። 

ዛሬ ክስ እንደተመሰረተባቸው ከተገለጸላቸው አመራሮች ውስጥ የቀድሞው የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ እና የዞኑ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ ጥበቡ ዩሃንስ ይገኙበታል

ክሱ በፌደራል ደረጃ ቢከፈትም፤ የክስ ሂደቱ ግን በፌደራል ተዘዋዋሪ ችሎት አማካኝነት በወላይታ ሶዶ ከተማ እንደሚታይ የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል። በዚህም መሰረት በቀድሞዎቹ አመራሮች እና ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ የተመሰረተው ክስ በዛሬው የችሎት ውሎ ሳይነበብ ቀርቷል። ክሱን ለማንበብም ለእሁድ ህዳር 20፤ 2013 ቀጠሮ ተሰጥቷል። 

“ሕገ መንግስቱን እና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በመናድ” ተጠርጥረው ከታሰሩት እና ክስ ከተመሰረተባቸው ውስጥ ሶስቱ በወላይታ ዞን የብልጽግና ጽህፈት ቤት በአመራርነት ተመድበው ሲሰሩ የነበሩ ናቸው። ከአመራሮቹ ውጭ ያሉት ሁለት ተጠርጣሪዎች፤ መጀመሪያ በተፈቀደላቸው ዋስትና ከእስር ከተፈቱ በኋላ በተከታታይ በነበሩ የጊዜ ቀጠሮ የችሎት ውሎዎች ያልተገኙ መሆናቸው ተነግሯል። 

ሁለቱ ተጠርጣሪዎች እያንዳንዳቸው በ100 ሺህ ብር ዋስትና ቢለቀቁም በችሎት ባለመገኘታቸው ያስያዙት የዋስትና ገንዘብ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን የወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው የችሎት ውሎው ወስኗል። በሌሉበት መከሰሳቸው የተነገረው ሁለቱ ተጠርጣሪዎች፤ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ መምህራኖቹ አቶ አሸናፊ ከበደ እና አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ናቸው። አቶ አሸናፊ በወላይታ የክልልነት ጥያቄ ላይ ባላቸው የአራማጅነት ሚናቸው ይበልጥኑ ይታወቃሉ።       

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ መምህሩ አቶ አሸናፊ ከበደ በወላይታ የክልልነት ጥያቄ ላይ ባላቸው የአራማጅነት ሚናቸው ይበልጥኑ ይታወቃሉ

ክስ ከተመሰረተባቸው ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውጭ ያሉ ግለሰቦች በነጻ እንዲለቀቁ የተወሰነው በተጠረጠሩበት ወንጀል “ምንም አይነት ማስረጃ አለመገኘቱን” ለፍርድ ቤት ካስታወቀ በኋላ ነው። በዚህ መሰረት ጥቅምት 10፤ 2013 በዋለው ችሎት የ30 ሺህ ብር ዋስትና የተከበረላቸው አምስት ተጠርጣሪዎችን ጨምሮ 13 ግለሰቦች ክስ ሳይመሰረትባቸው በነጻ ተሰናብተዋል። በነጻ ከተሰናበቱት ውስጥ የወላይታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉነህ ወልደጻዲቅ፣ የዞኑ የፍትህ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ምህረት ቡኬ እና የወላይታ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ክፍል ዲን አቶ ተከተል ላቤና ይገኙበታል።

በዛሬው ችሎት በእስር ላይ የሚገኙ አምስቱን የቀድሞ አመራሮች ጨምሮ፤ 15 ተጠርጣሪዎች መገኘታቸውን ችሎቱን የተከታተሉ አንድ ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የፍርድ ቤት ሂደቱ በግልጽ ችሎት እንደሚታይ ቢገለጽም፤ እንደከዚህ ቀደሙ የችሎት ውሎዎች ሁሉ ታዳሚያን እንዳልተገኙ አስረድተዋል። በዛሬው የችሎት ውሎ የፌደራል ፖሊስ እና የደቡብ ክልል ልዩ ኃይሎች የጸጥታ ቁጥጥር ሲያደርጉ ቢታይም፤ ከዚህ በፊት እንደነበሩ ችሎቶች “ጥብቅ” እንዳልነበር ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)  

[ይህ ዘገባ ዘግየት ብሎ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]