ከኮሮና ቫይረስ ጋር የሚደረገውን ፍልሚያ የሚመራ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ተቋቋመ

በሐይማኖት አሸናፊ

ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን ለማሸነፍ የምታደርገውን ትግል በበላይነት የሚያዝ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የሚኒስትሮች ኮሚቴ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም በወጣው ደንብ ተቋቋመ። ኮሚቴው ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖ ለክልል እና ለከተማ አስተዳደሮች መመሪያ እና ትዕዛዝ የመስጠት ስልጣን ተሰጥቶታል።

ኮሚቴው የኮቪድ-19 ስርጭት ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውንም ጉዳት ለመቀነስ የሚሰራውን ስራ በበላይነት የሚመራ እንዲሁም የሚያስተባብር ሲሆን ስለቫይረሱ መረጃ የመሰብሰብ፣ የመተንተን እና በዛም ላይ ተመስርቶ አቅጣጫ የመስጠት ስልጣን አለው። በስሩም በፌደራል፣ በክልል እንዲሁም በወረዳ የሚቋቋሙ ንኡሳን ኮሚቴዎች እንደሚኖሩት ተገልጿል።

የሚኒስትሮች ኮሚቴው ለንኡስ ኮሚቴዎቹ መረጃ እና ማስረጃ የመስጠት፣ ሪፖርታቸውን የመገምገም ብሎም በዚህ ላይ በመመስረት አቅጣጫ የመስጠት ስልጣን ዛሬ በፀደቀው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ አማካኝነት ተሰጥቶታል። የቫይረሱ ስርጭት እየሰፋ የሚሄድ ከሆነም “ተጨማሪ ክልከላዎችን መጣል አስፈላጊ ነው” ብሎ ባመነ ጊዜ ኮሚቴው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል።

ደንቡ ምን ክልከላዎችን ይይዛል?

አራት ክፍሎች ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ የማስፈፀሚያ ደንብ ክልከላን የሚያስቀምጥ፣ ግዴታ የሚጥል፣ የአስፈፃሚ አካላትን ክንውን እንዲሁም ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘ ነው፡፡ በደንቡ መሰረት ማንኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄዱ ስብሰባዎች ከአራት ሰው በላይ ማሳተፍ እንዳይችሉ ገደብ ተጥሏል። በአራቱ ሰዎች መካከልም ቢሆን የሁለት የአዋቂ እርምጃ ርቀት እንዲጠበቅ ደንቡ ያስገድዳል።  

የበርካታ ሰዎችን ስብሰባ የከለከለው ደንብ፤ አስገዳጅ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ በሚኒስትሮች ኮሚቴ አሊያም ውክልና በሚሰጣቸው ንኡሳን ኮሚቴዎች ፍቃድ ሊሰጥ እንደሚችል ደንግጓል። ደንቡን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ የሰጡት የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አዳነች አበቤ ቀብር እና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች ሲኖሩ ጉዳዮቹ እየታዩ እንደሚፈቀድ ተናግረዋል፡፡

ደንቡ ማንም አሰሪ በዚህ ወቅት የስራ ውል ማቋረጥ ወይም ሰራተኛ መቀነስ እንደማይችል መከልከሉን ያስታወቁት ጠቅላይ ዓቃቤ ህጓ ሆኖም የቤት ኪራይን መቀነስ ወይም መተው ግዴታ ያለመሆኑን አመልክተዋል፡፡ ነገር ግን በደንቡ መሰረት ማንም አከራይ ተከራዩን በዚህ ወቅት “ማባረር አይችልም” ብለዋል፡፡

ታራሚዎች ስንቅ ከመቀበል ውጪ ማንንም በአካል የማያገኙ  ሲሆን ከጠበቆቻቸው ጋር ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲነጋገሩ ግን ደንቡ ፈቅዷል፡፡ በአካል የመማር ማስተማር ሂደትን፣ ለአዋቂም ሆነ ለህፃናት በመጫወቻ ስፍራዎች ተገኝቶ መጫወትን የከለከለው ደንቡ በእጅ መጨባበጥ ሰላምታንም በህግ አግዷል፡፡ የአገር አቋራጭ መኪናዎች ከአቅማቸው በግማሽ ቀንሰው እንዲሰሩም አዝዟል፡፡

በሚኒስትሮች ኮሚቴ ፈቃድ ከተሰጠው አካል ውጪ ማንም ሰው የክልል ወይም የፌደራል መንግስቱን ወክሎ ኮቪድ19ን የተመለከተ መግለጫ መስጠት ደንቡ ከልክሏል። ቫይረሱን ለመከላከል የሚወጡ ህጎችን በተመለከተ ወይም በህክምና ባለሞያዎች የሚሰጡ ማብራሪያዎች እና በጤና ሚኒስቴር በየቀኑ የሚሰጡ መግለጫዎች ግን ክልከላ አልተደረገባቸውም።

መሰረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት አገልግሎት አሊያም ስራቸውን ያለመስራት፣ ማቋረጥ፣ ማስተጓጎል እና መሰል ተግባራትን መፈፀም የተከለከለ መሆኑን ደንቡ አስቀምጧል። የኮሮና ቫይረስ እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ማህበረሰቡ እንዳይረጋጋ የሚያደርግ እና በማህበረሰቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና የሚፈጥር ማናቸውንም መረጃ ማሰራጨት መከልከሉም በደንቡ ተደንግጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)