በሐይማኖት አሸናፊ
ኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎችን ቁጥር አለመደበቋን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ተናገሩ፡፡ ነገር ግን ቁጥሩ አሁን ያለው ብቻ ነው ብሎ በእርግጠኝነት መናገር እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ሊያ ይህን የገለጹት ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገር ደረጃ እየተደረገ ባለው ዝግጅት እና እየተከናወነ ስላለው ተግባር ትላንት፤ እሁድ ሚያዝያ 4፤ 2012 በሰጡት ሰፊ ማብራሪያ ነው፡፡ ሚኒስትሯ ከህብረተሰቡ በፌስ ቡክ ገጻቸው ለተቀበሏቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ በርካታ ጉዳዮችን ዳስሰዋል፡፡ በፌስ ቡክ በቪዲዮ በቀጥታ በተሰራጨው በዚህ ማብራሪያ ስለ ህክምና ባለሙያዎች የደህንነት ሁኔታ፣ ለታማሚዎቸ እየቀረበ ስላለው ህክምና፣ ከለይቶ ማቆያ እስከ ሆስፒታል ስላሉ ተቋማት፣ ስለ ህክምና ግብዓቶች ለተነሱ ጥያቄዎች ሚኒስትሯ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ የዳሰሳ ምልከታ፣ የፈጣን ቡድን ምላሽ መዘግየት፣ ምርምራ ስለሚካሄድባቸው ቦታዎች ማነስ፣ “በኢትዮጵያ ተገኝቷል” ተብሎ ስለነበረው የኮሮና ቫይረስ መድኃኒት፣ በበሽታው ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ስለሚደረግላቸው የቀብር ስነ ስርዓት በማብራሪያው ተነስቷል፡፡ በኢትዮጵያ በምርመራ ከተገኙ ታማሚዎች በርካታዎቹ ከዱባይ መምጣታቸው መረጋገጡን ተከትሎ “የዱባይ በረራ ለምን አይዘጋም?” የሚል ጥያቄም ለሚኒስትሯ ቀርቦላቸዋል፡፡
የተደበቀ እውነት አለን?
ዶ/ር ሊያ ሶስት ሺህ ሰው ገደማ በተከታተለው የቀጥታ ማብራሪያቸው አጽንኦት ሰጥተው ያነሱት ጉዳይ “በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተጠቃው ሰው ይሄ ብቻ ነውን?” በሚል ስለሚነሳው ጥያቄ ነው፡፡ “ያልተነገረ ወይም ያልተደበቀ እውነት አለ ወይ?” የሚል ሀሳብ ያዘሉ ጥያቄዎችን መመልከታቸውን የተናገሩት የጤና ሚኒስትሯ “ቁጥሩን በመደበቅ እንደ ሀገር ምንም የምንጠቀመው ነገር የለም” ሲሉ ምላሸ ሰጥተዋል፡፡
“እንደ ሀገር ቁጥር ልንደብቅበት የምንችለው ምንም ምክንያት የለም፡፡ እርዳታ ለማግኘት አይጠቅመንም፡፡ ለመከላከልም አይጠቅመንም፡፡ በሽታውንም፣ ወረርሽኙንም ለመቆጣጠር አይጠቅመንም” ያሉት ዶ/ር ሊያ እንደውም ይበልጥ ሊጠቅም የሚችለው የበለጠ ቁጥርን በምርምራ አግኝቶ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
“ይሄንን ስንል ’71 ብቻ ነው፤ እርግጠኛ ነን’ ብለን የምንናገረው አይደለም፡፡ ግን እኛ በሰራናቸው፣ እስካሁን ባደረግናቸው ምርመራዎች ከዚህ ቁጥር በላይ አላገኘንም፡፡ ያገኘነውን በየዕለቱ ለማህብረሰቡ በየዕለቱ እያሳወቅን ነው” ብለዋል፡፡ ሚኒስትሯ ማብራሪያውን ከመስጠታቸው ሰዓታት አስቀድመው ባወጡት ዕለታዊ መግለጫ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 71 መድረሱን አስታውቀው ነበር፡፡ ከመግለጫቸው በፊት በነበረው 24 ሰዓት ብቻ 286 የላብራቶሪ ምርመራ መካሄዱን የገለጹት ዶ/ር ሊያ በምርምራው ሁለት ተጨማሪ ሰዎች “በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል” ብለዋል፡፡
ምርመራው ለምን አነሰ?
የቫይረሱ ምርመራ ቁጥር ማነስን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ከዚህ በኋላ የምርመራ ቁጥር ለመጨመር መታሰቡን ገልፀዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ምርምራ ሲጀመር ናሙና ወደ ደቡብ አፍሪካ እየተላከ እንደነበር የጤና ሚኒስትሯ አስታውሰዋል፡፡ ከጥር 30 ጀምሮ በሀገር ውስጥ መደረግ የጀመረው ምርመራ በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ውስጥ ባለ አንድ የምርምራ ቦታ ብቻ ረዘም ላለ ጊዜ ሲከናወን መቆየቱንም ጠቅሰዋል፡፡ አሁን በኢንስቲትዩት ውስጥ ብቻ ያለው የምርምራ ቦታ ከአንድ ወደ 3 ማደጉን አስረድተዋል፡፡
በመዲናይቱ አዲስ አበባ የምርመራ ቦታዎቹ 3 መድረሳቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ በአራት ክልሎች ውስጥ በአሁኑ ወቅት በ7 ቦታዎች ምርመራዎች እየተካሄዱ ነው ብለዋል፡፡ በቅርቡ ስራ የሚጀመሩ ተጨማሪ ሁለት መኖራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ በመላው ሀገሪቱ በ9 የተለያዩ የምርመራ ማዕከሎች ስራ ለመጀመር የመጨረሻ የማረጋገጫ (verification) ምዕራፍ ላይ መድረሳቸውን አብራርተዋል፡፡ በየክልሉ የሳንባ ምች (ኒሞኒያ) ምልክት የሚያሳዩ ዜጎችን በመለየት እና የውጪ ጉዞ ያላቸውን በመለየት ሰፊ የምርመራ ስራ መሰራት መጀመሩን ገልፀዋል፡፡
“ነገር ግን በክልሎች ያሉ የመመርመሪያ ማሽኖች የሚፈለገውን ውጤት የሚሰጡ አይደለም፤ ይህም በማሽኖቻችን መለያየት የመጣ ችግር ነው” ብለዋል። ይህንን በማሻሻልም በቅርቡ የመመርመር አቅምን ለመጨመር መታሰቡንም ተናግረዋል፡፡ በሽታው ማህበረሰቡ ውስጥ መግባቱን ለማወቅ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ወይም የጉዞ ታሪክ ባይኖርም እንኳን ምርመራዎች ከዚህ በኋላ እንደሚካሄዱም አመልክተዋል፡፡
የህክምና ግብዓቶች ነገር
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱ ከተነገረ ወዲህ አነጋጋሪ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የህክምና ግብዓቶች ጉዳይ ነው፡፡ በርከት ያሉ የህክምና ባለሙያዎች ራሳቸውን የሚከላከሉባቸው አልባሳት እና የፊት መሸፈኛ በቅጡ ለማግኘት መቸገራቸውን ሲናገሩ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል፡፡ የህክምና ግብዓቶች እጥረት እንዳለ ዶ/ር ሊያም አልሸሸጉም፡፡ ያለውን ያክል ግን በክልል ደረጃ ለማቅረብ እየተሞከረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የህክምና ባለሙያዎች ራሳቸውን ከበሽታው የሚከላከሉባቸው መሳሪያዎች አቅርቦት ቅድሚያ የሚሰጠው ሲሆን ቀጥሎም በኦክስጂን እና በጽኑ ህሙማን መርጃ ክፍሎች (ICU) የሚታዩ የግብዓት እጥረቶችን ለማቃለል ጥረት እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ለሁለት አመት ጥቅም ላይ ይውል የነበረው የፊት መሸፈኛ ክምችት ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር በተያያዘ ለሶስት ወር ያክል እንኳን የማይበቃ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
“ኤን 95” የተሰኘው እና ከ95 በመቶ በላይ ቫይረሱን የሚከላከለው የፊት መሸፈኛ እጥረት እንዳለ የጤና ሚኒስትሯ ገልፀዋል፡፡ ይህን አይነት የፊት መሸፈኛ በቫይረሱ የተጠረጠሩ፣ ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጡ እና ቲቢን ጨምሮ ሌሎች ተመሳሳይ በሽታን የሚያክሙ ሃኪሞች ቅድሚያ በመስጠት እንዲጠቀሙ ዘንድ በፕሮቶኮል መወሰኑን ተናግረዋል፡፡ ሌሎች የህክምና ባለሙያዎች እና አጋዥ የሆስፒታል ሰራተኞች መደበኛውን የሰርጂካል እንዲሁም የሜዲካል የፊት መሸፈኛ እንዲጠቀሙ ውሳኔ መተላለፉንም አስታውቀዋል፡፡ የኮሮና ወረርሽን ከተከሰተ ወዲህ ሶስት ሚሊዮን ሰርጂካል የፊት መሸፈኛዎች ለተቋማት ተሰራጭተዋል ብለዋል፡፡
ከትላንት በስቲያ የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች የፊት መሸፈኛ መጠቀም ግዴታ ማድረጉን ያታወሱት ዶ/ር ሊያ “ማስኮቻችን ሙሉ በሙሉ ቫይረሱን የሚከላከሉ ሳይሆኑ በተለያየ መጠን የሚከላከሉ ስለሆኑ አሁንም የአካላዊ ርቀትን መጠበቅ ካልተቻለ የፊት መሸፈኛ ማድረጉ ብቻውን ማስተማመኛ አይሆንም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከኮሮና ጋር በተያየዘ ከውጭ የሚገቡ ማንኛውም ግብዓቶች ከቀረጥ ነፃ እንዲሆኑ መወሰኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ በአገር ውስጥ ለሚመረቱትም የተለያየ ማበረታቻ እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የቢራ፣ የአረቄ እና የስኳር ፋብሪካዎች አልኮል እና ሳኒታይዘር እያመረቱ መሆኑን በምሳሌነት ያነሱት ዶ/ር ሊያ እንደውም አሁን እጥረቱ ተቀርፎ ምርቶቻቸውን እንዲወስዱላቸው ጥሪ እያቀረቡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በአልኮል እና ሳኒታይዘር አቅርቦት መሻሻል ቢታይም በሌሎች ግብዓቶች ግን አሁንም እጥረቱ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ያጋጠመውን እጥረት በግዢ እና በእርዳታ ለመፍታት እየተሞከረ መሆኑን ያስረዱት ዶ/ር ሊያ ግዢን በተመለከተ በዓለም ባንክ፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል እንዲሁም በመንግስት መዋቅር ግዚዎች እየተፈፀመ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ወሳኞቹ የህክምና እርዳታ መስጪያዎች እጥረት
በተለይም ሳንባን በሚያጠቃው የኮሮና ቫይረስ በጽኑ ለተጠቁ ሰዎች የህክምና እርዳታ ለመስጠት ኦክሲጅን እና ቬንትሌተር ወሳኝ ግብዓቶች እንደሆኑ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። የእነዚህ መሳሪያዎች እጥረት መኖሩን የገለፁት ዶ/ር ሊያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው በተለይም የኦክስጂን አቅርቦት ላይ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ የጽኑ ህሙማን መርጃ ክፍሎች (ICU) እና የቬንትሌተር መሰረተ ልማቶችን ቁጥር እና ጥራት ለመጨመርም ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ከሚጠቁ ሰዎች ውስጥ 20 በመቶ ኦክስጂን እና 5 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የቬንትሌተር ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ማመላከታቸውን ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል፡፡ አንድ ታካሚ የቬንትሌተር እርዳታ ላይ እንዲሆን ከተደረገ በኋላ በህይወት የመትረፉ እድል ከ25 በመቶ በታች መሆኑን፤ በአንጻሩ ህሙማን በኦክሲጅን ድጋፍ በሚደረግላቸው ወቅት ከፍተኛ ውጤት እየታየበት መሆኑን አነጻጽረዋል፡፡በዚህም ምክንያት ከፍተኛው ትኩረት ለኦክስጂን አቅርቦት መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡
ይህንን ታሳቢ ያደረገው የጤና ሚኒስቴር 3,223 ተጨማሪ የኦክስጂን ሲሊንደሮችን እና 1,000 የኦክስጂን መለኪያዎችን አሰራጭቷል፡፡ ‹በተለይም ለኮሮና ተብለው በተለዩ የህክምና ተቋማት ኦክስጂንን የማሟላት ስራ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ለመስራት እየተሞከረ ነው›› ያሉት ዶ/ር ሊያ የተለያዩ ፋብሪካዎችም ኦክስጂን ማምረት እንዲችሉ እና ይህንን እንዲደግፉ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙት ቬንትሌተሮች ቁጥር 435 መሆናቸውን የገለጹት የጤና ሚኒስትሯ ከእነዚህ ውስጥ የተበላሹት በርካታ ቁጥር ያላቸው እንደነበሩ አመልክተዋል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተ በኋላ 122 ቬንትሌተሮች ተጨምረዋል ብለዋል፡፡ ከአንድ የቻይና ኩባንያ ጋር በተደረገ ስምምነት፤ 400 ተጨማሪ ቬንትሌተሮችን ለመግዛት ስምምነት ላይ ተደርሶ፤ “200 የሚሆኑት በቅርቡ እንደሚገቡ ይጠበቃል” ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ የኳራንቲን፣ የለይቶ ማቆያ እና የህክምና ቦታዎችን የማዘጋጀት እና የማስፋፋት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ሊያ የተገኙ በርካታ ቦታዎችንም “ለህክምና እንዲሆኑ ለሟሟላት እየተሰራ ነው” ብለዋል፡፡ የጤና ሚኒስቴር በሽታው ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸው ወይም የውጪ ጉዞ የነበራቸው ዜጎችን በተለዩ ቦታዎች በማስቀመጥ ጤናቸውን እየተከታተለ ይገኛል፡፡ በለይቶ ማቆያነት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ቦታዎች ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና ሆቴሎች ናቸው፡፡
የህመም ስሜት ላላቸው ዜጎች ተገቢው ምርመራ እስኪደረግላቸው የሚቆዩባቸው የለይቶ ማቆያ ቦታዎች ደግሞ የሚገኙት በህክምና ቦታዎች ውስጥ ነው። ዶ/ር ሊያ “ይህንን የማስፋፋት እና አስፈላጊ ቁሳቁስ የማሟላት ስራ እየተሰራ ነው” ብለዋል፡፡
በበሽታው ለተጠቁ እና የህክምና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ህሙማን በቂ አልጋ ለማዘጋጀት መስሪያ ቤታቸው እያደረገ ያለውን ክንውንም አብራርተዋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ 4,800 የሆስፒታል አልጋዎች ለማሰራጨት የታቀደ ሲሆን 1,150 የሚሆነው አልጋ ተሰራጭቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ የወረርሽኙ ትልቅ ስጋት ባለባት አዲስ አበባ ከተማ ሚሊኒየም አዳራሸን ወደ ህክምና ማዕከል ለመቀየር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን እና በክልሎችም መሰል እርምጃዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
ለኮሮና ቫይረስ መድኃኒት ተገኝቷልን?
የኮሮና ቫይረስ እስካሁን ምንም አይነት መድሃኒት ባይገኝለትም በተለያዩ አገራት ተሞክረው የተሻለ ውጤት ያሳዩ መድኃኒቶች፤ በሽታው የሚያመጣቸውን ጉዳቶች ለመቀነስ ስራ ላይ እየዋሉ መሆኑን ዶ/ር ሊያ ገልጸዋል፡፡ የወባ በሽታን ለማከም የሚውለው “ክሎሮኪን” እና የተለያዩ አይነት የባክቴሪያ ኢንፌክሽኖችን ለማከም የሚያገለግለው “አዚትሮማይሲን” የተሰኘው መድኃኒት በተለይም በሽታው ለጠናባቸው ታማሚዎች እየተሰጡ እንደሆነ ዶ/ር ሊያ ተናግረዋል፡፡ መድኃኒቶቹ “ሙሉ ለሙሉ ያድናል ባይባልም የተሻለ ውጤት ያመጣሉ” በሚል ጥቅም ላይ እንደዋሉ አስረድተዋል።
‹‹ፕሮቶኮሉ ላይ እንደ ዋና አሰራር ባይቀመጥም፤ [ታማሚዎች] በጣም የከፋ ደረጃ ላይ ሲደርሱ፤ እንደ አስፈላጊነቱ መጠቀም የተጀመረበት ሁኔታ አለ፡፡ በቅርቡ የአለም የጤና ድርጅት ከተለያዩ ሀገራት ጋር በእነዚህ መድሃኒቶች ላይ የክሊኒካል ሙከራ ስለጀመረ፤ እዚያ ውስጥ እኛም አንዱ አገር ሆነን፤ እነዚህን መድሃኒቶች እና ሌሎችም አብረው የሚጠኑትን እየተጠቀምን የጥናቱ አካል ከሆንን፤ የበለጠ እገዛ ያደርግልናል” ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያም የባህላዊ እውቀትን ከዘመናዊ እውቀት ጋር በማቀናጀት ለኮሮና መድኃኒት ለማግኘት “ስራ ተጀመረ እንጂ መድኃኒት አልተገኘም” ሲሉ ከዚህ ቀደም ሲዘዋወሩ የነበሩ የሚጣረሱ መረጃዎችን አጥርተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች በኢትዮጵያ ያሉ እጽዋትን በመውሰድ የኤች. አይ. ቪ ኤድስ መድኃኒት ለማግኘት ምርምር ጀምረው እንደነበር ያስታወሱት የጤና ሚኒስትሯ ይህም “ከክሊኒካል ሙከራ በማለፍ ወደ እንስሳት ሙከራ ተሻግሮ ነበር “ብለዋል፡፡
ይህንን ምርምር ሲያከናውኑ የቆየው ቡድን የኮሮና ቫይረስ ሲከሰት ፊቱን ወደዚያ በማዞር በተመሳሳይ ምርምር ሲያካሂዱ መቆይታቸውን እና የመጀመሪያውን የክሊኒካል ሙከራ ማለፋቸውን ዶ/ር ሊያ አስረድተዋል፡፡ “ገና ረጅም ርቀት ይቀራል፣ መድሃኒት ተገኝቷል የሚለው ማሰተካከያ ሊደረግበት ይገባል። ብዙ አገራት ምርምር እያደረጉ ሲሆን የእዚህ ምርምር አካል መሆን ጥሩ እድል ነው” ሲሉ አክለዋል፡፡
የዱባይ በረራ ጣጣ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ ከመጋቢት 9 ጀምሮ ከ80 በላይ በረራዎችን ያቋረጠ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያም ሌሎች አየር መንገዶች እንዳይመጡ ተከልክሏል፡፡ በኢትዮጵያ ከውጭ ሀገር ከመጡ መንገደኞች ላይ በተደረገው ምርመራ የኮሮና ቫይረስ በምርመራ የተገኘባቸው በርካታዎቹ ተጠቂዎች ከዱባይ መምጣታቸው ተረጋግጧል፡፡
ይህ እውነታ በበርካቶች ዘንድ “የዱባይ በረራ ለምን አይዘጋም?” የሚል ጥያቄን ወልዷል፡፡ ጥያቄ ለጤና ሚኒስትሯም ቀርቦላቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድም ሆነ በኤምሬትስ ወደ ዱባይ የሚደረግ በረራም ከመጋቢት 18 ጀምሮ መቆሙንም የጤና ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
ሳውዲ አረቢያ፣ ጂቡቲ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በርካታ ኢትዮጵያውያንን “ወደ አገር የመመለስ እና በግድ የማባረር ስራ እየሰሩ” መሆኑ ከሰሞኑን ትልቁ ተግዳሮት ፈጥሮባቸው እንደነበር ዶ/ር ሊያ ገልጸዋል፡፡ እነዚህን ዜጎች በኳራንቲን ለይቶ ለማቆየት ከባህል እና ቱሪዝም፣ ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት፣ ከፌደራል ፖሊስ እንዲሁም ከሰላም ሚኒስቴር በጋራ በመሆን በትብብር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
“አስገዳጅ ኳራንቲን” ከተጀመረ ሶስት ሳምንት ሲሆን ለዚህም ቁጥራቸው ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው ተብሏል፡፡ ማንኛውም ሰው ከኳራንቲን ከመውጣቱ በፊት ምርመራ መደረጉ በሽታውን ለማግኘት ትልቅ እድል መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ሊያ አብዛኛው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ቁጥርም ከኳራንቲኖች የተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
“ትኩረት ወደ ኮሮና ቫይረስ በመዞሩ ምክንያት ሌሎች የጤና ችግሮች በተለይም የእናቶች እና የህጻናት ሞት እንዳይጨምር ጎን ለጎን ስራዎች እየተሰሩ ነው” ብለዋል፡፡ መቆየት የሚችሉ የጤና ችግሮች በማቆየት ዋና ዋና የጤና ችግሮችን መመሪያ በማውጣት ከክልል እና ከፌደራል አካላት ጋር በመሆን ኤች. አይ/ ቪ ኤድስን ጨምሮ ቁልፍ ህክምናዎች ላይ ጉድለት አንዳይኖር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከኮሮና ጋር የሚደረገው ፍልሚያም በቀጣይ ለሀገሪቱ ጤና ስርአት መጠናከር ከፍተኛ ሚና አንደሚኖረው የገለፁት ዶ/ር ሊያ የምርምር ስራዎች፣ ለወረርሽኝ ምላሽ አሰጣጥ እና እየተሟሉ ያሉ የጤና መሰረተ ልማቶች በዘላቂነት ዘርፉን እንደሚያጠናክሩት ገልፀዋል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)