አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ማደስ መፈለጓን የሚያሳይ ፍንጭ ሰጠች

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማረቅ ፍላጎት እንዳላት ፍንጭ ሰጡ። ፕሬዝዳንቱ ዛሬ የተከበረውን የኤርትራን 29ኛ ዓመት የነፃነት በዓል በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት ሀገሪቱ በምትገኝበት ቀጠና “ዕርቅ በማውረድ እና ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለመፍጠር ተጫውታለች” ያሉትን ሚና አድንቀዋል።

“ኤርትራ ባለፈው ዓመት በአፍሪካ ቀንድ የተጫወተችውን አዎንታዊ ሚና በተለይም ከጎረቤቶቻችሁ ሰላም ለማውረድ እና ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለመፍጠር ያደረጋችሁትን ጥረት አደንቃለሁ” ብለዋል ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለኤርትራ ሕዝቦች ባስተላለፉት መልዕክት። “ከፍተኛ ባለስልጣኖቻችን፤ ባለፈው ዓመት እንዳደረጉት ሁሉ፤ በአገሮቻችን መካከል የታደሰ እና ፍሬያማ ወዳጅነት ለመፍጠር መስራታቸውን ይቀጥላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

አሜሪካ ከአስመራ ያላት ወዳጅነት የመለሳለስ ምልክት ያሳየው፤ ባለፈው አመት ግንቦት ወር፤ ኤርትራን ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ተባባሪ አይደሉም ከምትላቸው አገራት ዝርዝር ስታስወጣ ነበር። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኤርትራን ከዝርዝሩ ያስገባው ከአስራ ሁለት አመታት በፊት ሲሆን ከዚያ በኋላ የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ መንግሥት የሶማሊያውን አልሻባብ ይደግፋል በሚል ክስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማዕቀብ ተጥሎባታል። 

በሀገራቸው ላይ የሚቀርበውን በማጣጣል የሚታወቁት የኤርትራ ባለስልጣናት የአሜሪካ መሪዎች ለማዕቀቦቹ መጣል የተጫወቱትን ሚና እየጠቀሱ የከረሩ ተቃውሞዎች ሲያሰሙ ቆይተዋል። የኤርትራ መንግሥት በቢል ክሊንተን እና በባራክ ኦባማ አስተዳደሮች “አምባገነን” ተብሎ የተፈረጀ ሲሆን በሰብዓዊ መብት አያያዝም በብርቱ ሲተች ነበር። 

ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻከር ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ከሚባሉ ክስተቶች መካከል ኤርትራ ለሁለት ጊዜያት ያህል የአሜሪካ ኤምባሲ ሰራተኞች ማሰሯ ይጠቀሳል። ሰራተኞቹ ክስ ሳይመሰርትባቸው ለዓመታት በእስር እንዲቆዩ ተደርገው ነበር። የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID) በፕሬዝዳንት ኢሳይያስ መንግሥት ጥያቄ ከኤርትራ ጥሎ እንዲወጣ መደረጉም ይታወሳል። 

በአስመራ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አሁንም በስራ ላይ ቢሆንም ስራውን የሚያከናውነው በተሿሚ አምባሳደር መሪነት ሳይሆን በ“ቻርዥ ዲ አፌር” ደረጃ ነው። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ዕርቅ ካወረዱ በኋላ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ላይ ይከተል በነበረው ፖሊሲ የመለሳለስ ምልክቶች አሳይቷል። በመሥሪያ ቤቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ የሆኑት ቲቦር ናዥ በህዳር 2010 ወደ አስመራ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጋር መወያየታቸው የግንኙነታቸው መሻሻል ምልክት ተደርጎ ተወስዷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)