የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ጉባኤ በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ላይ ለመወያየት ለነገ አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ

በቅድስት ሙላቱ

የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ጉባኤ ለነገ እሁድ ሚያዝያ 3፤ 2013 አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ። ጉባኤው ስብሰባውን የጠራው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከክልሉ ውጭ የሚገኙ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚኖሩ የብሔረሰቡ አባላትን የመራጭነት ተሳትፎን በተመለከተ ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ  ነው። 

አስራ አራት አባላት ያሉት ጉባኤው በሐረሪ ክልል ምክር ቤት ስር የሚገኝ ነው። ጉባኤው በነገው ስብሰባው የምርጫ ቦርድ ውሳኔን የማይቀበል መሆኑን በአቋም ደረጃ እንደሚያስታውቅ ይጠበቃል ሲሉ የክልሉ መንግስት ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  በጉባኤ ውሳኔ ላይ በመመስረት በቀጣይ የሚቀመጡ አቅጣጫዎችን የሐረሪ ክልል ምክር ቤት የሚወስን መሆኑንም ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል።

ለነገው ስብሰባ መጠራት ምክንያት የሆነው የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ይፋ የተደረገው በትላንትናው ዕለት ነበር። ቦርዱ ውሳኔውን የሰጠው ከሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ፣ ከሐረሪ ህዝብ ክልል ምክር ቤት ጽህፈት ቤት፣ ከሐረሪ ሕዝብ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት እንዲሁም ከክልሉ ገዢ ፓርቲ ጽህፈት ቤት ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በደብዳቤ የቀረቡለትን ጥያቄዎች ከመረመረ በኋላ ነው።

ደብዳቤዎቹ፤ ባለፉት አምስት አገራዊ ምርጫዎች ላይ እንደተካሄደው ከሐረሪ ክልል ውጭ የሚኖሩ የብሔረሰቡ አባላት ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ የሚመረጡ ግለሰቦችን የመምረጥ መብት እንዳላቸው አንስተው፤ ቦርዱ በቀጣዩ ምርጫ በተመሳሳይ መልክ ሂደቱን እንዲያስፈጽም ጠይቀዋል። ቦርዱ ጥያቄውን ላቀረቡት አካላት በትላንትናው ዕለት በደብዳቤ በሰጠው ምላሽ፤ ከሕገ መንግስቱ እንዲሁም ከሚተገብራቸው የምርጫ ሕግ እና መመሪያዎች አንጻር በተጠየቀው አኳኋን ምርጫውን ለማካሄድ እንደሚቸገር አስታውቋል። 

የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ጉባኤ አፈ ጉባኤ አቶ ሙህየዲን አህመድ ክልሉ በቅንነት ከምርጫ ቦርድ ጋር በአካል ጭምር ለመነጋገር መሞከሩን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ክልሉ ጥያቄውን ያቀረበው በመጋቢት 6፤ 1987 ዓ. ም.  የሽግግር መንግስት የተወካዮች ምክር ቤት ባጸደቀው ውሳኔ መሰረት እንደሆነም ጠቁመዋል። በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ የብሔረሰቡ አባላት የመምረጥ መብት በክልሉ ሕገ መንግስት ላይም የተቀመጠ እንደሆነ ያብራራሉ።

በመስከረም 1997 ዓ.ም. የተሻሻለው የሐረሪ ሕዝብ ክልል ሕገ መንግስት፤ ስለ ጉባኤ አባላት አወካከል እና አመራርጥ በሚዳስስበት አንቀጽ 50 ላይ ይህንኑ ጉዳይ ተመልክቶታል። የክልሉ ሕገ መንግስት አንቀጽ 50፤ ንዑስ አንቀጽ 2 “የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላት፤ በክልሉ ውስጥና ከክልሉ ውጭ፣ በሌላ በኢትዮጵያ ክልሎችና ከተሞች ከሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰብ አባላት ይመረጣል” ሲል ደንግጓል።

ምርጫ ቦርድ በጻፈው የምላሽ ደብዳቤ ላይ፤ በ1987 በተወካዮች ምክር ቤት የተላለፈውን ውሳኔም ሆነ ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም የነበሩ ምርጫዎችን ያስፈጸመበት መመሪያ ነው በሚል በሐረሪ ክልል የቀረቡለትን ሰነዶች መመርመሩን ገልጿል። ሰነዶቹን እና ከዚህ ቀደም የተካሄዱ ምርጫዎችን ከሕገ መንግስቱ አንጻር መፈተሹን አብራርቷል። 

“በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት መሰረት በአንድ ክልል የመንግስት አወቃቀር ውስጥ የሚገኙ የምክር ቤት አባላት መመረጥ የሚኖርባቸው በክልሉ ድምጽ መስጠት በሚችሉ ነዋሪዎች ነው” ሲል የሚንደረደረው የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ፤ “ከዚህ ውጭ ሕገ መንግስቱ፤ አንድ ቁጥሩ አነስተኛ የሆነ ብሔረሰብ ለክልል ምክር ቤቶች አባላት ሲያስመርጥ ከክልሉ ውጭ ያሉ የብሔረሰቡ አባላት እንዲመርጡ የደነገገው ነገር የለም” ሲል አትቷል። 

ከዚህ በተጨማሪም ቦርዱ ባደረገው ምርመራ፤ ለሐረሪ ብሔረሰብ አባላት ለብቻው የተለየ አሰራር መተገበር የሚያስችል ድንጋጌ በሕገ መንግስቱ ላይ አለማግኘቱን አብራርቷል። ቦርዱ የሐረሪ ክልልን ጥያቄ ቢቀበልና ሌሎች አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ብሔረሰቦች ተመሳሳይ ጥያቄ አንስተው ቦርዱ “አልቀበልም” ቢል፤ በቦርዱ “ፍትሐዊነት እና ገለልተኛነት” ላይ ጥያቄ እንደሚያስነሳ አመልክቷል። 

በሐረሪ ክልል በቀረበው ጥያቄ ላይ የተያያዘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰነድ ላይ የተላለፈው ውሳኔ አግባብ ያለውን የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ የተጠቀሰበት አለመሆኑን ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ላይ በተጨማሪነት አንስቷል። ሰነዱ የተወካዮች ምክር ቤት “ማህተም ያረፈበት አይደለም” በማለትም የሰነዱን ህጋዊነት ጥያቄ ውስጥ ከትቷል። ቦርዱ እነዚህን ምክንያቶች በደብዳቤው ከዘረዘረ በኋላ የሐረሪ ክልልን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።  

ምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንደማይቀበሉት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጹት የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ጉባኤ አፈ ጉባኤ፤ “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ ግልጽ ሆኖ ሳለ ቦርዱ እንደማይተገብረው ማስታወቁን አልስማማበትም” ብለዋል። ከዚህ ቀደም ላለፉት አምስት ምርጫዎች በክልሉ ሲካሄድ የነበረውን የአመራረጥ ሂደት ቦርዱ “ሕገ መንግሥታዊ አይደለም” ሲል ያወጣው መግለጫም “ተቀባይነት የሌለው ነው” ሲሉ አጣጥለዋል።   

“የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ ግልጽ ሆኖ ሳለ ቦርዱ እንደማይተገብረው ማስታወቁን አልስማማበትም”

አቶ ሙህየዲን አህመድ – የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ጉባኤ አፈ ጉባኤ

የሐረሪ ክልል ያቀረባቸውን የሰነድ ማስረጃዎች ቦርዱ የመመርመር ኃላፊነት ነበረበት የሚሉት አቶ ሙህየዲን፤ “የተቋሙን ድክመት ወደ እኛ የማምጣት አዝማሚዎች ይታያሉ” በማለት ወንጅለዋል። “እኛ ውሳኔው መኖሩ መግለጻችን በቂ ነው” ያሉት አፈ ጉባኤው፤ “ቦርዱ ሰነዶቹን ማህተም የላቸውም ካለ የሚመለከተውን አካል ጠይቆ ማጣራት ነበረበት” ሲሉ ተችተዋል።     

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች፤ ከክልላቸው ውጪ ባሉት ከተሞች እንዲመርጡ የሚያደርግ ድንጋጌ እንዳለው የሚከራከሩት አቶ ሙህየዲን፤ የሐረሪ ክልልም በዚሁ መሰረት “ምርጫውን ማካሄድ አለበት” ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል። ይህ ጉዳይ በክልሉ ሕገ መንግሥት ሥር በግልጽ እንደተደነገገ ጠቁመው፤ የምርጫ ቦርድ በምርጫ አፈፃጸም መመሪያው ላይ፤ “ሊያከብራቸው ከሚገባው የክልል ሕገ መንግሥቶች በተቃራኒው እየሰራ ነው” ሲሉ ነቅፈዋል።  

የምርጫ ቦርድ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመሆኑ፤ የምክር ቤቱን ማንኛውም ውሳኔዎች አክብሮ መስራት አለበት ሲሉም አፈ ጉባኤው አስታውቀዋል። ስለሆነም ምርጫ ቦርድ ያወጣው ክልከላ “የሕዝብ ተወካዮች ውሳኔ እና ሕገ መንግስት የተጣሰበት ነው የሚል አቋም አለን” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል፡፡ 

ቦርዱ በዚህ አቋሙ የሚጸና ከሆነ፤ “ሕዝቡ የሚጠይቃቸውን ሀሳቦች እናስፈጽማለን” ያሉት አፈ ጉባኤው “ሕዝቡ አልመርጥም ካለ እኛም በእጩነት አንወዳደርም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)