በቅድስት ሙላቱ
የሐረሪ ብሔረሰብ አባላት የምርጫ ተሳትፎን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያስተላለፈውን ውሳኔ የተቃወመው የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ጉባኤ፤ ጉዳዩን ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊወስደው ነው። ጉባኤው የቦርዱን ውሳኔ “በአጭር ጊዜ ለማስቀየር ያስችላሉ” ያላቸውን ህጋዊ አማራጮች በሙሉ ጎን ለጎን እንደሚያስኬድ አስታውቋል።
የሐረሪ ክልል ከፍተኛ የሕግ አውጪ አካል በሆነው የክልሉ ምክር ቤት ስር የሚገኘው ጉባኤው፤ እነዚህን እርምጃዎች ለመውሰድ ከውሳኔ ላይ የደረሰው ትላንት እሁድ ሚያዝያ 3፤ 2013 ካካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ ነው። አስራ አራት አባላት ያሉት ጉባኤው በትላንቱ ስብሰባው፤ “የሀረሪዎችን ህገ መንግስታዊ ውሳኔ የምርጫ ቦርድ ሊሸራርፍ አይችልም” በማለት የቦርድን ውሳኔ በጽኑ አውግዟል።
የብሔራዊው ጉባኤ አፈ ጉባኤ አቶ ሙህየዲን አህመድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ ጉባኤው ዛሬ አሊያም በሚመጡት ቀናት ውስጥ፤ ጉዳዩን በተመለከተ የሐረሪ ክልል ያለውን አቋም የሚገልጽ ደብዳቤ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስገባል። የደብዳቤው ይዘት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለምርጫ ቦርድ አቅጣጫ እንዲሰጥ የሚጠይቅ እንደሚሆንም አስረድተዋል።
ጉባኤው ጉዳዩ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወስደው፤ እንዳለፉት አምስት ጠቅላላ ምርጫዎች ሁሉ፤ ከሐረሪ ክልል ውጭ ያሉ የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች የጉባኤውን አባላት መምረጥ የሚያስችላቸው አካሄድ በዘንድሮውም ምርጫም እንዲተገበር ለምርጫ ቦርድ የቀረበው ጥያቄ ውድቅ ከተደረገ በኋላ ነው። ምርጫ ቦርድ ጥያቄውን ያልተቀበለው፤ ጉዳዩን ከኢፌዲሬ ሕገ መንግስት እንዲሁም ከሚተገብራቸው የምርጫ ሕግ እና መመሪያዎች አንጻር ከመረመረ በኋላ እንደሆነ ገልጾ ነበር።
ብሔራዊ ጉባኤው ከትላንቱ ስብሰባው በኋላ ባወጣው መግለጫ ምርጫ ቦርድ ሕገ መንግስቱን በማጣቀስ ያሳለፈውን ውሳኔ አጥብቆ ተቃውሟል። “ ‘ምርጫ ቦርድ በህገ መንግስቱ ላይ መምረጥ የሚችሉት የክልሉ ነዋሪዎች ብቻ ናቸው’ ተብሎ ተደንግጓል ማለቱ፤ አግባብ ባለው የህግ አንቀፅ የታገዘ ባለመሆኑ፤ የህዝባችንን መብት ለማፈን የተደረገ ሙከራ ነው” ሲል ጉባኤው ነቅፏል።
የምርጫ ቦርድ ውሳኔ በአጠቃላይ “ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን የሚፃረር እና ፍትሀዊነት የጎደለው” ሲል የተቸው የጉባኤው መግለጫ፤ ቦርዱ ውሳኔውን በድጋሚ እንዲያጤነው ጠይቋል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን የጉባኤው አባላት ጉዳዩን ለህግ እና ሕገ መንግስት ተርጓሚ አካላት በማቅረብ ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ለማስከበር መስማማታቸውን በመግለጫው ተጠቅሷል።
የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አፈ ጉባኤ አቶ ሙህየዲን፤ ጉዳዩን ወደ ፓርላማ ከመውሰድ ጎን ለጎን ክልሉ የዳኝነት አማራጮችንም ሊጠቀም እንደሚችል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የዳኝነት ስርዓቱን በመከተል “ምርጫ ቦርድን ልንከስ እንችላለን” ሲሉ የክልሉን የወደፊት አካሄድ ፍንጭ የሚሰጡት አፈ ጉባኤው፤ ጉዳዩ ከዚህም ተሻግሮ የሕገ መንግስታዊ ትርጓሜ ጉዳዮችን ወደ ሚመለከተው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊደርስ እንደሚችልም ያብራራሉ።
መጪው ምርጫ በግንቦት ወር መጨረሻ ከመካሄዱ አንጻር የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን የሚገልጹት የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አፈ ጉባኤ፤ ከተወካዮች ምክር ቤት “በአጭር ጊዜ መልስ ይሰጠናል ብለን እንጠብቃለን” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የሐረሪ ክልል መንግስት ካቢኔ በትላንትው ዕለት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባው፤ እንደ ክልሉ ብሔራዊ ጉባኤ ሁሉ ተቃውሞውን አሰምቷል። ካቢኔው ምርጫ ቦርድ ያስተላለፈውን ውሳኔ፤ “ሕገ መንግስታዊ፣ ህጋዊ፣ ፍትሃዊ፣ አመክኖያዊ” ያልሆነ ሲል ገልጾታል። ካቢኔው ጉዳዩን በተመለከተ አግባብ ያለው አካል ተቋቁሞ ተገቢው የእርምት እርምጃ እንዲደረግ ውሳኔ በማሳለፍ የትላንትና ስብሰባውን አጠናቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)