የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መሪዎች በዝግ እንዲወያዩ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጥሪ አቀረቡ

46

በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ለአመታት ተደራድረው ከአንዳች ስምምነት መድረስ የተሳናቸው የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መሪዎች በሚቀጥሉት 10 ቀናት ተገናኝተው በዝግ እንዲወያዩ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጥሪ አቀረቡ። 

ካሁን ቀደም የተደረጉ ድርድሮች ወደ ስምምነት አለማድረሳቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመጋቢት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. የሶስቱ አገሮች መሪዎች ለትብብር እና ልዩነቶቻቸውን በሰላም ለመፍታት በፈረሙት ውል መሠረት ጥያቄውን ማቅረባቸውን ጽህፈት ቤታቸው ትናንት ዕኩለ ለሊት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። 

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከግብጽ እና ሱዳን መሪዎች የተፈራረሙት “የመርሆዎች ስምምነት” (Declaration of Principles) የተባለ ውል አስረኛ አንቀጽ፤ “ሶስቱ አገራት አለመግባባቶችን በምክክር ወይም በድርድር መፍታት ከተሳናቸው ዕርቅ ወይም ሽምግልና ሊጠይቁ ወይም ጉዳዩን ወደ መሪዎቻቸው ሊመሩ ይችላሉ” ይላል። ሱዳን የውይይት ጥሪውን ያቀረበችው ይህንን አንቀጽ በመጥቀስ ነው። 

የጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ ጽህፈት ቤት፤ “በቀጥታም ሆነ በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት በተደረጉ ድርድሮች ስምምነት ላይ ባለመደረሱ ሱዳን የሶስቱ አገሮች ጠቅላይ ሚኒስትሮች በቪዲዮ ኮንፈረንስ ዝግ ስብሰባ” እንዲደረግ ጥሪ ማቅረቧን አስታውቋል። በመግለጫው መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ፤ በሚቀጥሉት 10 ቀናት ውስጥ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የግብጹ አቻቸው ሙስጠፋ ማዶብሊ ጋር ተገናኝተው የታላቁ የህዳሴ ግድብን ድርድር ለመገምገም ጥያቄ አቅርበዋል። 

ሐምዶክ ለኢትዮጵያ እና የግብጽ አቻዎቻቸው በላኩት መልዕክት የግድቡ የግንባታ ሒደት ከፍ ባለ ደረጃ ሲደርስ ድርድሩ “ፈቅ ከማይልበት ደረጃ” መገኘቱ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ከመጀመሩ በፊት ከስምምነት መድረስን አንገብጋቢ ጉዳይ ያደርገዋል ብለዋል። የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ-መንበርን የሆኑት የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ትሺሴኬዲ፤ ተንገራግጮ የቆመውን ድርድር ለማስቀጠል በኪንሻሳ ያደረጉት ሙከራ ሳይሰምር ቀርቷል።  

ሶስቱ አገሮች በኪንሻሳ ካደረጉት ውይይት በኋላ፤ ኢትዮጵያ የግድቡ ሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሌት በመጪው ክረምት ከመቀጠሉ በፊት ለመረጃ ልውውጥ ባለሙያዎች እንዲያቀርቡ ጥሪ ብታደርግም ሱዳን እና ግብጽ ሳይቀበሉት ቀርተዋል። ግብጽ እና ሱዳን “የአፍሪካ ህብረት በነጻነት ጉዳዩን ለመምራት እንዳይችል እና የተሰጠውን ኃላፊነት በሚያኮስስ መልኩ ሌሎች ተዋናዮች ይህን ጉዳይ አብረው እንዲመሩ” ሐሳብ ማቅረባቸውን የኢትዮጵያ የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ተናግረዋል። 

ከልዩነቶቻቸው መካከል ሱዳን የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት የሚሳተፉበት የአራትዮሽ ድርድር እንዲካሔድ ጥያቄ ማቅረቧ ይገኝበታል። ይህንን ምክረ ሐሳብ ግብጽ ስትደግፍ ኢትዮጵያ ግን ሳትቀበለው ቀርታለች። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)