በታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድሮች እና ሁለቱ አገሮች በይገባኛል በሚወዛገቡባቸው የድንበር ጉዳዮች የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎች መልሰው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ የሉዓላዊነት ጥያቄ እንደሚያስነሱ ሱዳን አስጠነቀቀች። የሱዳን ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ትላንት አርብ ዕኩለ ለሊት ገደማ ባወጣው መግለጫ፤ የሁለቱ አገሮች ልዩነት በግድቡም ሆነ በድንበር ውዝግባቸው መበርታቱን የሚጠቁም የከረረ ትችት በኢትዮጵያ ላይ ሰንዝሯል።
የሱዳን ማስጠንቀቂያ የተደመጠው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ መርየም አል-ሳዲቅ በግድቡ ጉዳይ የአገራቸውን አቋም ለማስረዳት እና ድጋፍ ለማሰባሰብ በአፍሪካ አገራት ጉዞ በማድረግ ላይ በሚገኙበት ወቅት ነው። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በትላንት መግለጫው፤ ሱዳን ኢትዮጵያን በአባይ ውሃ እና በድንበር ጉዳዮች ላይ ከተፈረሙ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ለማቆራኘት እየሰራች ነው እያሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ የሚሰጧቸውን መግለጫዎች በጥልቅ ሀዘኔታ እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል።
“አገራት እና መንግሥታት በቀደሙ አገዛዞች እና መንግሥታት ለተፈረሙ ስምምነቶች እና ውሎች ቁርጠኛ መሆናቸው በዓለም አቀፍ ግንኙነት መሠረት የጣለ ልማድ ነው” ብሏል የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ መግለጫ። “ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና ውሎችን፤ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን በማውጣት፣ ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል እነርሱን የሚቃረን የህዝብ አስተያየት በማደራጀት ገሸሽ ማድረግ፤ ዓለም አቀፍ ግንኙነትን የሚበክል፣ ለአንድ ወገን ፍላጎት ተጋላጭ የሚያደርግ፣ ቀውስን የሚያስፋፋ፣ የጥሩ ጉርብትና መሠረትን የሚያናጋ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው” ሲል የከረረ ተቃውሞ ሰንዝሯል።
ስምምነቶች ሲፈረሙ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር ሱዳን በአንፃሩ ቅኝ ተገዢ እንደነበረች በመግለጫው የጠቀሰው የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተናጠል የትኞቹ ስምምነቶች እንደሆኑ ማብራሪያ አልሰጠም። “ለፕሮፓጋንዳ እና ለሀገር ውስጥ የፖለቲካ ምክንያቶች እንዲህ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን እየመረጡ ውድቅ ማድረግ በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት ካለው ስምምነት ለመድረስ የማይረዳ ጎጂ እና ዋጋ የሚያስከፍል እንደሆነ ለማሳሰብ እንወዳለን” ብሏል።
የሱዳን ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በመግለጫው “አሳሳች ሀሳብ ማቅረብ እና ከዚህ ቀደም የተፈረሙ ስምምነቶችን ውድቅ ማድረግ ማለት ከስምምነቶቹ በአንዱ ከሱዳን ተላልፎ በተሰጠው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ መክተት እንደሆነ ለኢትዮጵያ ማስታወስ አያስፈልገንም” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይዞታ “ቀደም ሲል የሱዳን አካል ነበር” የሚለው ክስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሱዳን ፖለቲከኞች፣ ምሁራን እና መገናኛ ብዙሃን ዘንድ በተደጋጋሚ እየተነሳ ይገኛል።
በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል በተለይ በሁለቱ አበይት ጉዳዮች ምክንያት የበረታው ውጥረት የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካንን ጨምሮ ዓለም አቀፉን የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ ካሳሰቡ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የሾሟቸው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ በአፋጣኝ መፍትሔ ከሚያፈላልጉላቸው ቀውሶች መካከል የኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኙነትን ያሻከሩት ሁለቱ ጉዳዮች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ውጊያ ተቀስቅሶ የተፈናቀሉ ከ60 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ሱዳን መሰደዳቸውን ተከትሎ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት የስደተኞቹ ሁኔታው እንደሚያሳስባቸው ሲገልጹ ቆይተዋል። ከዚህ ቀደም በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልዩ መልዕክተኛነት ወደ አዲስ አበባ አቅንተው ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ሹማምንት ጋር የተወያዩት ሴናተር ክሪስ ኩንስ እና ሌላው የሴኔት ባልደረባቸው ክሪስ ቫን ሆለን በመጪው ሰኞ ወደ ካርቱም እንደሚያቀኑ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ለማረጋገጥ ችላለች።
ለሶስት ቀናት በሱዳን የሚቆዩት ሁለቱ ሴናተሮች ከትግራይ ክልል የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ከሚገኙባቸው መጠለያዎች አንዱ የሆነውን እና አል ገዳሪፍ ግዛት ውስጥ የሚገኘውን የኡም ራኩባ መጠለያ ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። በኡም ራኩባ ወደ 20 ሺህ ኢትዮጵያውያን ተጠልለው እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)