ምርጫ ቦርድ በሰበር ሰሚ ችሎት ላቀረበው ይግባኝ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ምላሽ ሰጠ

በቅድስት ሙላቱ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች የመምረጥ መብትን በተመለከተ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ላቀረበው ይግባኝ፤ የክልሉ ብሔራዊ ጉባኤ ዛሬ በፍርድ ቤት ምላሽ ሰጠ። ጉባኤው በምርጫ ቦርድ በኩል ለተነሱ የመከራከሪያ ነጥቦች ምላሽ የሚሆን ባለ 12 ገፅ መልስ ያቀረበው በችሎቱ ጽህፈት ቤት በኩል ነው። 

ምርጫ ቦርድ ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ያለው፤ ከክልሉ ውጪ ያሉ የሐረሪ ብሔር ተወላጆች ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ በአባልነት የሚወዳደሩ ግለሰቦችን የመምረጥ መብታቸው እንዲከበር የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ነው። የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላት የምርጫ ሂደት ከዚህ ቀደም በነበሩ አምስት ተከታታይ ሀገራዊ ምርጫዎች ላይ ይደረግ በነበረው መልኩ እንዲፈጸምም ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። 

ይህንን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ የተቃወመው ምርጫ ቦርድ ለሰበር ሰሚ ችሎት የይግባኝ አቤቱታውን ያስገባው ባለፈው ሳምንት ሰኞ ግንቦት 2፤ 2013 ነበር። ቦርዱ በይግባኙ ላይ፤ በጠቅላይ ፍርድ ቤት በተካሄደው ክርክር ወቅት የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ “በልዩ ሁኔታ ስለሚቋቋም የምርጫ ጣቢያ” በአዋጅ የተደነገገውን በማንሳት መከራከሩን አስታውሷል። 

በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ አንቀጽ 17 (1) ላይ ስለ እንደዚህ አይነት የምርጫ ጣቢያዎች በዝርዝር የተደነገገው፤ በሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤው ከሚጠይቀው ጥያቄ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ሲል ምርጫ ቦርድ በይግባኙ ተከራክሮ ነበር። በአዋጁ በልዩ ሁኔታ የምርጫ ጣቢያ እንዲቋቋምላቸው የሚገቡ የህብረተሰብ ክልሎች ቢዝረዘርም፤ የብሔራዊ ጉባኤው ጥያቄ ያቀረበላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ግን በአዋጁ አለመካተታቸውን ቦርዱ በይግባኙ አትቷል። በዚህም ምክንያት ጠቅላይ ፍርድ ቤት “ይህንን የማየት ስልጣን አልነበረውም” ሲል ተሟግቷል። 

ለዚህ የምርጫ ቦርድ ይግባኝ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ዛሬ ሰኞ ባስገባው ምላሽ፤ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀፅ 17 (1) ስር የምርጫ ሂደትን በተመለከተ ቦርዱ በሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የሚቀርቡ የይግባኝ አቤቱታዎችን ለማየት ስልጣን ያለው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሆነ ጠቁሟል። በዚህም ምክንያት “የታች ፍርድ ቤት ውሳኔ አግባብ ነው” ሲል ጉባኤው ምላሽ ሰጥቷል። 

የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ሌላው ምላሽ ያቀረበበት የይግባኝ አቤቱታ፤ የሐረሪ ክልል ህገ መንግስት ከፌደራል ህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን መሆኑን በመጥቀስ በምርጫ ቦርድ በኩል ከቀረበው መከራከሪያ ጋር የተያያዘ ነው። ቦርዱ ሁለቱ ህገ መንግስቶች የሚቃረኑ በመሆኑ “ጉዳዩን የማየት ስልጣን ያለው የፌደሬሽን ምክር ቤት እንጂ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አይደለም” በሚል ያቀረበው አቤቱታ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጎበት ነበር። 

ይህ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ “መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው” ያለው ቦርዱ፤ ሰበር ሰሚ ችሎት ሊመረምረው ይገባል ሲል ምርጫ ቦርድ በይግባኙ ላይ ጠይቋል። የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ለዚህ ይግባኝ በሰጠው ምላሽ፤ በሐረሪ ክልል ህገ መንግስት አንቀፅ 50(2) እና በፌደራሉ ህገ መንግስት አንቀፅ 50 (3) የተቀመጡት ድንጋጌዎች እርስ በራሳቸው የማይጣረሱ እና ህገ መንግስታዊ ትርጓሜ የሚያስፈልጋቸው አይደሉም በማለት ነው። 

ይህንም ሲያስረዳም በክልሉ ህገ መንግስት ስር የሐረሪን ምክር ቤት ከሚያዋቅሩት ሁለት ጉባኤዎች መካከል አንዱ የሆነው የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላት በክልሉ ውስጥና ከክልሉ ውጪ በሚገኙ የሀረሪ ብሔረሰብ አባላት እንደሚመረጡ መደንገጉን ጠቅሷል።  የፌደራል ህገ መንግስት አንቀፅ 50 (3) የሚደነግገው በበኩሉ የክልል ምክር ቤት ተጠሪነቱ ለወከለው የክልል ህዝብ እንደሆነ መሆኑንም አስታውሷል። 

ሁለቱ ድንጋጌዎች የሚያወሩት ስለሁለት የተለያዩ አካላት እና ርዕሰ ጉዳዮች በመሆኑ ሊቃረኑ አይችሉም ያለው የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ፤ ስለዚህም የጠቅላይ ፍርድ ቤት እነዚህ ግልጽ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ውሳኔ መስጠቱ፤ “ከስልጣኑ በላይ ሄዶ ህገ መንግስታዊ ትርጉሜ ሰጥቷል የሚያስብል አይደለም” በማለት በምላሹ ሞግቷል። ምርጫ ቦርድ “ሁለቱ ድንጋጌዎች ይቃረናሉ” በሚል በስር ፍርድ ቤት ያላነሳውን መከራከሪያ አሁን ለሰበር ሰሚ ችሎት ማቅረቡ ከስነ ስርዓት ውጪ ነው በማለትም ጉባኤው በተጨማሪነት ነጥብነት አንስቷል። 

ምርጫ ቦርድ በይግባኙ ላይ በሶስተኛ መከራከሪያነት ያቀረበው ጉዳይም እንደ ሁለተኛው ጉዳይ ሁሉ ከሐረሪ ክልል ህገ መንግስት ጋር የተያያዘ ነው። የምርጫ ህጎችን የማውጣት ስልጣን የፌደራል መንግስት ስልጣን መሆኑን እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  ይህንኑ የሚመለከቱ ህጎች እንደሚያወጣ በፌደራሉ ህገ መንግስት በግልጽ መደንገጉን ያስታወሰው ቦርዱ፤ የሐረሪ ክልል ህገ መንግስት ግን ከተሰጠው ስልጣን ውጪ በሆነ መልኩ ከምርጫ ጋር የተያያዘ ድንጋጌ ማካተቱ “ከፍተኛ የሆነ የህግ ስህተት ነው” ሲል ተሟግቷል።  

በዚህም ምክንያት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሐረሪ ክልል ህገ መንግስት ምርጫን የተመለከተ ድንጋጌ ተቀብሎ ሊወስን አይገባም በማለት ምርጫ ቦርድ በይግባኙ ላይ አስቀምጧል። የፌደራል ህገ መንግስት አነስተኛ ቁጥር ላላቸው ብሔረሰቦች የሚያደርገው ጥበቃ በክልሉ ውስጥ (territorial) እንጂ ከክልሉ ውጪ (non – territorial) አለመሆኑንም በተጨማሪ መከራከሪያነት አንስቷል። 

በሐረሪ ክልል ህገ መንግስት ላይ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ከክልሉ ውጪ ባሉ የብሔረሰቡ አባላት ጭምር እንዲመረጥ ማስቀመጡ እና ይህንንም ድንጋጌ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተቀብሎ ያለ ስልጣኑ ህገ መንግስትን መተርጎሙን ምርጫ ቦርድ በይግባኙ ላይ አመልክቷል። የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዚህ ድርጊቱ “ተደራራቢ የህግ ጥሰት ፈፅሟል” ያለው ምርጫ ቦርድ፤ የሰበር ሰሚ ችሎት ይህን የህግ ጥሰት እንዲያርም ሲል አቤቱታውን አቅርቧል።

የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ለዚህ አቤቱታ በሰጠው ምላሽ፤ ምርጫ ቦርድ የፌደራል ህገ መንግስቱን ድንጋጌዎች “በተሳሳተ መልኩ ተርጉሞታል” ብሏል። በፈደራሉ ህገ መንግስት ላይ የተዘረዘሩ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ድንጋጌዎች በሙሉ የነዋሪነትን መስፈርት ባላቀመጡበት ሁኔታ፤ ህገ መንግስቱ በ “ክልል ውስጥ (territorial) የሆነ መርህን ይከተላል ማለቱ አግባብነት የለውም” ሲል ብሔራዊ ጉባኤው መከራከሪያውን አስቀምጧል። 

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ የቀረበውን አጠቃላይ አቤቱታ ውድቅ በማድረግም የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ እንዲያጸና የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ በምላሽ ማጠቃለያው ላይ ጠይቋል። የብሔራዊ ጉባኤውን ዝርዝር ምላሽ በጽህፈት ቤት በኩል የተቀበለው ሰበር ሰሚ ችሎቱ፤ ምርጫ ቦርድ ለተነሱት መከራከሪያዎች የመልስ መልስ እንዲሰጥ ለረቡዕ ግንቦት 11 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)