የቀድሞ የወላይታ ዞን አመራሮች ከእስር ተፈቱ

በተስፋለም ወልደየስ 

ላለፉት 10 ወራት በእስር ላይ የቆዩት የወላይታ ዞን የቀድሞ አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ እና ምክትላቸው አቶ ጎበዜ ጎዳና ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 17 ከእስር ተፈቱ። ሁለቱ የቀድሞ አመራሮች ከእስር የተፈቱት በተከሰሱበት ወንጀል በፍርድ ቤት በነጻ ከተሰናበቱ በኋላ እንደሆነ ጠበቃቸው አቶ ተመስገን ዋጃና ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ሁለቱ አመራሮች የተከሰሱት “ስልጣናቸውን አላግባብ የመገልገል” ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ነበር። በዚህ ክስ ስር የቀድሞው የወላይታ ዞን የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተከተል ጎአም ተካትተዋል። የሶስቱን ተከሳሾች ክስ ሲመለከት የቆየው የወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው ውሎው፤ ተከሳሾቹ ወንጀሉን ባለመፈጸማቸው በነጻ እንዲሰናበቱ ብይን መስጠቱን ጠበቃ ተመስገን ገልጸዋል። 

ፍርድ ቤቱ የወላይታ ዞን የቀድሞ አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ በተከሰሱበት ሁለተኛ መዝገብም ተመሳሳይ ውሳኔ መስጠቱን ጠበቃቸው አስረድተዋል። በአቶ ዳጋቶ ላይ የቀረበው ሁለተኛ ክስ፤ ከነብይ ኢዩ ጩፋ የጉቦ ገንዘብ በመቀበል የኢንቨስትመንት መሬት እንዲሰጣቸው አድርገዋል የሚል ነበር።

አቶ ኢዩ ጩፋ በሶዶ ከተማ ለኢንቨስትመንት የሚውል 1,000 ካሬ ሜትር ገደማ ከሰው ገዝተው እንደነበር የሚገልጹት ጠበቃ ተመስገን፤ ለማስፋፊያ በሚል ተጨማሪ 300 ካሬ ሜትር ጠይቀው እንደተፈቀደላቸው ያስታውሳሉ።

ይህን የማስፋፊያ መሬት፤ “የጉቦ ገንዘብ ተቀብለው የፈቀዱት የቀድሞው የዞኑ አስተዳዳሪ ናቸው” የሚል ክስ ቢቀርብም፤ የተከሳሽ ጠበቃ ግን ውሳኔ የተላለፈው በተለያዩ እርከኖች በሚገኙ የመንግስት አካላት ነው ሲሉ ቀደም ባሉ ችሎቶች መከራከራቸውን ጠቅሰዋል። ይህንኑ በሰው ምስክሮች እና በሰነድ ማስረጃ በማስደገፍም ለፍርድ ቤቱ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። 

የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ፍርድ ቤቱ፤ ተከሳሽ “የቀረበባቸውን ወንጀል በሚገባ ተከላክለዋል” በሚል በነጻ እንዲሰናበቱ በዛሬው ችሎት ብይን መስጠቱን ጠበቃ ተመስገን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። በዛሬው ችሎት ሶስቱ የቀድሞ የወላይታ ዞን አመራሮች በአካል ቀርበው ሂደቱን የተከታተሉ ሲሆን ነብይ ኢዩ ጩፋ ግን አልተገኙም።

ወደ አራት ሰዓት ተኩል ገደማ ከተጠናቀቀው ከዛሬው የችሎት ውሎ በኋላ ተከሳሾቹ ወደ ሶዶ ማረሚያ ቤት ከተወሰዱ በኋላ እኩለ ቀን አካባቢ ከእስር መለቀቃቸውን ጠበቃ ተመስገን ተናግረዋል። የአቶ ዳጋቶን መፈታት ተከትሎ በርካታ የሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ከማረሚያ ቤቱ ቅጽር ግቢ ውጪ እና በመኖሪያ ቤታቸው በመገኘት ደስታቸውን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)