ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከሳውዲ አረቢያ ለማስመለስ ኮሚቴ ተቋቋመ

በበእምነት ወንድወሰን  

በሳውዲ አረቢያ በእስር ቤቶች፣ በስደተኛ መጠለያዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ የቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ቅጽር ግቢ ውስጥ የሚገኙ ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ኮሚቴ መቋቋሙን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ኮሚቴው የተቋቋመው ከሶስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ከክልል መንግስታት ተውጣጥቶ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ “የሚቻል ከሆነ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀስን ነው” ብለዋል። ይህንን ለማገዝም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሰላም ሚኒስቴር፣ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ እንዲሁም የክልል መንግስታት ያሉበት ኮሚቴ መዋቅሩንም ጠቁመዋል። 

ኢትዮጵያውያንን ለስደት ከሚያበቋቸው ምክንያቶች ውስጥ ድህነት እና ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ዋነኞች መሆናቸው የጠቀሱት ዲና፤ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ የስራ እድልን ከመፍጠር አንጻር የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ከፍተኛ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል። በኮሚቴው ውስጥ የተካተቱት የክልል መንግስታትም በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት የሚደረገውን ስደት ከመከላከል አንጻር ሚና እንዳላቸው አብራርተዋል። 

እነዚህ አካላት ያሉበት ኮሚቴ ዋና ዋና ስራዎች፤ የመጓጓዣ ሰነዶችን ማዘጋጀት፣ የስደተኞችን ማንነት ማረጋገጥ እና ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ ለመሆናቸው ጥያቄ የሚያቀርብ እንደሆነ ቃል አቃባዩ አስረድተዋል። በእስር እና በእንግልት ላይ የሚገኙት ስደተኞች “ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው” ማለት እንደማይቻል የተናገሩት ዲና፤ “የሶማሊያ፣ የጅቡቲ እንዲሁም የኤርትራ ስደተኞችም ተቀላቅለው ይገኛሉ” ብለዋል።

በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ጉዳይ በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ሳምንት ሰኔ 11 አንድ ልዑክ ወደ ቦታው መላኩ የሚታወስ ነው። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት የተውጣጡ አባላትን የያዘው ይሄው ልዑክ፤ ከሳውዲ አረቢያ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ተወያይቷል። በውይይቱ ላይም በሳውዲ አረቢያ ብዙ እንግልት ስለሚደርስባቸው እና እየደረሰባቸው ስላሉ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መነሳቱን ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል። (በኢትዮጵያ ኢንሳይደር)