ኢዜማ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ “በብዙ ችግሮች የታጀበ ነበር” አለ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሂደቱ እና ውጤቱ ለህዝብ የተገለጸ ባይሆንም “በብዙ ግልጽ ችግሮች የታጀበ ነበር” ሲል ገለጸ። ኢዜማ በቅድመ ምርጫና በምርጫ ወቅት ያጋጠሙት እና ለምርጫ ቦርድ ያሳወቃቸው ተግዳሮቶች ውሳኔ የማይሰጥባቸው ከሆነ ጉዳዩን ወደ ፍትህ አካላት እንደሚወስደውም አስታውቋል፡፡

ፓርቲው ይህን ያለው ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 17፤ 2013 አዲስ አበባ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ ነው። በመግለጫው ላይ የተገኙት የፓርቲው ምክትል መሪ አቶ አንዷለም አራጌ፤ ፓርቲያቸው በድምጽ መስጫ ዕለት ያጋጠሙት ችግሮች 460 እንደሚሆኑ እና ይህንኑ ለምርጫ ቦርድ እንዳሳወቁም ተናግረዋል።

“[ምርጫው] ያሰብነውን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማዋለድ በሚመጥን ሁኔታ የተከናወነ አይደለም” ያሉት የፓርቲው ምክትል መሪ አንዷለም አራጌ  “አጠቃላይ ሂደቱ በጣም የከፋ ነበር ይህን በድፍረት መናገር ይቻላል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ምክትል መሪው “ታግቶ ምርጫ የተካሄደበት” ባሉት ኦሮሚያ ክልል ፓርቲያቸው በቅድመ ምርጫ ወቅት እንደልብ መንቀሳቀስ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡ “በኦሮሚያ ክልል ያለው 178 ወንበር ከ547ቱ [ተወካዮች ምክር ቤት] ጋር ቢሰላ 36 ከመቶ ይሆናል” ያሉት አቶ አንዷለም “36 ሜትር ላይ [ቀድሞ] የቆመ መቶ ሜትር ሯጭ እናንተ ዜሮ ሜትር ላይ ቆማችሁ ሩጣችሁ ድረሱብኝ እና ካሸነፋችሁኝ እጨብጣችኋለሁ ማለት ቀልድ ነው” በማለት አስረድተዋል። 

የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው “ይህ ምርጫ የሽግግሩ አንድ አካል አንጂ መጨረሻ አይደለም። ኢትዮጵያ ገና ዲሞክራሲያዊ አገር አልሆነችም” በማለት አስረድተዋል። “ከምርጫው ማግስት ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ አገር ትሆናለች የሚል ህልምም ቅዠትም አልነበረንም። ነገር ግን መሰረቱን ይጥላል ብለን እናምናለን” ሲሉም አክለዋል፡፡

የፓርቲው ዕጩዎች ከምርጫ ውጤት ጋር በተያያዘ በማህበራዊ የትስስር ገጾቻቸው ያስተላለፏቸውን መልዕክቶች በተመለከተ የተጠየቁት አቶ የሺዋስ፤ “የፓርቲው አቋም፤ የስራ አስፈጻሚ ተሰብስቦ ወስኖ የሚገልጸው ብቻ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። “ኢዜማ ሽንፈቱን አምኖ ተቀብሏል ወይ?” በሚል በጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም “አምኖ ለመቀበልም፤ ላለመቀበልም ስልጣን የተሰጠው አካል መወሰን አለበት” ሲሉ ቅድሚያ ውጤቱ በምርጫ ቦርድ መጽደቅ እንዳለበት ተናግረዋል። 

የምርጫ ውጤትን በተመለከተ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት የኢዜማ ምክትል መሪ፤ “ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትክከለኛውን ውሳኔ ያሳልፋል ብለን እንጠብቃለን” ሲሉ የፓርቲውን አቋም አሳውቀዋል። “የድል አክሊል የመጫን ብቻ ሳይሆን፤ ህዝብ ካልመረጠን በጸጋ የመቀበል ዝግጁነት አለን” ሲሉም ተደምጠዋል። 

“እስካሁን ባላችሁ ተሳትፎ የሚቆጫችሁ ነገር አለ ወይ?” በሚል ለፓርቲው አመራሮች ለቀረበው ጥያቄ አቶ የሺዋስ ሲመልሱ፤ “የቻልነውን ያህል ሩጠናል። እስካሁን ያልሰራነው፣ ያሳደርነው ነገር የለም” ብለዋል።

ኢዜማ ከምርጫ ውጤት ጋር በተያያዘ በፓርቲው ስር ያሉም ሆነ ገለልተኛ አካላት የሚያቀርቧቸው ግምገማዎች ላይ ተመስርቶ አጠቃላይ ሁኔታውን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚያሳውቅ በዛሬው መግለጫው ላይ ጠቁሟል። ፓርቲው በምርጫ ሂደት ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በህግ አግባብ መጠየቁ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ከምርጫው ማግስት ጀምሮ የፓርቲውን መዋቅር በማጠናከር ወደ ስራ መግባቱንም አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)